በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

በአትክልቱ ሥፍራ ያሳለፈው ሥቃይ

በአትክልቱ ሥፍራ ያሳለፈው ሥቃይ

ምዕራፍ 117

በአትክልቱ ሥፍራ ያሳለፈው ሥቃይ

ኢየሱስ ጸሎቱን ሲጨርስ እሱና 11 የታመኑ ሐዋርያቱ ለይሖዋ የውዳሴ መዝሙር ዘመሩ። ከዚያም ደርብ ላይ ከሚገኘው ክፍል ወጥተው በቀዝቃዛው የሌሊት ጨለማ የቄድሮንን ሸለቆ ተሻግረው እንደገና ወደ ቢታንያ አቀኑ። ሆኖም በመካከሉ መንገድ ላይ እጅግ ተወዳጅ ወደሆነው ወደ ጌቴሴማኒ የአትክልት ሥፍራ ጎራ አሉ። ይህ የአትክልት ሥፍራ የሚገኘው በደብረ ዘይት ተራራ ላይ አለዚያም በዚያው አካባቢ ነው። ኢየሱስ ብዙ ጊዜ ከሐዋርያቱ ጋር ሆኖ ወደዚህ ሥፍራ እየመጣ በወይራ ዛፎቹ መካከል ከእነርሱ ጋር ይወያይ ነበር።

ከሐዋርያቱ መካከል ስምንቱን ለብቻቸው ተዋቸውና “ወዲያ ሄጄ ስጸልይ ሳለ በዚህ ተቀመጡ” አላቸው። እነዚህን ሐዋርያት የተዋቸው በአትክልት ሥፍራው መግቢያ ላይ ሳይሆን አይቀርም። ከዚያም ሌሎቹን ሦስቱን ሐዋርያት ማለትም ጴጥሮስን፣ ያዕቆብንና ዮሐንስን ይዞ ወደ አትክልት ሥፍራው ውስጥ ገባ። ኢየሱስ እጅግ አዘነ፤ መንፈሱም በጣም ተረበሸ። “ነፍሴ እስከ ሞት ድረስ እጅግ አዘነች፤” አላቸው። “በዚህ ቆዩ ከእኔም ጋር ትጉ [“ነቅታችሁ ጠብቁ፣” NW]።”

ኢየሱስ ጥቂት ወደ ፊት እልፍ ብሎ መሬት ላይ በግንባሩ ተደፋና እንዲህ ሲል አጥብቆ መጸለይ ጀመረ:- “አባቴ፣ ቢቻልስ፣ ይህች ጽዋ ከእኔ ትለፍ፤ ነገር ግን አንተ እንደምትወድ ይሁን እንጂ እኔ እንደምወድ አይሁን።” ምን ማለቱ ነበር? ‘እስከ ሞት ድረስ እጅግ ያዘነው’ ለምንድን ነው? ለመሞትና ቤዛውን ለማቅረብ ከወሰደው ውሳኔ እያፈገፈገ ነበርን?

በፍጹም! ኢየሱስ ከሞት ለመትረፍ እንዲችል መማጸኑ አልነበረም። አንድ ጊዜ ጴጥሮስ አቅርቦለት የነበረውን መሥዋዕታዊውን ሞት የማስቀረቱን ሐሳብ እንኳ ጭራሽ ወደ አእምሮው ሊያመጣው አይፈልግም። ከዚህ ይልቅ በጭንቀት እየተሠቃየ ያለው ከጥቂት ጊዜ በኋላ የተናቀ ወንጀለኛ እንደሆነ ተቆጥሮ የሚሞትበት መንገድ በአባቱ ስም ላይ የሚያመጣው ነቀፋ በጣም ስላሳሰበው ነው። ከጥቂት ሰዓታት በኋላ አምላክን የሰደበ ከሁሉም የከፋ መጥፎ ሰው እንደሆነ ተቆጥሮ በእንጨት ላይ እንደሚሰቀል ተገንዝቧል! መንፈሱን በጣም የረበሸው ነገር ይህ ነው።

ኢየሱስ ረዘም ላለ ጊዜ ሲጸልይ ከቆየ በኋላ ሲመለስ ሦስቱ ሐዋርያት ተኝተው አገኛቸው። ጴጥሮስን “ከእኔ ጋር አንዲት ሰዓት ስንኳ ልትተጉ አልቻላችሁምን? ወደ ፈተና እንዳትገቡ ትጉና ጸልዩ [“ነቅታችሁ በመጠበቅ ያለ ማቋረጥ ጸልዩ፣” NW]” አለው። ይሁን እንጂ ያደረባቸውን ጭንቀትና የሌሊቱን ሰዓት መግፋት ግምት ውስጥ በማስገባት “መንፈስ ተዘጋጅታለች ሥጋ ግን ደካማ ነው” አለ።

