በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

በአምላክ ቀኝ

በአምላክ ቀኝ

ምዕራፍ 132

በአምላክ ቀኝ

በጰንጠቆስጤ ዕለት መንፈስ ቅዱስ መፍሰሱ ኢየሱስ ወደ ሰማይ እንደተመለሰ የሚያሳይ ማስረጃ ነው። ይህ ከሆነ ከጥቂት ጊዜ በኋላ ደቀ መዝሙሩ እስጢፋኖስ ያየው ራእይም ኢየሱስ እዚያ እንደደረሰ ያረጋግጣል። እስጢፋኖስ በታማኝነት በሰጠው ምሥክርነት ሳቢያ ከመወገሩ ከጥቂት ጊዜ በፊት “እነሆ፣ ሰማያት ተከፍተው የሰው ልጅም በእግዚአብሔር ቀኝ ቆሞ አያለሁ” ሲል ተናግሯል።

ኢየሱስ በአባቱ ቀኝ ሆኖ “በጠላቶችህም መካከል ግዛ” የሚለውን ትእዛዝ አባቱ እስኪሰጠው እየተጠባበቀ ነበር። ሆኖም ኢየሱስ በጠላቶቹ ላይ እርምጃ የሚወስድበት ጊዜ እስኪደርስ ድረስ ምን ነገር ያከናውናል? ቅቡዓን ደቀ መዛሙርቱን በስብከቱ ሥራቸው በመምራትና ትንሣኤ አግኝተው በአባቱ መንግሥት ከእሱ ጋር ተባባሪ ነገሥታት እንዲሆኑ በማዘጋጀት በእነርሱ ላይ ይገዛል።

ለምሳሌ ያህል ኢየሱስ ደቀ መዛሙርት የማድረጉን ሥራ በሌሎች አገሮች በግንባር ቀደምትነት እንዲያካሄድ ሳውልን (ከጊዜ በኋላ ይበልጥ የታወቀው ጳውሎስ በሚለው ሮማዊ ስሙ ነው) መርጦታል። ሳውል ለአምላክ ሕግ ቀናተኛ የነበረ ቢሆንም የአይሁድ ሃይማኖታዊ መሪዎች በተሳሳተ አቅጣጫ እንዲጓዝ አድርገውት ነበር። በዚህም ምክንያት ሳውል በእስጢፋኖስ ግድያ ከመስማማቱም በላይ የኢየሱስ ተከታዮች ሆነው ያገኛቸውን ወንዶችና ሴቶች በሙሉ ይዞ ወደ ኢየሩሳሌም ለማምጣት የሚያስችል ሥልጣን እንደተሰጠው የሚገልጽ ደብዳቤ ከሊቀ ካህናቱ ከቀያፋ ተቀብሎ ወደ ደማስቆ ሄደ። ይሁን እንጂ ሳውል እየተጓዘ ሳለ በድንገት አንድ ደማቅ ብርሃን በዙሪያው ሲያንጸባርቅበት መሬት ላይ ወደቀ።

ከአንድ የማይታይ አካል የመጣ ድምፅ “ሳውል ሳውል፣ ስለ ምን ታሳድደኛለህ?” ሲል ጠየቀው። ሳውል “ጌታ ሆይ፣ ማን ነህ?” ሲል ጠየቀው።

“አንተ የምታሳድደኝ እኔ ኢየሱስ ነኝ” የሚል መልስ ተሰጠው።

በተአምራዊው ብርሃን ዓይኑ የታወረው ሳውል ወደ ደማስቆ ሄዶ መመሪያዎችን እንዲጠባበቅ ኢየሱስ ነገረው። ከዚያም ከኢየሱስ ደቀ መዛሙርት አንዱ ለሆነው ለሐናንያ በራእይ ተገለጠለት። ኢየሱስ ሳውልን አስመልክቶ ሐናንያን እንዲህ አለው:- “ይህ በአሕዛብም በነገሥታትም በእስራኤልም ልጆች ፊት ስሜን ይሸከም ዘንድ ለእኔ የተመረጠ ዕቃ ነው።”

በእርግጥም በኢየሱስ ድጋፍ ሳውልና (አሁን ጳውሎስ ተብሎ የሚታወቀው) ሌሎች ወንጌላውያን በስብከቱና በማስተማሩ ሥራቸው እጅግ ተሳክቶላቸዋል። እንዲያውም ጳውሎስ ወደ ደማስቆ በሚወስደው መንገድ ላይ ኢየሱስ ከተገለጠለት ከ25 ዓመታት ገደማ በኋላ ‘ምሥራቹ ከሰማይ በታች ባለው ፍጥረት ሁሉ ዘንድ ተሰብኳል’ ሲል ጽፏል።

ሌሎች ብዙ ዓመታት ካለፉ በኋላ ኢየሱስ በጣም ለሚወደው ሐዋርያው ለዮሐንስ ተከታታይ የሆኑ ራእዮችን አሳየው። ዮሐንስ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል በሆነው የራእይ መጽሐፍ ላይ በገለጻቸው በእነዚህ ራእዮች አማካኝነት ኢየሱስ በመንግሥቱ ሥልጣን ሲመጣ በሕይወት ቆይቶ አይቷል ማለት ይቻላል። ዮሐንስ “በመንፈስ” ወደፊት ወደሚመጣው የ“ጌታ ቀን” እንደተወሰደ ተናግሯል። ይህ “ቀን” ምንድን ነው?

