በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ብዙ ደቀ መዛሙርት ኢየሱስን መከተል አቆሙ

ብዙ ደቀ መዛሙርት ኢየሱስን መከተል አቆሙ

ምዕራፍ 55

ብዙ ደቀ መዛሙርት ኢየሱስን መከተል አቆሙ

ኢየሱስ ከሰማይ የወረደ እውነተኛ እንጀራ መሆኑን አስመልክቶ ቅፍርናሆም ውስጥ በሚገኝ አንድ ምኩራብ እያስተማረ ነበር። ንግግሩ ተአምራዊ በሆነ መንገድ ቀርቦላቸው የነበረውን እንጀራና ዓሣ ከበሉበት ከገሊላ ባሕር በስተ ምሥራቅ ከሚገኘው ሥፍራ ከመጡት ሰዎች ጋር የተጀመረው ውይይት ቀጣይ ክፍል እንደሆነ ከሁኔታው መረዳት ይቻላል።

ኢየሱስ “እኔም ስለ ዓለም ሕይወት የምሰጠው እንጀራ ሥጋዬ ነው” በማለት ንግግሩን ቀጠለ። ከሁለት ዓመታት በፊት በ30 እንደ ዘመናችን አቆጣጠር በጸደይ ወራት ኢየሱስ፣ አምላክ ዓለምን በጣም በመውደዱ ልጁን አዳኝ አድርጎ እንዳቀረበ ለኒቆዲሞስ ነግሮታል። ስለዚህ ኢየሱስ ከጥቂት ጊዜ በኋላ ሊያቀርበው በተዘጋጀው መሥዋዕት በማመን ሥጋውን ምሳሌያዊ በሆነ መንገድ የሚበላ ማንኛውም የሰው ዘር የዘላለም ሕይወት ሊያገኝ እንደሚችል ማመልከቱ ነበር።

ይሁን እንጂ ሕዝቡ በኢየሱስ ቃላት ተሰናከሉ። “ይህ ሰው ሥጋውን ልንበላ ይሰጠን ዘንድ እንዴት ይችላል?” የሚል ጥያቄ አቀረቡ። ኢየሱስ አድማጮቹ ሥጋው የሚበላው በምሳሌያዊ መንገድ እንደሆነ እንዲገነዘቡ ፈልጎ ነበር። ስለዚህ ይህን ጎላ አድርጎ ለመግለጽ ሲል አሁንም ቃል በቃል ከተተረጎመ ከበፊቱ የበለጠ ለመቀበል የሚያስቸግር ነገር ተናገረ።

ኢየሱስ እንዲህ አለ:- “የሰውን ልጅ ሥጋ ካልበላችሁ ደሙንም ካልጠጣችሁ በራሳችሁ ሕይወት የላችሁም። ሥጋዬን የሚበላ ደሜንም የሚጠጣ የዘላለም ሕይወት አለው፣ እኔም በመጨረሻው ቀን አስነሣዋለሁ። ሥጋዬ እውነተኛ መብል ደሜም እውነተኛ መጠጥ ነውና። ሥጋዬን የሚበላ ደሜንም የሚጠጣ በእኔ ይኖራል እኔም በእርሱ እኖራለሁ።”

ኢየሱስ ቃል በቃል የሰውን ሥጋ ስለ መብላት መናገሩ ቢሆን ኖሮ በእርግጥም ኢየሱስ የሰጠው ትምህርት የሚዘገንን ይሆን ነበር። ሆኖም ኢየሱስ ቃል በቃል የሰውን ሥጋ መብላትን ወይም ደም መጠጣትን ደግፎ መናገሩ አልነበረም። የዘላለም ሕይወት የሚያገኙ ሁሉ ኢየሱስ ከጥቂት ጊዜ በኋላ ፍጹም ሰብዓዊ አካሉን አሳልፎ በመስጠትና ደመ ሕይወቱን በማፍሰስ በሚያቀርበው መሥዋዕት ማመን እንዳለባቸው ጠበቅ አድርጎ መግለጹ ነበር። ሆኖም ብዙዎቹ የእሱ ደቀ መዛሙርት እንኳ ሳይቀሩ ትምህርቱን ለመረዳት ምንም ዓይነት ጥረት አላደረጉም፤ ከዚህ ይልቅ “ይህ የሚያስጨንቅ ንግግር ነው፤ ማን ሊሰማው ይችላል?” በማለት ተቃወሙ።

