በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

በዳስ በዓል ላይ

በዳስ በዓል ላይ

ምዕራፍ 66

በዳስ በዓል ላይ

ኢየሱስ ከተጠመቀ በኋላ ባሳለፈው ወደ ሦስት ዓመት በሚጠጋ ጊዜ ውስጥ ዝነኛ ሆኗል። በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ሰዎች ተአምራቱን አይተዋል፤ ስላከናወናቸው ነገሮች የሚገልጽ ወሬም በመላው አገሪቱ ተሰራጭቷል። አሁን ሕዝቡ የዳስን በዓል ለማክበር በኢየሩሳሌም ሲሰበሰቡ ኢየሱስን መፈለግ ጀመሩ። “እርሱ ወዴት ነው?” እያሉ ይፈልጉት ነበር።

ኢየሱስ መከራከሪያ ርዕስ ሆኗል። አንዳንዶቹ “እርሱ ጥሩ ሰው ነው” ይላሉ። (የ1980 ትርጉም) ሌሎቹ ደግሞ “አይደለም፣ ሕዝቡን ግን ያስታል” ይላሉ። በበዓሉ መክፈቻ ቀናት ይህን የመሰለ ብዙ ሹክሹክታ ነበር። ሆኖም ኢየሱስን ደግፎ በግልጽ ለመናገር የደፈረ አልነበረም። ሕዝቡ ከአይሁድ መሪዎች የሚወሰድባቸውን አጸፋዊ እርምጃ ይፈሩ ስለነበር ይህን ለማድረግ አልደፈሩም።

በበዓሉ አጋማሽ ላይ ኢየሱስ መጣ። ወደ ቤተ መቅደሱ ሄዶ ሲያስተምር ሕዝቡ የማስተማር ችሎታው ከጠበቁት በላይ ስለሆነባቸው በጣም ተደነቁ። ኢየሱስ በረቢዎች ትምህርት ቤት ገብቶ ስላልተማረ አይሁዶች በጣም ተገርመው “ይህ ሰው ሳይማር መጻሕፍትን እንዴት ያውቃል?” አሉ።

ኢየሱስ እንዲህ ሲል ገለጸ:- “ትምህርቴስ ከላከኝ ነው እንጂ ከእኔ አይደለም፤ ፈቃዱን ሊያደርግ የሚወድ ቢኖር፣ እርሱ ይህ ትምህርት ከእግዚአብሔር ቢሆን ወይም እኔ ከራሴ የምናገር ቢሆን ያውቃል።” የኢየሱስ ትምህርት የአምላክን ሕግ በጥብቅ የተከተለ ነበር። ስለዚህ የራሱን ሳይሆን የአምላክን ክብር ይፈልግ እንደነበረ ግልጽ ሊሆንላቸው ይገባ ነበር። “ሙሴ ሕግን አልሰጣችሁምን?” ሲል ኢየሱስ ጠየቃቸው። “ከእናንተ ግን ሕግን የሚያደርግ አንድ ስንኳ የለም” በማለት ነቀፋቸው።

ከዚያም ኢየሱስ “ልትገድሉኝ ስለ ምን ትፈልጋላችሁ?” ሲል ጠየቃቸው።

በሕዝቡ መካከል ያሉ ሰዎች፣ ምናልባትም ለበዓሉ ከሌላ ቦታ የመጡት ሰዎች ሳይሆኑ አይቀሩም፣ ኢየሱስን ለመግደል የተደረጉትን ሴራዎች አያውቁም ነበር። ይህን የመሰለ ግሩም አስተማሪ ለመግደል የሚፈልግ ሰው ይኖራል ብሎ ማሰብ የማይመስል ነገር ሆነባቸው። ስለዚህ ኢየሱስ እንዲህ ብሎ ሊያስብ የቻለው አንድ ችግር ቢኖርበት ነው የሚል እምነት አደረባቸው። “ጋኔን አለብህ፤ ማን ሊገድልህ ይፈልጋል?” አሉት።