ኢየሱስ ስለ መጨረሻዎቹ ቀኖች የተናገረውን ትንቢት ጨምሮ የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶችን በሚገባ ስንመረምር የ“ጌታ ቀን” የጀመረው ታላቅ ታሪካዊ ክንውን በተፈጸመበት ዓመት ማለትም በ1914 እንደሆነ እንረዳለን! ስለዚህ ኢየሱስ ያላንዳች ሕዝባዊ አቀባበል በማይታይ ሁኔታ የተመለሰው በ1914 ነው። መመለሱን ያወቁት ታማኝ አገልጋዮቹ ብቻ ናቸው። በዚያ ዓመት ይሖዋ በጠላቶቹ መካከል እንዲገዛ ለኢየሱስ ትእዛዙን አስተላልፏል!

ኢየሱስ የአባቱን ትእዛዝ በማክበር ሰይጣንንና አጋንንቱን ወደ ምድር ወርውሮ ሰማያትን አጽድቷል። ዮሐንስ ይህ ሲፈጸም በራእይ ካየ በኋላ አንድ ድምፅ ከሰማይ “አሁን የአምላካችን ማዳንና ኃይል መንግሥትም የክርስቶስም ሥልጣን ሆነ” ብሎ ሲያውጅ ሰማ። አዎን፣ በ1914 ክርስቶስ ንጉሥ ሆኖ መግዛት ጀምሯል!

ይህ በሰማይ ላሉ የይሖዋ አምላኪዎች እንዴት ያለ አስደሳች ዜና ነው! “ሰማይና በውስጡ የምታድሩ ሆይ፣ ደስ ይበላችሁ” ተብለዋል። ይሁን እንጂ በምድር ያሉት ሰዎች ሁኔታስ ምን ይመስላል? ከሰማይ የመጣው ድምፅ እንዲህ ሲል ቀጠለ:- “ለምድርና ለባሕር ወዮላቸው፣ ዲያብሎስ ጥቂት ዘመን እንዳለው አውቆ በታላቅ ቁጣ ወደ እናንተ ወርዶአልና።”

አሁን ያለነው በዚህ ጥቂት ዘመን ውስጥ ነው። በአሁኑ ጊዜ ሰዎች አምላክ ለሚያመጣው አዲስ ዓለም ይበቁ እንደሆነ አለዚያም ይጠፉ እንደሆነ እያሳዩ ናቸው። የወደፊቱ ዕጣህ የተመካው በክርስቶስ አመራር ሥር በምድር ዙሪያ እየተሰበከ ላለው የአምላክ መንግሥት ምሥራች በምትሰጠው ምላሽ ላይ እንደሆነ ጥርጥር የለውም።

ከዚያ በኋላ ኢየሱስ ክርስቶስ የአምላክ ወኪል ሆኖ በማገልገል መላውን የሰይጣን የነገሮች ሥርዓትና ሥርዓቱን የሚደግፉትን ሰዎች በሙሉ ከምድር ላይ ጠራርጎ ያጠፋል። ኢየሱስ በዚህ መንገድ ክፋትን ሁሉ ጠራርጎ የሚያጠፋው በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ሐርማጌዶን ወይም አርማጌዶን ተብሎ በተጠራው ጦርነት ይሆናል። ከዚያ በኋላ ከይሖዋ አምላክ ቀጥሎ በአጽናፈ ዓለም ውስጥ ታላቁ አካል የሆነው ኢየሱስ ሰይጣንንና አጋንንቱን ለሺህ ዓመት አስሮ ወደ “ጥልቁ” ይጨምራቸዋል፤ ይህም የሞት ያህል ከእንቅስቃሴ ውጪ መሆንን ያመለክታል። ሥራ 7:​55-60፤ 8:​1-3፤ 9:​1-19፤ 16:​6-10፤ መዝሙር 110:​1, 2፤ ዕብራውያን 10:​12, 13፤ 1 ጴጥሮስ 3:​22፤ ሉቃስ 22:​28-30፤ ቆላስይስ 1:​13, 23፤ ራእይ 1:​1, 10፤ 12:​7-12፤ 16:​14-16፤ 20:​1-3፤ ማቴዎስ 24:​14

▪ ኢየሱስ ወደ ሰማይ ካረገ በኋላ የት ተቀመጠ? ይጠባበቅ የነበረውስ ነገር ምንድን ነው?

▪ ኢየሱስ ወደ ሰማይ ካረገ በኋላ እነማንን ሲገዛ ቆይቷል? አገዛዙስ የተገለጠው እንዴት ነው?

▪ የ“ጌታ ቀን” የጀመረው መቼ ነው? በጌታ ቀን መጀመሪያ ላይስ ምን ነገር ተከናውኗል?

▪ በአሁኑ ጊዜ እየተካሄደ ያለው የስብከቱ ሥራ እያንዳንዳችንን በግለሰብ ደረጃ የሚነካን እንዴት ነው?

▪ የስብከቱ ሥራ ከተጠናቀቀ በኋላ ምን ነገሮች ይከናወናሉ?