በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

በወይን አትክልት ምሳሌዎች ተጋለጡ

በወይን አትክልት ምሳሌዎች ተጋለጡ

ምዕራፍ 106

በወይን አትክልት ምሳሌዎች ተጋለጡ

ኢየሱስ ያለው ቤተ መቅደሱ ውስጥ ነው። የፈጸማቸውን ነገሮች ያከናወነው በማን ሥልጣን እንደሆነ የጠየቁትን የሃይማኖት መሪዎች ግራ ያጋባቸው ከጥቂት ጊዜ በፊት ነበር። ግራ በተጋቡበት ሁኔታ ውስጥ እንዳሉ ኢየሱስ “ምን ይመስላችኋል?” ሲል ጠየቃቸው። ከዚያም አንድ ምሳሌ በመጠቀም ምን ዓይነት ሰዎች እንደሆኑ አመለከታቸው።

“አንድ ሰው ሁለት ልጆች ነበሩት፤” በማለት ኢየሱስ ታሪኩን መናገር ጀመረ። “ወደ አንደኛው ቀርቦ:- ልጄ ሆይ፣ ዛሬ ሂድና በወይኔ አትክልት ሥራ አለው። እርሱም መልሶ:- አልወድም አለ፤ ኋላ ግን ተጸጸተና ሄደ። ወደ ሁለተኛውም ቀርቦ እንዲሁ አለው እርሱም መልሶ:- እሺ ጌታዬ አለ፤ ነገር ግን አልሄደም። ከሁለቱ የአባቱን ፈቃድ ያደረገ ማን ነው?” በማለት ኢየሱስ ጠየቃቸው።

ተቃዋሚዎቹ “ፊተኛው” ብለው መለሱለት።

ስለዚህ ኢየሱስ እንዲህ ሲል ገለጸ:- “እውነት እላችኋለሁ፣ ቀራጮችና ጋለሞቶች ወደ እግዚአብሔር መንግሥት በመግባት ይቀድሙአችኋል።” ቀራጮቹና ጋለሞቶቹ በመጀመሪያ አምላክን ለማገልገል ፈቃደኞች እንዳልሆኑ ያህል ነበር። በኋላ ግን እንደ መጀመሪያው ልጅ ተጸጸቱና አገለገሉት። በሌላ በኩል ግን የሃይማኖት መሪዎቹ እንደ ሁለተኛው ልጅ አምላክን እናገለግላለን ብለው ነበር፤ ሆኖም ኢየሱስ እንዲህ ብሏል:- “[አጥማቂው] ዮሐንስ በጽድቅ መንገድ መጥቶላችሁ ነበርና፣ አላመናችሁበትም፤ ቀራጮችና ጋለሞቶች ግን አመኑበት፤ እናንተም ይህን አይታችሁ ታምኑበት ዘንድ በኋላ ንስሐ አልገባችሁም።”

ኢየሱስ በመቀጠል የእነዚህ ሃይማኖታዊ መሪዎች ጉድለት አምላክን አለማገልገላቸው ብቻ እንዳልሆነ አመልክቷል። መጥፎዎችና ክፉዎችም ነበሩ። “የወይን አትክልት የተከለ ባለቤት ሰው ነበረ” ሲል ኢየሱስ ተናገረ፤ “ቅጥርም ቀጠረለት፣ መጥመቂያም ማሰለት፣ ግንብም ሠራና ለገበሬዎች አከራይቶ ወደ ሌላ አገር ሄደ። የሚያፈራበትም ጊዜ ሲቀርብ፣ ፍሬውን ሊቀበሉ ባሮቹን ወደ ገበሬዎች ላከ። ገበሬዎቹም ባሮቹን ይዘው አንዱን ደበደቡት አንዱንም ገደሉት ሌላውንም ወገሩት። ደግሞ ከፊተኞች የሚበዙ ሌሎች ባሮችን ላከ፣ እንዲሁም አደረጉባቸው።”

“ባሮቹ” “ባለቤት” የሆነው ይሖዋ አምላክ ‘በወይን አትክልቱ ቦታ’ ወደሚሠሩት “ገበሬዎች” የላካቸው ነቢያት ናቸው። እነዚህ ገበሬዎች መጽሐፍ ቅዱስ የአምላክ “የወይን አትክልት” እንደሆነ አድርጎ የሚገልጸው የእስራኤል ሕዝብ ዋና ወኪሎች ናቸው።