ምንም እንኳ ሕዝቡ ያልተገነዘቡት ሊሆን ቢችልም የአይሁድ መሪዎች ኢየሱስን ለመግደል ይፈልጉ ነበር። ኢየሱስ ከአንድ ዓመት ተኩል በፊት በሰንበት ቀን አንድ ሰው በፈወሰ ጊዜ መሪዎቹ ሊገድሉት ሞክረው ነበር። ስለዚህ ኢየሱስ እንደሚከተለው ብሎ በመጠየቅ ምክንያታዊ አለመሆናቸውን አመለከተ:- “የሙሴ ሕግ እንዳይሻር ሰው በሰንበት መገረዝን የሚቀበል ከሆነስ ሰውን ሁለንተናውን በሰንበት ጤናማ ስላደረግሁ ትቆጡኛላችሁን? ቅን ፍርድ ፍረዱ እንጂ በመልክ አትፍረዱ።”

በዚህ ጊዜ ሁኔታውን የሚያውቁ የኢየሩሳሌም ነዋሪዎች እንዲህ አሉ:- “ሊገድሉት የሚፈልጉት ይህ አይደለምን? እነሆም፣ በግልጥ ይናገራል አንዳችም አይሉትም። አለቆቹ ይህ ሰው በእውነት ክርስቶስ እንደ ሆነ በእውነት አወቁን?” እነዚህ የኢየሩሳሌም ነዋሪዎች ክርስቶስ ነው ብለው ያላመኑበት ለምን እንደሆነ እንዲህ ሲሉ ገለጹ:- “ይህን ከወዴት እንደ ሆነ አውቀናል፤ ክርስቶስ ሲመጣ ግን ከወዴት እንደ ሆነ ማንም አያውቅም።”

ኢየሱስ እንዲህ ሲል መለሰላቸው:- “እኔንም ታውቁኛላችሁ ከወዴትም እንደ ሆንሁ ታውቃላችሁ፤ እኔም በራሴ አልመጣሁም ነገር ግን እናንተ የማታውቁት የላከኝ እውነተኛ ነው፤ እኔ ግን ከእርሱ ዘንድ ነኝ እርሱም ልኮኛልና አውቀዋለሁ።” በዚህ ጊዜ ሊይዙት ሞከሩ፤ ይህን ያደረጉት ሊያስሩት ወይም ሊገድሉት ፈልገው ይሆናል። ሆኖም ኢየሱስ የሚሞትበት ጊዜ ስላልደረሰ ሊሳካላቸው አልቻለም።

ያም ሆኖ ግን ብዙዎች በኢየሱስ አምነው ነበር፤ ማመንም ይገባቸዋል። በውኃ ላይ ሄዷል፣ ነፋስን አቁሟል፣ በነፋስ የሚናወጥን ባሕር ጸጥ አሰኝቷል፣ በሺህ የሚቆጠሩ ሰዎችን በጥቂት እንጀራና ዓሣ በተአምር መግቧል፣ የታመሙትን ፈውሷል፣ ሽባዎች እንዲሄዱ አድርጓል፣ የዓይነ ስውሮችን ዓይን ገልጧል፣ የሥጋ ደዌ የያዛቸውን ፈውሷል፣ አልፎ ተርፎም የሞቱ ሰዎችን አስነስቷል። ታዲያ “ክርስቶስ በመጣ ጊዜ ይህ ካደረጋቸው ምልክቶች ይልቅ ያደርጋልን?” ብለው ሊጠይቁ ችለዋል።

ፈሪሳውያን ሕዝቡ እንዲህ እያሉ ሲንሾካሾኩ በሰሙ ጊዜ እነርሱና የካህናት አለቆች ኢየሱስን ለመያዝ መኮንኖችን ላኩ። ዮሐንስ 7:​11-32

▪ ኢየሱስ ወደ በዓሉ የደረሰው መቼ ነው? ሕዝቡ ስለ እርሱ ምን እያሉ ነበር?

▪ አንዳንዶች ኢየሱስ ጋኔን አለበት ያሉት ለምን ሊሆን ይችላል?

▪ የኢየሩሳሌም ነዋሪዎች ስለ ኢየሱስ ምን አመለካከት ነበራቸው?

▪ ብዙዎች በኢየሱስ ያመኑት ለምን ነበር?