በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

በገሊላ ባሕር

በገሊላ ባሕር

ምዕራፍ 130

በገሊላ ባሕር

አሁን ሐዋርያቱ ኢየሱስ አስቀድሞ ባዘዛቸው መሠረት ወደ ገሊላ ተመልሰዋል። ሆኖም እዚያ ምን ማድረግ እንዳለባቸው አላወቁም ነበር። ከጥቂት ጊዜ በኋላ ጴጥሮስ ቶማስን፣ ናትናኤልን፣ ያዕቆብንና ወንድሙን ዮሐንስን እንዲሁም ሌሎች ሁለት ሐዋርያትን “ዓሣ ላጠምድ እሄዳለሁ” አላቸው።

ስድስቱም “እኛም ከአንተ ጋር እንመጣለን” አሉት።

ሌሊቱን ሙሉ ምንም ዓሣ ማጥመድ አልቻሉም። ይሁን እንጂ ጎሕ ሲቀድ ኢየሱስ በባሕሩ ዳርቻ ተገለጠ፤ ሐዋርያቱ ግን ኢየሱስ መሆኑን አላወቁም ነበር። ኢየሱስ “ልጆች ሆይ፣ አንዳች የሚበላ አላችሁን?” ሲል ጮክ ብሎ ጠየቃቸው።

እነርሱም ከውኃው ባሻገር ሆነው “የለንም” ሲሉ ጮክ ብለው መለሱለት።

“መረቡን በታንኳይቱ በስተ ቀኝ ጣሉት ታገኙማላችሁ” አላቸው። እንዳላቸው ሲያደርጉ ከዓሣው ብዛት የተነሣ መረቡን መጎተት አቃታቸው።

ዮሐንስ “ጌታ እኮ ነው” ብሎ ጮኸ።

ጴጥሮስ ይህን ሲሰማ አውልቆት የነበረውን ልብስ ታጥቆ ባሕሩ ውስጥ ዘሎ ገባ። ከዚያም ዘጠና ሜትር ያህል ዋኝቶ ወደ ባሕሩ ዳርቻ መጣ። ሌሎቹ ሐዋርያት በትንሿ ጀልባ ላይ ሆነው በዓሣ የሞላውን መረብ እየጎተቱት ተከትለውት መጡ።

ወደ ባሕሩ ዳርቻ ሲደርሱ ዓሣ በላዩ የተቀመጠበት የከሰል ፍምና ዳቦ አዩ። ኢየሱስ “አሁን ካጠመዳችሁት ዓሣ አምጡ” አላቸው። ጴጥሮስ ወደ ጀልባዋ ገብቶ መረቡን ወደ ባሕሩ ዳርቻ ጎተተው። መረቡ 153 ትልልቅ ዓሦች ይዞ ነበር!

ኢየሱስ “ኑ፣ ቁርሳችሁን ብሉ” ሲል ጋበዛቸው።​— NW

ሁሉም ኢየሱስ መሆኑን አውቀው ስለነበረ ከመካከላቸው “አንተ ማን ነህ?” ብሎ ለመጠየቅ የደፈረ አልነበረም። ከሞት ከተነሣ በኋላ ሲገለጥ ይህ ሰባተኛ ጊዜው ነበር፤ በቡድን ደረጃ ለሐዋርያቱ ሲገለጥ ደግሞ ሦስተኛ ጊዜው ነበር። አሁን ለእያንዳንዳቸው ጥቂት ዳቦና ዓሣ በመስጠት ቁርሳቸውን አበላቸው።

በልተው ሲጨርሱ ኢየሱስ ወደተጠመደው ብዙ ዓሣ እየተመለከተ ሳይሆን አይቀርም፣ ጴጥሮስን “የዮና ልጅ ስምዖን ሆይ፣ ከእነዚህ ይልቅ ትወደኛለህን?” ሲል ጠየቀው። ዓሣ የማጥመድ ሥራህን እኔ እንድትሠራው ካዘጋጀሁህ ሥራ ይበልጥ ትወደዋለህን? ብሎ መጠየቁ እንደነበረ ጥርጥር የለውም።

ጴጥሮስ “ጌታ ሆይ፣ እንድወድህ አንተ ታውቃለህ” ሲል መለሰለት።

ኢየሱስ “ግልገሎቼን አሰማራ” አለው።

እንደገና ለሁለተኛ ጊዜ “የዮና ልጅ ስምዖን ሆይ፣ ትወደኛለህን?” ሲል ጠየቀው።

ጴጥሮስ ከልቡ “አዎን ጌታ ሆይ፣ እንድወድህ አንተ ታውቃለህ” በማለት መለሰለት።

ኢየሱስ “ጠቦቶቼን ጠብቅ” በማለት በድጋሚ አዘዘው።

ከዚያም እንደገና ለሦስተኛ ጊዜ “የዮና ልጅ ስምዖን ሆይ፣ ትወደኛለህን?” ሲል ጠየቀው።

በዚህ ጊዜ ጴጥሮስ አዘነ። ኢየሱስ ታማኝነቴን ተጠራጠረ እንዴ ብሎ አስቦ ሊሆን ይችላል። ደግሞም ከጥቂት ጊዜ በፊት ኢየሱስ ሞት ሊፈረድበት ችሎት ፊት ቀርቦ በነበረ ጊዜ ጴጥሮስ ኢየሱስን አላውቀውም በማለት ሦስት ጊዜ ክዶት ነበር። ስለዚህ ጴጥሮስ “ጌታ ሆይ፣ አንተ ሁሉን ታውቃለህ፤ እንድወድህ አንተ ታውቃለህ” አለው።