“ገበሬዎቹ” “ባሮቹን” ስላሠቃዩአቸውና ስለገደሏቸው ኢየሱስ እንዲህ ሲል ገለጸ:- “በኋላ ግን:- [የወይን አትክልቱ ባለቤት] ልጄንስ ያፍሩታል ብሎ ልጁን ላከባቸው። ገበሬዎቹ ግን ልጁን ባዩ ጊዜ እርስ በርሳቸው:- ወራሹ ይህ ነው፤ ኑ፣ እንግደለውና ርስቱን እናግኝ ተባባሉ። ይዘውም ከወይኑ አትክልት አወጡና ገደሉት።”

አሁን ኢየሱስ “የወይኑ አትክልት ጌታ በሚመጣ ጊዜ በእነዚህ ገበሬዎች ምን ያደርግባቸዋል?” ሲል የሃይማኖት መሪዎቹን ጠየቃቸው።

የሃይማኖት መሪዎቹ እንዲህ ብለው መለሱ:- “ክፉዎችን በክፉ ያጠፋቸዋል፣ የወይኑንም አትክልት ፍሬውን በየጊዜው ለሚያስረክቡ ለሌሎች ገበሬዎች ይሰጠዋል።”

የሃይማኖት መሪዎቹ የይሖዋ “የወይን አትክልት” በሆነው በእስራኤል ብሔር ላይ ከሚሠሩት እስራኤላውያን “ገበሬዎች” መካከል የሚገኙ በመሆኑ ሳያውቁት በዚህ መንገድ በራሳቸው ላይ ፍርድ በይነዋል። ይሖዋ ከእነዚህ ገበሬዎች ይጠብቀው የነበረው ፍሬ እውነተኛ መሲሕ በሆነው ልጁ ማመንን ነበር። እንዲህ ዓይነት ፍሬ ባለማፍራታቸው ኢየሱስ እንዲህ ሲል አስጠነቀቃቸው:- “ግንበኞች የናቁት ድንጋይ፣ እርሱ የማዕዘን ራስ ሆነ፤ ይህም ከጌታ ዘንድ ሆነ፣ ለዓይኖቻችንም ድንቅ ነው የሚለውን ከቶ በመጽሐፍ [በመዝሙር 118:​22, 23 ላይ] አላነበባችሁምን? ስለዚህ እላችኋለሁ፣ የእግዚአብሔር መንግሥት ከእናንተ ትወሰዳለች ፍሬዋንም ለሚያደርግ ሕዝብ ትሰጣለች። በዚህም ድንጋይ ላይ የሚወ​ድቅ ይቀጠቀጣል፤ ድንጋዩ ግን የሚወድቅበትን ሁሉ ይፈጨዋል።”

በዚህ ጊዜ ጻፎቹና የካህናት አለቆቹ ኢየሱስ ስለ እነርሱ እየተናገረ እንዳለ ተገነዘቡና ሕጋዊ ‘ወራሽ’ የሆነውን ኢየሱስን ሊገድሉት ፈለጉ። ስለዚህ በብሔር ደረጃ በአምላክ መንግሥት ገዥዎች የመሆን መብታቸው ይወሰድባቸዋል። በምትኩ ተስማሚ የሆኑ ፍሬዎችን የሚያፈሩ ‘የወይን አትክልት ገበሬዎችን’ ያቀፈ አዲስ ብሔር ይፈጠራል።

ሕዝቡ ኢየሱስን ነቢይ አድርገው ይመለከቱት ነበር፤ ስለዚህ የሃይማኖት መሪዎቹ ሕዝቡን ስለፈሩ በዚህ ጊዜ ኢየሱስን ለመግደል አልሞከሩም። ማቴዎስ 21:​28-46፤ ማርቆስ 12:​1-12፤ ሉቃስ 20:​9-19፤ ኢሳይያስ 5:​1-7

▪ ኢየሱስ በተናገረው የመጀመሪያ ምሳሌ ላይ የተጠቀሱት ሁለት ልጆች እነማንን ያመለክታሉ?

▪ በሁለተኛው ምሳሌ ላይ የተጠቀሱት ‘ባለቤቱ፣’ ‘የወይኑ አትክልት፣’ “ገበሬዎቹ፣” “ባሮቹ” እና “ወራሹ” እነማንን ያመለክታሉ?

▪ ‘የወይኑ አትክልት ገበሬዎች’ ምን ይሆናሉ? እነርሱን የሚተኳቸውስ እነማን ናቸው?