በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

በእርግጥ ኢየሱስ ማን ነው?

በእርግጥ ኢየሱስ ማን ነው?

ምዕራፍ 59

በእርግጥ ኢየሱስ ማን ነው?

ኢየሱስና ደቀ መዛሙርቱ ተሳፍረውባት የነበረችው ጀልባ ቤተ ሳይዳ ስትደርስ ሕዝቡ አንድ ዓይነ ስውር ወደ ኢየሱስ አመጡና እንዲዳስሰውና እንዲፈውሰው ለመኑት። ኢየሱስ እጁን ይዞ ከመንደሩ አወጣውና ዓይኖቹ ላይ ተፋበት፤ ከዚያም “አንዳች ታያለህን?” ሲል ጠየቀው።

ሰውየውም “ሰዎች እንደ ዛፍ ሲመላለሱ አያለሁ” ሲል መለሰለት። ኢየሱስ እጆቹን በሰውየው ዓይኖች ላይ ጫነና አጥርቶ መመልከት እንዲችል የማየት ችሎታውን መለሰለት። ኢየሱስ ሰውየውን ወደ ከተማ እንዳይገባ አዝዞ ወደ ቤት ሰደደው።

ከዚህ በኋላ ኢየሱስ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ሆኖ በፍልስጤም ምድር ሰሜናዊ ጫፍ ወደሚገኙት የፊልጶስ ቂሣርያ መንደሮች ሄደ። ከባሕር ወለል በላይ ወደ 350 ሜትር የሚጠጋ ከፍታ ላይ ወደሚገኘው የፊልጶስ ቂሣርያ ውብ አካባቢ ለመውጣት ወደ 50 ኪሎ ሜትር የሚጠጋ ረጅም ጉዞ ማድረግ ነበረባቸው። ጉዞው ሁለት ቀን ሳይወስድ አይቀርም።

በመንገድ ላይ ሳሉ ኢየሱስ ለመጸለይ ብቻውን ሄደ። ኢየሱስ ሊሞት የቀረው ጊዜ ዘጠኝ ወይም አሥር ወር ገደማ ቢሆን ነው፤ ስለዚህ የደቀ መዛሙርቱ ነገር አሳስቦታል። ብዙዎቹ እሱን መከተል አቁመዋል። ሌሎቹ ደግሞ ሕዝቡ እሱን ለማንገሥ ያደረጉትን ጥረት ባለመቀበሉና ጠላቶቹ ንግሥናውን የሚያረጋግጥ ምልክት ከሰማይ እንዲያሳያቸው በመጠየቅ በተፈታተኑት ጊዜ ምልክት ባለማሳየቱ ግራ የተጋቡና እነሱ እንዳሰቡት ሆኖ ባለመገኘቱ ቅር የተሰኙ ይመስላል። ሐዋርያቱስ ስለ እሱ ማንነት ያላቸው እምነት ምንድን ነው? ኢየሱስ እየጸለየ ወደነበረበት ቦታ ሲመጡ “ሕዝቡ እኔ ማን እንደ ሆንሁ ይላሉ? ብሎ ጠየቃቸው።”

“አንዳንዱ መጥምቁ ዮሐንስ፣ ሌሎችም ኤልያስ፣ ሌሎችም ኤርምያስ ወይም ከነቢያት አንዱ ነው ይላሉ” ብለው መለሱለት። አዎን፣ ሕዝቡ ከእነዚህ ሰዎች አንዱ ትንሣኤ አግኝቶ ኢየሱስ ተብሎ እንደተጠራ አድርገው ያስቡ ነበር!

ኢየሱስ “እናንተስ እኔን ማን እንደ ሆንሁ ትላላችሁ?” ሲል ጠየቃቸው።

ወዲያውኑ ጴጥሮስ “አንተ ክርስቶስ የሕያው እግዚአብሔር ልጅ ነህ” ሲል መለሰ።

ኢየሱስ በጴጥሮስ መልስ መስማማቱን ከገለጸ በኋላ እንዲህ አለ:- “እኔም እልሃለሁ፣ አንተ ጴጥሮስ ነህ፣ በዚህችም ዓለት ላይ ቤተ ክርስቲያኔን እሠራለሁ፣ የገሃነም [“የሔድስ፣” NW] ደጆችም አይችሉአትም።” እዚህ ላይ ኢየሱስ በመጀመሪያ ጉባኤ እንደሚገነባና የዚህ ጉባኤ አባላት ምድራዊ ጉዞአቸውን በታማኝነት ከጨረሱ በኋላ ሞትም እንኳ ሊይዛቸው እንደማይችል ገልጿል። ከዚያም ጴጥሮስን “የመንግሥተ ሰማያትንም መክፈቻዎች እሰጥሃለሁ” አለው።

