በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

በእንጨት ላይ ተሰቅሎ ያሳለፈው ሥቃይ

በእንጨት ላይ ተሰቅሎ ያሳለፈው ሥቃይ

ምዕራፍ 125

በእንጨት ላይ ተሰቅሎ ያሳለፈው ሥቃይ

ከኢየሱስ ጋር የሚሰቀሉ ሁለት ዘራፊዎች አብረውት ተወስደው ነበር። ከከተማው ብዙም ሳይርቁ ጎልጎታ ወይም የራስ ቅል ስፍራ ተብሎ ወደሚጠራው ቦታ ሲደርሱ ጉዞው አበቃ።

እስረኞቹ ልብሳቸውን እንዲያወልቁ ተደረገ። ከዚያም ከርቤ የተቀላቀለበት ወይን ጠጅ አቀረቡላቸው። መጠጡ የተዘጋጀው በኢየሩሳሌም ሴቶች ሳይሆን አይቀርም፤ ሮማውያን ይህ የሚያደነዝዝ መድኃኒት ለሚሰቀሉት ሰዎች እንዲሰጥ ይፈቅዱ ነበር። ይሁን እንጂ ኢየሱስ ከቀመሰው በኋላ አልጠጣም አለ። አልጠጣም ያለው ለምንድን ነው? እምነቱ በሚታይበት በዚህ ታላቅ ፈተና ወቅት አእምሮውን ለማደንዘዝ እንዳልፈለገ ግልጽ ነው።

አሁን ኢየሱስ እጆቹን ከራሱ በላይ ዘርግቶ በእንጨቱ ላይ ተጋደመ። ከዚያም ወታደሮቹ ትልልቅ ምስማሮች በእጆቹና በእግሮቹ ላይ ቸነከሩ። ምስማሮቹ ሥጋውንና ጅማቶቹን በስተው ሲገቡ በሥቃይ ይቃትት ነበር። እንጨቱ ቀጥ ብሎ እንዲቆም ሲደረግ የሰውነቱ ክብደት ምስማሮቹ በገቡባቸው ቁስሎች ላይ ስለሚያርፍ ሥቃዩ በጣም ይበረታል። ሆኖም ኢየሱስ በሮማ ወታደሮቹ ላይ አልዛተባቸውም፤ ከዚህ ይልቅ “አባት ሆይ፣ የሚያደርጉትን አያውቁምና ይቅር በላቸው” ሲል ጸለየላቸው።

ጲላጦስ “የአይሁድ ንጉሥ የናዝሬቱ ኢየሱስ” የሚል ጽሑፍ የተጻፈበት ምልክት በእንጨቱ ላይ እንዲለጠፍ አደረገ። ይህን ጽሑፍ የጻፈው ለኢየሱስ አክብሮት ስለነበረው ብቻ ሳይሆን የአይሁድ ካህናት በኢየሱስ ላይ የሞት ፍርድ እንዲፈርድ በእሱ ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ በማሳደራቸው በእነርሱ ላይ ባደረበት ጥላቻ ጭምር ይመስላል። ጲላጦስ ሰዎች ሁሉ ሊያነቡት እንዲችሉ በሦስት ቋንቋዎች ማለትም በዕብራይስጥ፣ በኦፊሴላዊው የላቲን ቋንቋና ቀለል ባለ ግሪክኛ እንዲጻፍ አደረገ።

ቀያፋንና ሐናን ጨምሮ የካህናት አለቆቹ ተበሳጩ። ይህ አዎንታዊ ማስታወቂያ በተቀዳጁት ድል ያገኙትን ደስታ አጨለመባቸው። ስለዚህ “እርሱ:- የአይሁድ ንጉሥ ነኝ እንዳለ እንጂ የአይሁድ ንጉሥ ብለህ አትጻፍ” ብለው ተቃወሙት። ጲላጦስ ካህናቱ እሱን መሣሪያ አድርገው መጠቀማቸው አናዶት ስለነበር “የጻፍሁትን ጽፌአለሁ” በማለት በንቀት የማያዳግም መልስ ሰጣቸው።

አሁን ካህናቱ ከብዙ ሕዝብ ጋር ሆነው የሞት ፍርዱ በሚፈጸምበት ቦታ ተሰበሰቡ፤ ከዚያም ካህናቱ ማስታወቂያው ላይ የተጻፈውን ቃል ማስተባበል ጀመሩ። ቀደም ሲል በሳንሄድሪን ፊት በተካሄዱት ችሎቶች ላይ ቀርቦ የነበረውን የሐሰት ምሥክርነት ደግመው ተናገሩ። ስለዚህ በዚያ የሚያልፉ ሰዎች በፌዝ መልክ ራሳቸውን እየነቀነቁ “ቤተ መቅደስን የምታፈርስ በሦስት ቀንም የምትሠራው፣ ራስህን አድን፤ የእግዚአብሔር ልጅስ ከሆንህ ከመስቀል [“ከመከራው እንጨት፣” NW] ውረድ” በማለት መሳደብ መጀመራቸው አያስደንቅም።

