በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ቢታንያ በሚገኘው የስምዖን ቤት ውስጥ

ቢታንያ በሚገኘው የስምዖን ቤት ውስጥ

ምዕራፍ 101

ቢታንያ በሚገኘው የስምዖን ቤት ውስጥ

ኢየሱስ ከኢያሪኮ ከወጣ በኋላ ወደ ቢታንያ አቀና። ጉዞው ዳገታማ በሆነ አስቸጋሪ መንገድ ላይ 19 ኪሎ ሜትር ያህል መጓዝ የሚጠይቅ በመሆኑ ቀኑ በጉዞ ብቻ ይገባደዳል። ኢያሪኮ ከባሕር ወለል በታች 250 ሜትር ዝቅ ብላ የምትገኝ ስትሆን ቢታንያ ደግሞ ከባሕር ወለል በላይ 760 ሜትር ከፍታ ላይ ትገኛለች። ቢታንያ የአልዓዛርና የእህቶቹ መኖሪያ እንደሆነች ታስታውስ ይሆናል። ይህች ትንሽ መንደር ከኢየሩሳሌም 3 ኪሎ ሜትር ያህል ርቃ በደብረ ዘይት ተራራ ምሥራቃዊ ዐቀበት ላይ ትገኛለች።

ብዙ ሰዎች በማለፍ በዓል ላይ ለመገኘት ኢየሩሳሌም ገብተዋል። ሃይማኖታዊ ሥርዓቶችን በመፈጸም ራሳቸውን ለማንጻት ቀደም ብለው መጥተዋል። ምናልባት አስከሬን ነክተው ወይም ደግሞ ሌላ የሚያረክስ ነገር አድርገው ይሆናል። ስለዚህ የማለፍ በዓሉን ተቀባይነት ባለው ሁኔታ ለማክበር ሲሉ ራሳቸውን ለማንጻት የሚያስችላቸውን ሥርዓት ፈጸሙ። አስቀድመው የመጡት እነዚህ ሰዎች በቤተ መቅደሱ ተሰብስበው ብዙዎቹ ኢየሱስ ወደ ማለፍ በዓሉ ይመጣ እንደሆነና እንዳልሆነ ማሰብ ጀመሩ።

ኢየሩሳሌም ስለ ኢየሱስ ብዙ ክርክር የሚካሄድባት ስፍራ ሆና ነበር። የሃይማኖት መሪዎቹ ኢየሱስን ይዘው ሊገድሉት እንደሚፈልጉ ማንም ያውቃል። እንዲያውም የት እንዳለ ያወቀ ሰው ለእነሱ ሪፖርት እንዲያደርግ አዘው ነበር። እነዚህ መሪዎች ባለፉት ጥቂት ወራት ውስጥ ሦስት ጊዜ ማለትም በዳስ በዓል ላይ፣ ቤተ መቅደሱ በድጋሚ ለአምላክ በሚወሰንበት በዓል ላይና አልዓዛርን ካስነሳው በኋላ ሊገድሉት ሞክረው ነበር። ስለዚህ ሰዎቹ ኢየሱስ እንደገና በሕዝብ ፊት ብቅ ይል ይሆን? ብለው ማሰብ ጀመሩ። “ምን ይመስላችኋል?” በማለት እርስ በርሳቸው ተጠያየቁ።

ይህ በእንዲህ እንዳለ ኢየሱስ በአይሁዶች የቀን አቆጣጠር መሠረት ኒሳን 14 ከሚውለው የማለፍ በዓል ስድስት ቀናት ቀደም ብሎ ቢታንያ ደረሰ። ኢየሱስ ወደ ቢታንያ የደረሰው አርብ ምሽት ማለትም ኒሳን 8 መጀመሪያ ላይ ነው። በአይሁድ ሕግ መሠረት በሰንበት ቀን ማለትም አርብ ፀሐይ ከጠለቀችበት ጊዜ አንስቶ ቅዳሜ ፀሐይ እስከምትጠልቅበት ጊዜ ድረስ ጉዞ ማድረግ የተከለከለ ስለነበረ ወደ ቢታንያ የተጓዘው ቅዳሜ ዕለት ሊሆን አይችልም። ኢየሱስ ቀደም ሲል እንዳደረገው ሁሉ አሁንም ወደ አልዓዛር ቤት በመሄድ አርብ ሌሊቱን ያሳለፈው በዚያ ሳይሆን አይቀርም።

