በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

በይሁዳ ጠቋሚነት መያዝ

በይሁዳ ጠቋሚነት መያዝ

ምዕራፍ 118

በይሁዳ ጠቋሚነት መያዝ

ይሁዳ ወታደሮችን፣ የካህናት አለቆችን፣ ፈሪሳውያንንና ሌሎች ሰዎችን ያቀፈ ትልቅ ጭፍራ አስከትሎ ወደ ጌቴሴማኒ የአትክልት ሥፍራ ሲመጣ እኩለ ሌሊት አልፎ ነበር። ካህናቱ ኢየሱስን አሳልፎ ከሰጣቸው ለይሁዳ 30 ብር ለመስጠት ተስማምተዋል።

ቀደም ሲል ይሁዳ ከማለፍ በዓሉ እራት ላይ ተነሥቶ ሲወጣ በቀጥታ ወደ ካህናት አለቆቹ እንደሄደ ግልጽ ነው። እነርሱም ወዲያውኑ የራሳቸውን መኮንኖችና አንድ የወታደሮች ቡድን ሰበሰቡ። ይሁዳ መጀመሪያ የወሰዳቸው ኢየሱስና ሐዋርያቱ የማለፍ በዓልን ወዳከበሩበት ቤት ሳይሆን አይቀርም። ከዚያ እንደሄዱ ሲገነዘቡ መሣሪያ የታጠቁትና ፋኖስና ችቦ የያዙት ጭፍሮች ይሁዳን ተከትለው ከኢየሩሳሌም ወጡና የቄድሮንን ሸለቆ ተሻገሩ።

ይሁዳ ጭፍሮቹን እየመራ ወደ ደብረ ዘይት ተራራ ወሰዳቸው፤ ኢየሱስን የት እንደሚያገኘው እርግጠኛ ነበር። ባለፈው ሳምንት ኢየሱስና ሐዋርያቱ ወደ ቢታንያና ወደ ኢየሩሳሌም ሲመላለሱ ብዙውን ጊዜ አረፍ ብለው ለመወያየት ወደ ጌቴሴማኒ የአትክልት ሥፍራ ጎራ ይሉ ነበር። አሁን ግን ኢየሱስ ያለው በወይራ ዛፎች ሥር ጨለማ ውስጥ ሊሆን ስለሚችል ወታደሮቹ እንዴት ሊለዩት ይችላሉ? ከዚህ በፊት ጭራሽ አይተውት ላያውቁ ይችላሉ። ስለዚህ ይሁዳ “የምስመው እርሱ ነው፤ ያዙት ተጠንቅቃችሁም ውሰዱት” ብሎ ምልክት ሰጥቶአቸው ነበር።

ይሁዳ ጭፍሮቹን እየመራ ወደ አትክልት ሥፍራው ገባና ኢየሱስን ከሐዋርያቱ ጋር ሲመለከተው በቀጥታ ወደ እሱ ሄደ። “መምህር ሆይ፣ ሰላም ለአንተ ይሁን” ብሎ ሳም አደረገው።

ኢየሱስ “ወዳጄ ሆይ፣ ለምን ነገር መጣህ?” ሲል ጠየቀው። ከዚያም የራሱን ጥያቄ ራሱ በመመለስ “ይሁዳ ሆይ፣ በመሳም የሰውን ልጅ አሳልፈህ ትሰጣለህን?” አለው። ሆኖም ይሁዳ ተልዕኮውን ፈጽሞ ነበር! ኢየሱስ የችቦዎቹና የፋኖሶቹ መብራት ወዳለበት ቦታ ወጣ ብሎ “ማንን ትፈልጋላችሁ?” ሲል ጠየቃቸው።

“የናዝሬቱን ኢየሱስን” ሲሉ መለሱለት።

ኢየሱስ በሁሉም ፊት በድፍረት ቆሞ “እኔ ነኝ” አላቸው። ሰዎቹ በድፍረቱ ተደንቀውና ምን ሊያደርግ እንደሆነ ስላላወቁ ፈርተው ወደ ኋላ አፈገፈጉና ወደቁ።

ኢየሱስ “እኔ ነኝ አልኋችሁ” በማለት በተረጋጋ መንፈስ መናገሩን ቀጠለ። “እኔን ትፈልጉ እንደ ሆናችሁ እነዚህ ይሂዱ ተዉአቸው” አለ። ከጥቂት ጊዜ በፊት ደርብ ላይ በሚገኘው ክፍል ውስጥ እያሉ ኢየሱስ ታማኝ ሐዋርያቱን እንደጠበቃቸውና “ከጥፋት ልጅ በቀር” ከእነርሱ አንድም የጠፋ እንደሌለ ለአባቱ በጸሎት ገልጾለት ነበር። ስለዚህ ቃሉ መፈጸም ይችል ዘንድ ተከታዮቹ መሄድ እንዲፈቀድላቸው ጥያቄ አቀረበ።