ኢየሱስ ከደቀ መዛሙርቱ መካከል ብዙዎቹ እያጉረመረሙ መሆኑን በመረዳት እንዲህ አላቸው:- “ይህ ያሰናክላችኋልን? እንግዲህ የሰው ልጅ አስቀድሞ ወደ ነበረበት ሲወጣ ብታዩ እንዴት ይሆናል? . . . እኔ የነገርኋችሁ ቃል መንፈስ ነው ሕይወትም ነው። ነገር ግን ከእናንተ የማያምኑ አሉ።”

ኢየሱስ በመቀጠል “ስለዚህ አልኋችሁ፣ ከአብ የተሰጠው ካልሆነ ወደ እኔ ሊመጣ የሚችል የለም” ሲል ተናገረ። ብዙዎቹ ደቀ መዛሙርት ትተውት በመሄድ እሱን መከተላቸውን አቆሙ። ስለዚህ ኢየሱስ ወደ አሥራ ሁለቱ ሐዋርያት ዞረና “እናንተ ደግሞ ልትሄዱ ትወዳላችሁን?” ሲል ጠየቃቸው።

ጴጥሮስ እንዲህ ሲል መለሰለት:- “ጌታ ሆይ፣ ወደ ማን እንሄዳለን? አንተ የዘላለም ሕይወት ቃል አለህ፤ እኛስ አንተ ክርስቶስ የሕያው የእግዚአብሔር ልጅ እንደ ሆንህ አምነናል አውቀናልም።” ምንም እንኳ ጴጥሮስና ሌሎቹ ሐዋርያት ኢየሱስ በዚህ ረገድ የሰጠው ትምህርት ሙሉ በሙሉ ገብቷቸው የነበረ ባይሆንም ጴጥሮስ የሰጠው መልስ እንዴት ያለ ግሩም የታማኝነት መግለጫ ነው!

ኢየሱስ ምንም እንኳ ጴጥሮስ በሰጠው መልስ ቢደሰትም እንዲህ አለ:- “እኔ እናንተን አሥራ ሁለታችሁን የመረጥኋችሁ አይደለምን? ከእናንተም አንዱ ዲያብሎስ ነው።” ስለ አስቆሮቱ ይሁዳ መናገሩ ነበር። በዚህ ጊዜ ኢየሱስ ይሁዳ የኃጢአት መንገድ መከተል ‘እንደ ጀመረ’ ሳይገነዘብ አይቀርም።

ኢየሱስ ሕዝቡ እሱን ለማንገሥ ያደረጉት ሙከራ እንዳይሳካ ማድረጉ ያልጠበቁት ነገር ስለነበረ በነገሩ ተበሳጭተዋል። ምናልባትም ‘ይህ ሰው ለመሲሑ የሚሰጠውን ቦታ የማይቀበል ከሆነ እንዴት መሲሕ ሊሆን ይችላል?’ የሚል አስተሳሰብ አድሮባቸው ይሆናል። ይህም ጉዳይ በሕዝቡ አእምሮ ውስጥ ገና በመብሰልሰል ላይ የነበረ ይመስላል። ዮሐንስ 6:​51-71፤ 3:​16

▪ ኢየሱስ ሥጋውን የሰጠው ለእነማን ነው? እነዚህ ሰዎችስ ‘ሥጋውን የሚበሉት’ እንዴት ነው?

▪ ሕዝቡን ያስደነገጧቸው ኢየሱስ የተናገራቸው የትኞቹ ተጨማሪ ቃላት ናቸው? ሆኖም ኢየሱስ ሊያጎላው የፈለገው ነገር ምን ነበር?

▪ ብዙዎች ኢየሱስን መከተል ሲያቆሙ ጴጥሮስ የሰጠው መልስ ምን ነበር?