ኢየሱስም “በጎቼን አሰማራ” በማለት ለሦስተኛ ጊዜ አዘዘው።

ኢየሱስ የትኛውን ሥራ እንዲሠሩ እንደሚፈልግ ሌሎቹ ሐዋርያት እንዲገነዘቡ ለማድረግ ጴጥሮስን መሣሪያ አድርጎ ተጠቅሞበታል። እሱ ከጥቂት ጊዜ በኋላ ምድርን ለቆ ይሄዳል፤ በመሆኑም ወደ አምላክ የበጎች በረት የሚመጡትን ሰዎች ግንባር ቀደም ሆነው እንዲያገለግሉ ይፈልጋል።

ኢየሱስ፣ አምላክ የሰጠውን ሥራ በመሥራቱ እንደታሰረና እንደተገደለ ሁሉ ጴጥሮስም ተመሳሳይ ሁኔታ እንደሚገጥመው ገለጸ። “አንተ ጒልማሳ ሳለህ” አለው ኢየሱስ፤ “ወገብህን በገዛ ራስህ ታጥቀህ ወደምትወደው ትሄድ ነበር፤ ነገር ግን በሸመገልህ ጊዜ እጆችህን ትዘረጋለህ፣ ሌላውም ያስታጥቅሃል ወደማትወደውም ይወስድሃል።” ጴጥሮስ ሰማዕታዊ ሞት የሚጠብቀው ቢሆንም ኢየሱስ “እኔን መከተልህን ቀጥል” ሲል አጥብቆ አሳሰበው።​— NW

ጴጥሮስ ዞር ብሎ ሲመለከት ዮሐንስን አየና “ጌታ ሆይ፣ ይህስ እንዴት ይሆናል?” ሲል ጠየቀው።

ኢየሱስ “እስክመጣ ድረስ ይኖር ዘንድ ብወድስ፣ ምን አግዶህ? አንተ ተከተለኝ [“እኔን መከተልህን ቀጥል፣” NW]” ሲል መለሰለት። ብዙ ደቀ መዛሙርት ኢየሱስ የተናገረውን ይህን ቃል ሐዋርያው ዮሐንስ ጨርሶ አይሞትም ማለት እንደሆነ አድርገው ተረዱት። ይሁን እንጂ ሐዋርያው ዮሐንስ ከጊዜ በኋላ እንደገለጸው ኢየሱስ ዮሐንስ አይሞትም ማለቱ አልነበረም፤ ከዚህ ይልቅ ኢየሱስ በአጭሩ ያለው “እስክመጣ ድረስ ይኖር ዘንድ ብወድስ፣ ምን አግዶህ?” ነው።

በተጨማሪም ዮሐንስ ከጊዜ በኋላ የሚከተለውን ትልቅ ትርጉም ያዘለ አስተያየት ሰጥቷል:- “ኢየሱስም ያደረገው ብዙ ሌላ ነገር ደግሞ አለ፤ ሁሉ በእያንዳንዱ ቢጻፍ ለተጻፉት መጻሕፍት ዓለም ራሱ ባልበቃቸውም ይመስለኛል።” ዮሐንስ 21:​1-25፤ ማቴዎስ 26:​32፤ 28:​7, 10

▪ ሐዋርያቱ በገሊላ ማድረግ ያለባቸውን ነገር አውቀው እንዳልነበረ የሚያሳየው ምንድን ነው?

▪ ሐዋርያቱ በገሊላ ባሕር ዳርቻ ኢየሱስን ለይተው ያወቁት እንዴት ነው?

▪ ኢየሱስ ከሞት ከተነሳ ወዲህ እስካሁን ድረስ ስንት ጊዜ ተገልጧል?

▪ ኢየሱስ ሐዋርያቱ እንዲሠሩት የፈለገውን ሥራ ጎላ አድርጎ የገለጸው እንዴት ነው?

▪ ኢየሱስ ጴጥሮስ የሚሞትበትን ሁኔታ ያመለከተው እንዴት ነው?

▪ ብዙ ደቀ መዛሙርት በተሳሳተ መንገድ የተረዱት ኢየሱስ ስለ ዮሐንስ የተናገረውን የትኛውን ሐሳብ ነበር?