ኢየሱስ በዚህ መንገድ ጴጥሮስ ልዩ መብቶች እንደሚያገኝ ገልጿል። ሆኖም ጴጥሮስ በሐዋርያት መካከል ዋነኛ ቦታ ይሰጠዋል፤ ወይም ደግሞ የጉባኤው መሠረት ይሆናል ማለት አይደለም። ጉባኤው የሚገነባበት ዓለት ኢየሱስ ራሱ ነው። ሆኖም ጴጥሮስ የተለያዩ የሰዎች ቡድኖች ወደ መንግሥተ ሰማያት መግባት የሚችሉበትን አጋጣሚ የሚከፍትባቸው ሦስት ቁልፎች ይሰጡታል።

ጴጥሮስ የመጀመሪያውን ቁልፍ ንስሐ የገቡ አይሁዶች ለመዳን ምን ማድረግ እንዳለባቸው ለማመልከት በ33 እንደ ዘመናችን አቆጣጠር ተጠቅሞበታል። ሁለተኛውን ደግሞ ከዚያ በኋላ ብዙም ሳይቆይ ያመኑ ሳምራውያን ወደ አምላክ መንግሥት መግባት የሚችሉበትን አጋጣሚ ለመክፈት ተጠቅሞበታል። ከዚያም ሦስተኛውን ቁልፍ በ36 እንደ ዘመናችን አቆጣጠር ይህንኑ አጋጣሚ ላልተገረዙት አሕዛብ ማለትም ለቆርኔሌዎስና ለጓደኞቹ ለመክፈት ተጠቅሞበታል።

ኢየሱስ ከሐዋርያቱ ጋር የሚያደርገውን ውይይት ቀጠለ። በቅርቡ በኢየሩሳሌም መከራ እንደሚቀበልና እንደሚሞት ሲነግራቸው ያልጠበቁት ነገር በመሆኑ አዘኑ። ጴጥሮስ፣ ኢየሱስ ከሞት ተነሥቶ ሰማያዊ ሕይወት እንደሚያገኝ ባለመረዳቱ ኢየሱስን ወደ እሱ ወሰደውና “አይሁንብህ ጌታ ሆይ፤ ይህ ከቶ አይደርስብህም” አለው። ኢየሱስ ጀርባውን አዙሮ “ወደ ኋላዬ ሂድ፣ አንተ ሰይጣን፤ የሰውን እንጂ የእግዚአብሔርን አታስብምና ዕንቅፋት ሆነህብኛል” አለው።

ከሐዋርያቱ በተጨማሪ ሌሎችም ከኢየሱስ ጋር አብረው እንደተጓዙ ከሁኔታው መረዳት ይቻላል። ስለዚህ ወደ እርሱ ጠራቸውና የእሱ ተከታይ መሆን ቀላል እንዳልሆነ ገለጸላቸው። “በኋላዬ ሊመጣ የሚወድ ቢኖር፣ ራሱን ይካድ መስቀሉንም [“የመከራውንም እንጨት፣” NW] ተሸክሞ [“ያለማቋረጥ፣” NW] ይከተለኝ። ነፍሱን ሊያድን የሚወድ ሁሉ ያጠፋታልና፤ ስለ እኔና ስለ ወንጌል ነፍሱን የሚያጠፋ ሁሉ ግን ያድናታል” አላቸው።

አዎን፣ የኢየሱስ ተከታዮች የእሱን ሞገስ ለማግኘት ከፈለጉ ደፋሮችና የራሳቸውን ጥቅም የሚሰዉ መሆን አለባቸው። “በዚህም በዘማዊና በኃጢአተኛ ትውልድ መካከል በእኔና በቃሌ የሚያፍር ሁሉ፣ የሰው ልጅ ደግሞ በአባቱ ክብር ከቅዱሳን መላእክት ጋር በመጣ ጊዜ በእርሱ ያፍርበታል” አላ⁠ቸው። ማርቆስ 8:​22-38፤ ማቴዎስ 16:​13-28፤ ሉቃስ 9:​18-27

▪ ኢየሱስ የደቀ መዛሙርቱ ነገር ያሳሰበው ለምንድን ነው?

▪ የኢየሱስን ማንነት በተመለከተ ሰዎች ምን አመለካከቶች ነበሯቸው?

▪ ለጴጥሮስ የተሰጡት ቁልፎች ምንድን ናቸው? ጥቅም ላይ የሚውሉትስ እንዴት ነው?

▪ ጴጥሮስ ምን እርማት ተሰጠው? ለምንስ?