በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

በገሊላ የተካሄደ ሌላ የስብከት ዙር

በገሊላ የተካሄደ ሌላ የስብከት ዙር

ምዕራፍ 49

በገሊላ የተካሄደ ሌላ የስብከት ዙር

ኢየሱስ ለሁለት ዓመት ያህል በስፋት ሲሰብክ ከቆየ በኋላ ሥራው ጋብ እያለ እንዲሄድ ወይም እንዲቀዘቅዝ አደረገን? እንደዚያ አላደረገም፤ ከዚህ ይልቅ በገሊላ ለሦስተኛ ጊዜ የስብከት ዙር በማድረግ ሥራውን ይበልጥ አስፍቶታል። በምኩራቦች እያስተማረና የመንግሥቱን ምሥራች እየሰበከ በክልሉ ውስጥ ያሉትን ከተሞችና መንደሮች ሁሉ አዳረሰ። በዚህ ዙር ያየው ነገር የስብከቱን ሥራ የማጧጧፉን አስፈላጊነት ከምን ጊዜውም በበለጠ እንዲያምንበት አድርጎታል።

ኢየሱስ በሄደበት ሁሉ የሚያገኛቸው ሕዝቦች መንፈሳዊ ፈውስና መጽናኛ እንደሚያስፈልጋቸው ተገነዘበ። እረኛ እንደሌላቸው በጎች ተጨንቀውና ተጥለው ስለነበረ አዘነላቸው። ደቀ መዛሙርቱን “መከሩስ ብዙ ነው፣ ሠራተኞች ግን ጥቂቶች ናቸው፤ እንግዲህ የመከሩን ጌታ ወደ መከሩ ሠራተኞች እንዲልክ ለምኑት” አላቸው።

ኢየሱስ የሥራ ዕቅድ አወጣ። ከአንድ ዓመት ገደማ በፊት የመረጣቸውን አሥራ ሁለቱን ሐዋርያት ወደ እሱ ጠራቸው። ጥንድ ጥንድ እያደረገ ከፋፍሎ ስድስት የሰባኪዎች ቡድን ፈጠረና መመሪያ ሰጣቸው። እንዲህ አላቸው:- “በአሕዛብ መንገድ አትሂዱ፣ ወደ ሳምራውያንም ከተማ አትግቡ፤ ይልቅስ የእስራኤል ቤት ወደሚሆኑ ወደ ጠፉት በጎች ሂዱ እንጂ። ሄዳችሁም:- መንግሥተ ሰማያት ቀርባለች ብላችሁ ስበኩ።”

ይህ እነርሱ የሚሰብኩት መንግሥት ኢየሱስ ባስተማራቸው የናሙና ጸሎት ላይ የተጠቀሰው መንግሥት ነው። አምላክ የሾመው ንጉሥ ማለትም ኢየሱስ ክርስቶስ በመካከላቸው ስለነበረ የአምላክ መንግሥት ቀርቧል ብሎ መናገር ይቻላል። ደቀ መዛሙርቱ ከሰው በላይ የሆነው የዚህ መንግሥት ወኪሎች ለመሆናቸው ማረጋገጫ እንዲሆናቸው ኢየሱስ የታመሙ ሰዎችን እንዲፈውሱና የሞቱ ሰዎችንም እንኳ ሳይቀር እንዲያስነሱ ሥልጣን ሰጣቸው። ይህን አገልግሎት በነፃ ማከናወን እንዳለባቸውም ነገራቸው።

ቀጥሎም ኢየሱስ ለስብከት ጉዞአቸው ምንም ዓይነት ቁሳዊ ዝግጅት ማድረግ እንደሌለባቸው ነገራቸው። “ወርቅ ወይም ብር ወይም ናስ በመቀነታችሁ ወይም ለመንገድ ከረጢት ወይም ሁለት እጀ ጠባብ ወይም ጫማ ወይም በትር አታግኙ፤ ለሠራተኛ ምግቡ ይገባዋልና።” መልእክቱን ከፍ አድርገው የተመለከቱ ሰዎች አዎንታዊ ምላሽ በመስጠት ምግብና መጠለያ ያቀርባሉ። ኢየሱስ እንዲህ ብሏል:- “በምትገቡባትም በማናቸይቱም ከተማ ወይም መንደር፣ በዚያ የሚገባው ማን እንደ ሆነ በጥንቃቄ መርምሩ፤ እስክትወጡም ድረስ በዚያ ተቀመጡ።”

ከዚያም ኢየሱስ የመንግሥቱ መልእክት ለቤት ባለቤቶች እንዴት መቅረብ እንዳለበት አንዳንድ መመሪያዎች ሰጠ። እንዲህ አላቸው:- “ወደ ቤትም ስትገቡ ሰላምታ ስጡ፤ ቤቱም የሚገባው ቢሆን ሰላማችሁ ይድረስለት፤ ባይገባው ግን ሰላማችሁ ይመለስላችሁ። ከማይቀበላችሁም ቃላችሁንም ከማይሰሙ ሁሉ፣ ከዚያ ቤት ወይም ከዚያች ከተማ ስትወጡ የእግራችሁን ትቢያ አራግፉ።”

ኢየሱስ መልእክታቸውን በማትቀበል ከተማ ላይ የሚበየነው ፍርድ ከባድ እንደሚሆን ገልጿል። እንዲህ አለ:- “እውነት እላችኋለሁ፣ በፍርድ ቀን ከዚያች ከተማ ይልቅ ለሰዶምና ለገሞራ አገር ይቀልላቸዋል።” ማቴዎስ 9:​35 እስከ 10:​15፤ ማርቆስ 6:​6-12፤ ሉቃስ 9:​1-5

▪ ኢየሱስ በገሊላ ሦስተኛውን የስብከት ዙር የጀመረው መቼ ነው? ይህስ ምን እምነት እንዲያድርበት አድርጎታል?

▪ አሥራ ሁለቱን ሐዋርያት እንዲሰብኩ ሲልካቸው ምን መመሪያዎችን ሰጥቷቸዋል?

▪ ደቀ መዛሙርቱ መንግሥቱ ቀርቧል ብለው ማስተማራቸው ትክክል የሆነው ለምንድን ነው?