ይሁን እንጂ በቢታንያ የሚኖር ሌላ ሰው ቅዳሜ ማታ ኢየሱስንና አብረውት ያሉትን ሰዎች እራት ጋበዛቸው። ሰውየው ስምዖን ተብሎ የሚጠራ ከዚህ በፊት የሥጋ ደዌ የነበረበት ሰው ነው። ኢየሱስ ቀደም ሲል ሳይፈውሰው አይቀርም። ማርታ የተለመደውን የታታሪነት ባህርይዋን በማሳየት እንግዶቹን እያገለገለች ነው። ሆኖም ማርያም እንደ ወትሮዋ ኢየሱስን ታዳምጥ ነበር። በዚህ ጊዜ ደግሞ ያደረገችው ነገር ክርክር አስነስቶ ነበር።

ማርያም ግማሽ ኪሎ የሚሆን “የጥሩ ናርዶስ” ሽቶ የያዘ አንድ የአልባስጥሮስ ብልቃጥ ከፈተች። ይህ ሽቶ በጣም ውድ ነው። እንዲያውም ዋጋው የአንድ ዓመት ደሞዝ ያህል ነው! ማርያም ሽቶውን በኢየሱስ ራስና እግር ላይ አፍስሳ እግሩን በፀጉሯ ስታብሰው ጣፋጩ መዓዛ ቤቱን በሙሉ አወደው።

ደቀ መዛሙርቱ ተቆጥተው “ይህ ጥፋት ለምንድር ነው?” ሲሉ ጠየቁ። ከዚያም የአስቆሮቱ ይሁዳ “ይህ ሽቱ ለሦስት መቶ ዲናር ተሽጦ ለድሆች ያልተሰጠ ስለ ምን ነው?” አለ። ሆኖም ይሁዳ እንዲህ ያለው ከደቀ መዛሙርቱ የገንዘብ ከረጢት ውስጥ ይሰርቅ ስለነበረ እንጂ ለድሆች አስቦ አልነበረም።

ኢየሱስ ማርያምን በመደገፍ ተናገረ። “ተዉአት” ሲል አዘዘ። “ስለ ምን ታደክሙአታላችሁ? መልካም ሥራ ሠርታልኛለች። ድሆች ሁልጊዜ ከእናንተ ጋር ይኖራሉና፣ በማናቸውም በወደዳችሁት ጊዜ መልካም ልታደርጉላቸው ትችላላችሁ፣ እኔ ግን ሁል ጊዜ ከእናንተ ጋር አልኖርም። የተቻላትን አደረገች፤ አስቀድማ ለመቃብሬ ሥጋዬን ቀባችው። እውነት እላችኋለሁ፣ ይህ ወንጌል በዓለሙ ሁሉ በሚሰበክበት በማናቸውም ስፍራ፣ እርስዋ ያደረገችው ደግሞ ለእርስዋ መታሰቢያ ሊሆን ይነገራል።”

አሁን ኢየሱስ ወደ ቢታንያ ከመጣ ከ24 ሰዓት በላይ ሆኖታል፤ ወደዚያ እንደመጣ የሚገልጸውም ወሬ ተሰራጭቶ ነበር። ስለዚህ ኢየሱስን ለማየት ብዙ ሰዎች ወደ ስምዖን ቤት መጡ። ሆኖም ሰዎቹ የመጡት ኢየሱስን ለማየት ብቻ ሳይሆን በዚያ የነበረውን አልዓዛርንም ለማየት ነበር። ስለዚህ የካህናት አለቆቹ ኢየሱስን ብቻ ሳይሆን አልዓዛርንም ለመግደል ተማከሩ። ይህን ለማድረግ ያቀዱት ብዙ ሰዎች ኢየሱስ ከሞት ያስነሳውን ሰው ሕያው ሆኖ በመመልከታቸው በኢየሱስ ስላመኑ ነው! በእርግጥም እነዚህ የሃይማኖት መሪዎች ምንኛ ክፉዎች ናቸው! ዮሐንስ 11:​55 እስከ 12:​11፤ ማቴዎስ 26:​6-13፤ ማርቆስ 14:​3-9፤ ሥራ 1:​12

▪ ኢየሩሳሌም ውስጥ በሚገኘው ቤተ መቅደስ የተካሄደው ውይይት ምንድን ነው? ለምንስ?

▪ ኢየሱስ ቢታንያ የደረሰው ቅዳሜ ሳይሆን ዓርብ መሆን ያለበት ለምንድን ነው?

▪ ኢየሱስ ቢታንያ በደረሰ ጊዜ ሰንበትን ያሳለፈው የት ሳይሆን አይቀርም?

▪ ክርክር ያስነሳው ማርያም ያደረገችው የትኛው ነገር ነው? ኢየሱስ እሷን በመደገፍ የተናገረውስ እንዴት ነው?

▪ የካህናት አለቆቹ እጅግ ክፉዎች እንደነበሩ ቁልጭ አድርጎ የሚያሳየው ምንድን ነው?