ወታደሮቹ ድንጋጤያቸው ለቀቅ ሲያደርጋቸው ተነሱና ኢየሱስን ማሰር ጀመሩ፤ በዚህ ጊዜ ሐዋርያቱ ምን ሊፈጸም እንደሆነ ገባቸው። “ጌታ ሆይ፣ በሰይፍ እንምታቸውን?” ብለው ጠየቁት። ኢየሱስ መልስ ከመስጠቱ በፊት ጴጥሮስ ሐዋርያቱ ይዘዋቸው ከነበሩት ሁለት ሰይፎች መካከል አንደኛውን መዘዘና የሊቀ ካህናቱ ባሪያ የሆነውን ማልኮስን መታው። ጴጥሮስ የሰነዘረው ሰይፍ የባሪያውን ጭንቅላት ሳተና የቀኝ ጆሮውን ቆረጠው።

ኢየሱስ ጣልቃ ገባና “ይህንስ ፍቀዱ” አለ። የማልኮስን ጆሮ ዳሰሰና ቁስሉን ፈወሰው። ከዚያም ጴጥሮስን እንደሚከተለው ብሎ በማዘዝ አንድ ትልቅ ትምህርት ሰጠ:- “ሰይፍ የሚያነሡ ሁሉ በሰይፍ ይጠፋሉና ሰይፍህን ወደ ስፍራው መልስ። ወይስ አባቴን እንድለምን እርሱም አሁን ከአሥራ ሁለት ጭፍሮች የሚበዙ መላእክት እንዲሰድልኝ የማይቻል ይመስልሃልን?”

ኢየሱስ “እንደዚህ ሊሆን ይገባል የሚሉ መጻሕፍት እንዴት ይፈጸማሉ?” ሲል በመግለጽ ለመያዝ ፈቃደኛ መሆኑን አሳይቷል። አክሎም “አብ የሰጠኝን ጽዋ አልጠጣትምን?” ሲል ተናገረ። አምላክ ለእርሱ ካለው ፈቃድ ጋር ሙሉ በሙሉ ተስማምቶ ነበር!

ከዚያም ኢየሱስ ጭፍሮቹን አነጋገራቸው። “ወንበዴን እንደምትይዙ ሰይፍና ጐመድ ይዛችሁ ልትይዙኝ ወጣችሁን?” ሲል ጠየቃቸው። “በመቅደስ ዕለት ዕለት እያስተማርሁ ከእናንተ ጋር ስቀመጥ ሳለሁ አልያዛችሁኝም። ነገር ግን ይህ ሁሉ የሆነ የነቢያት መጻሕፍት ይፈጸሙ ዘንድ ነው።”

በዚህ ጊዜ ወታደሮቹ፣ የወታደሮቹ አዛዥና የአይሁድ መኮንኖች ኢየሱስን ያዙና አሰሩት። ሐዋርያቱ ይህን ሲመለከቱ ኢየሱስን ጥለው ሸሹ። ሆኖም አንድ ወጣት፣ ምናልባትም ደቀ መዝሙሩ ማርቆስ ሳይሆን አይቀርም፣ በጭፍሮቹ መካከል ቀረ። ቀደም ሲል ኢየሱስ የማለፍ በዓሉን ባከበረበት ቤት ውስጥ የነበረ ይመስላል። ከዚያም ጭፍሮቹን ተከትሎ መጥቶ ሊሆን ይችላል። ይሁን እንጂ አሁን ማንነቱን ሲያውቁ ሊይዙት ሞከሩ። ሆኖም ወጣቱ እንዲሁ አጣፍቶት የነበረውን በፍታ ጥሎ ሸሸ። ማቴዎስ 26:​47-56፤ ማርቆስ 14:​43-52፤ ሉቃስ 22:​47-53፤ ዮሐንስ 17:​12፤ 18:​3-12

▪ ይሁዳ ኢየሱስን በጌቴሴማኒ የአትክልት ሥፍራ እንደሚያገኘው እርግጠኛ የነበረው ለምንድን ነው?

▪ ኢየሱስ ለሐዋርያቱ ያለውን አሳቢነት የገለጸው እንዴት ነው?

▪ ጴጥሮስ ኢየሱስን ከጥቃት ለመጠበቅ ሲል ምን እርምጃ ወሰደ? ሆኖም ኢየሱስ ይህን ጉዳይ በተመለከተ ጴጥሮስን ምን አለው?

▪ ኢየሱስ፣ አምላክ ለእርሱ ካለው ፈቃድ ጋር ሙሉ በሙሉ እንደሚስማማ ያሳየው እንዴት ነው?

▪ ሐዋርያቱ ኢየሱስን ጥለው በሸሹ ጊዜ እዚያው ቀርቶ የነበረው ማን ነው? ምንስ ደረሰበት?