የካህናት አለቆቹና ሃይማኖታዊ ግብረ አበሮቻቸውም በመቀጠል እንዲህ አሉ:- “ሌሎችን አዳነ፣ ራሱን ሊያድን አይችልም፤ የእስራኤል ንጉሥ ከሆነ፣ አሁን ከመስቀል [“ከመከራው እንጨት፣” NW] ይውረድ እኛም እናምንበታለን። በእግዚአብሔር ታምኖአል፤ የእግዚአብሔር ልጅ ነኝ ብሎአልና ከወደደውስ አሁን ያድነው።”

ወታደሮቹም እነርሱን ተከትለው በኢየሱስ መቀለድ ጀመሩ። ሆምጣጤ አመጡና የደረቁት ከንፈሮቹ ላይ አስጠግተው በመያዝ ሳይሆን አይቀርም፣ አሾፉበት። “አንተስ የአይሁድ ንጉሥ ከሆንህ፣ ራስህን አድን” እያሉ ዘበቱበት። በኢየሱስ ቀኝና ግራ የተሰቀሉት ዘራፊዎች እንኳን ሳይቀሩ አሾፉበት። እስቲ አስበው! እስከ ዛሬ ከኖሩት ሁሉ የሚበልጠው ታላቅ ሰው፣ አዎን፣ ከይሖዋ አምላክ ጋር ሆኖ ሁሉንም ነገሮች የፈጠረው ይህ ሰው ይህን ሁሉ ኢሰብዓዊ ድርጊት በጽናት ተቋቁሟል!

ወታደሮቹ ኢየሱስ ከላይ ይደርበው የነበረውን ልብስ ወስደው አራት ቦታ ከፋፈሉት። ከዚያም ልብሱን ለመከፋፈል ዕጣ ተጣጣሉ። እጀ ጠባቡ ግን ስፌት የሌለው ከላይ ጀምሮ ወጥ የሆነ ከፍተኛ ጥራት ያለው ልብስ ነበር። ስለዚህ ወታደሮቹ “ለማን እንዲሆን በእርሱ ዕጣ እንጣጣልበት እንጂ አንቅደደው” ተባባሉ። በዚህ መንገድ ሳያውቁት “ልብሴን እርስ በርሳቸው ተከፋፈሉ በእጀ ጠባቤም ዕጣ ተጣጣሉበት” የሚለው ጥቅስ እንዲፈጸም አድርገዋል።

ከጊዜ በኋላ ከዘራፊዎቹ አንዱ ኢየሱስ በእርግጥም ንጉሥ እንደሆነ ተገነዘበ። ስለዚህ ጓደኛውን እንዲህ ሲል ገሠጸው:- “አንተ እንደዚህ ባለ ፍርድ ሳለህ እግዚአብሔርን ከቶ አትፈራውምን? ስለ አደረግነውም የሚገባንን እንቀበላለንና በእኛስ እውነተኛ ፍርድ ነው፤ ይህ ግን ምንም ክፋት አላደረገም።” ከዚያም ኢየሱስን “በመንግሥትህ በመጣህ ጊዜ አስበኝ” ሲል ለመነው።

ኢየሱስ “እውነት እልሃለሁ ዛሬ፣ ከእኔ ጋር በገነት ትሆናለህ” ሲል መለሰለት። (NW) ኢየሱስ በሰማይ ንጉሥ ሆኖ በሚገዛበት ጊዜ ከአርማጌዶን የተረፉት ሰዎችና ጓደኞቻቸው በሚያለሟት ገነት በምትሆነው ምድር ላይ እንዲኖር ይህን ንስሐ የገባ ክፉ አድራጊ ከሞት ሲያስነሳው ይህ ተስፋ ፍጻሜውን ያገኛል። ማቴዎስ 27:​33-44፤ ማርቆስ 15:​22-32፤ ሉቃስ 23:​27, 32-43፤ ዮሐንስ 19:​17-24

▪ ኢየሱስ ከርቤ የተቀላቀለበትን ወይን ጠጅ መጠጣት ያልፈለገው ለምንድን ነው?

▪ ኢየሱስ በተሰቀለበት እንጨት ላይ ማስታወቂያ የተለጠፈው ለምን ሳይሆን አይቀርም? ይህስ በጲላጦስና በካህናት አለቆቹ መካከል ምን የሐሳብ ልውውጥ እንዲደረግ ምክንያት ሆኗል?

▪ ኢየሱስ በእንጨቱ ላይ ተሰቅሎ እያለ ምን ተጨማሪ በደል ተፈጽሞበታል? ከሁኔታው ለመረዳት እንደሚቻለው ለዚህ ምክንያት የሆነውስ ነገር ምንድን ነው?

▪ በኢየሱስ ልብሶች ላይ በተፈጸመው ነገር አንድ ትንቢት ፍጻሜውን ያገኘው እንዴት ነው?

▪ ከሌቦቹ አንዱ ምን ለውጥ አደረገ? ኢየሱስ ጥያቄውን የሚያሟላለትስ እንዴት ነው?