ከዚያም ኢየሱስ ለሁለተኛ ጊዜ እልፍ ብሎ ሄደና ‘ጽዋውን’ ማለትም ይሖዋ የመደበለትን ዕጣ ወይም ለእሱ ያለውን ፈቃድ እንዲያስቀርለት ለመነው። ሲመለስ አሁንም ሦስቱ ሐዋርያት ወደ ፈተና እንዳይገቡ መጸለይ ሲገባቸው ተኝተው አገኛቸው። ኢየሱስ ሲያናግራቸው ምን እንደሚመልሱለት ግራ ገባቸው።

በመጨረሻ ኢየሱስ ለሦስተኛ ጊዜ የድንጋይ ውርወራ ያህል ራቀና ተንበርክኮ “አባት ሆይ፣ ብትፈቅድ ይህችን ጽዋ ከእኔ ውሰድ” በማለት ከብርቱ ጩኸትና ከእንባ ጋር ጸለየ። ኢየሱስ እጅግ ከባድ የሆነ ጭንቀት እንዲሰማው ያደረገው እንደ ወንጀለኛ ተቆጥሮ የሚሞት መሆኑ በአባቱ ስም ላይ የሚያመጣው ነቀፋ ነው። አምላክን የተሳደበና ያቃለለ ነው ተብሎ መወንጀል በጣም ከባድ ነው!

ሆኖም ኢየሱስ በመቀጠል “የእኔ ፈቃድ አይሁን የአንተ እንጂ” ሲል ጸለየ። ኢየሱስ በታዛዥነት የራሱን ፍላጎት ለአባቱ ፈቃድ አስገዝቷል። በዚህ ጊዜ አንድ መልአክ ከሰማይ ታየና በሚያበረታቱ ቃላት አጠነከረው። መልአኩ ኢየሱስ በአባቱ ፊት ያለውን ሞገስ ሳይነግረው አይቀርም።

ሆኖም በኢየሱስ ጫንቃ ላይ እጅግ ታላቅ የሆነ ኃላፊነት ወድቋል! የእሱም ሆነ የመላው የሰው ዘር የዘላለም ሕይወት በእሱ ላይ የተመካ ነው። ይህ ነው የማይባል የስሜት ውጥረት ይዞታል። ስለዚህ ኢየሱስ ከበፊቱ ይበልጥ አጥብቆ መጸለዩን ቀጠለ፤ ላቡም እንደ ደም ሆኖ ወደ መሬት ይንጠባጠብ ነበር። ዘ ጆርናል ኦቭ ዚ አሜሪካን ሜዲካል አሶሲየሽን “ይህ ሁኔታ ብዙ ጊዜ የማያጋጥም ቢሆንም እንኳ . . . ከፍተኛ የስሜት ውጥረት በሚኖርበት ጊዜ ደም የተቀላቀለበት ላብ ሊወጣ ይችላል” ሲል ገልጿል።

ከዚያ በኋላ ኢየሱስ ለሦስተኛ ጊዜ ወደ ሐዋርያቱ ሲመለስ እንደገና ተኝተው አገኛቸው። የተሰማቸው ጥልቅ ሐዘን በጣም አድክሟቸው ነበር። “አሁንም ገና ተኝታችኋልን? አሁንም ዕረፍት ታደርጋላችሁን?” ሲል በመደነቅ ጠየቃቸው። “እነሆ፣ ሰዓቱ ደርሶአል፤ የሰው ልጅ በኃጢአተኞች እጅ ተላልፎ ይሰጣል፤ ተነሡ እንሂድ፤ እነሆ አሳልፎ የሚሰጠኝ ቀርቦአል።”​— የ1980 ትርጉም

ኢየሱስ ገና እየተናገረ ሳለ የአስቆሮቱ ይሁዳ ችቦ፣ ፋኖስና መሣሪያዎች ከያዙ ብዙ ሕዝብ ጋር ሆኖ መጣ። ማቴዎስ 26:​30, 36-47፤ 16:​21-23፤ ማርቆስ 14:​26, 32-43፤ ሉቃስ 22:​39-47፤ ዮሐንስ 18:​1-3፤ ዕብራውያን 5:​7

▪ ደርብ ላይ ከሚገኘው ክፍል ከወጡ በኋላ ኢየሱስ ሐዋርያቱን ወዴት ወሰዳቸው? እዚያስ ምን አደረገ?

▪ ኢየሱስ እየጸለየ ሳለ ሐዋርያቱ ምን እያደረጉ ነበር?

▪ ኢየሱስ በጭንቀት ሲሠቃይ የነበረው ለምንድን ነው? ለአምላክ ያቀረበው ልመናስ ምንድን ነው?

▪ የኢየሱስ ላብ እንደ ደም ነጠብጣብ ሆኖ መውረዱ ምን ያመለክታል?