በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ተወዳዳሪ ያልተገኘለት ዝነኛ ስብከት

ተወዳዳሪ ያልተገኘለት ዝነኛ ስብከት

ምዕራፍ 35

ተወዳዳሪ ያልተገኘለት ዝነኛ ስብከት

ትዕይንቱ ፈጽሞ ከማይረሱት የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮች አንዱ ነው። ኢየሱስ በአንድ ተራራ ላይ ተቀምጦ ዝነኛውን የተራራ ስብከቱን እየሰጠ ነው። ቦታው በገሊላ ባሕር አቅራቢያ ነው፤ ለቅፍርናሆም ቅርብ ሳይሆን አይቀርም። ኢየሱስ ሌሊቱን ሙሉ ሲጸልይ ካደረ በኋላ ከደቀ መዛሙርቱ መካከል አሥራ ሁለቱን ሐዋርያት አድርጎ መርጧል። ከዚያም ከእነርሱ ጋር ሆኖ በተራራው ላይ ወደሚገኘው ወደዚህ ደልዳላ ቦታ ወረደ።

አሁን መቼም ኢየሱስ በጣም ደክሞት ሊሆን ስለሚችል መተኛት ሳይፈልግ አይቀርም ብለህ ታስብ ይሆናል። ሆኖም በጣም ብዙ ሰዎች ጎረፉ፤ አንዳንዶቹ ከ95 እስከ 115 ኪሎ ሜትር የሚሆን መንገድ አቋርጠው ከኢየሩሳሌምና ከይሁዳ የመጡ ናቸው። በስተ ሰሜን ከሚገኙት ከጢሮስና ከሲዶና ባሕር ዳርቻዎች የመጡም ነበሩ። ወደዚህ ሥፍራ የመጡት ኢየሱስን ለመስማትና ከበሽታዎቻቸው ለመፈወስ ነበር። የሰይጣን ግብረ አበሮች በሆኑት ክፉ መላእክት ማለትም በአጋንንት የሚሠቃዩ ሰዎችም እንኳን ሳይቀሩ መጥተው ነበር።

ኢየሱስ ወደዚህ ቦታ ሲወርድ የታመሙት ሰዎች እሱን ለመንካት በጣም ተጠጉት፤ ኢየሱስም ሁሉንም ፈወሳቸው። ከዚያ በኋላ ኢየሱስ ከፍ ወዳለው ሥፍራ ሳይወጣ አይቀርም። ከፍ ባለው ቦታ ላይ ተቀምጦ በደልዳላው ቦታ ላይ ዙሪያውን በፊቱ የተቀመጡትን ብዙ ሰዎች ማስተማር ጀመረ። እስቲ አስበው! በዚህ ጊዜ በአድማጮቹ መካከል በከባድ ሕመም የሚሠቃይ አንድም ሰው አልነበረም!

ሰዎቹ እነዚህን አስደናቂ ተአምራት መፈጸም የቻለው አስተማሪ የሚናገረውን ለመስማት ጓጉተዋል። ይሁን እንጂ ኢየሱስ ይህን ስብከት የሰጠበት ዋነኛ ዓላማ ደቀ መዛሙርቱን ለመጥቀም ሲል ነበር። ደቀ መዛሙርቱም የተሰበሰቡት ወደእሱ ቀረብ ብለው ሳይሆን አይቀርም። ይሁን እንጂ እኛም መጠቀም እንድንችል ማቴዎስም ሆነ ሉቃስ ኢየሱስ የሰጠውን ስብከት መዝግበውልናል።

ማቴዎስ ስለ ስብከቱ የጻፈው ዘገባ ሉቃስ የጻፈውን ዘገባ አራት እጥፍ ይሆናል። ከዚህም በተጨማሪ ማቴዎስ በጻፈው ዘገባ ውስጥ የሚገኙትን አንዳንድ ክፍሎች ሉቃስ ያቀረባቸው ኢየሱስ በአገልግሎቱ ወቅት በሌላ ጊዜ እንደተናገራቸው አድርጎ ነው። ማቴዎስ 6:​9-13ን ከ⁠ሉቃስ 11:​1-4 ጋር እንዲሁም ማቴዎስ 6:​25-34ን ከ⁠ሉቃስ 12:​22-31 ጋር በማነጻጸር ይህን መረዳት ይቻላል። ሆኖም ይህ ሊያስደንቅ አይገባም። ኢየሱስ አያሌ ነገሮችን ከአንድ ጊዜ በላይ እንዳስተማረ ግልጽ ነው። ሉቃስ ከእነዚህ ትምህርቶች መካከል አንዳንዶቹን ለየት ካለ ሁኔታ አንፃር ለመዘገብ መርጧል።

የኢየሱስን ስብከት በጣም ጠቃሚ ያደረገው መንፈሳዊ ይዘቱ ጥልቅ መሆኑ ብቻ ሳይሆን እነዚህን እውነቶች ቀላልና ግልጽ አድርጎ ማቅረቡም ጭምር ነው። ይጠቀምባቸው የነበሩት ተሞክሮዎች የተለመዱ ከመሆናቸውም በላይ ይጠቅሳቸው የነበሩት ነገሮች ሰዎቹ የሚያውቋቸው ነበሩ። ይህም በአምላክ መንገድ የተሻለ ሕይወት ለመምራት የሚፈልጉ ሰዎች በሙሉ ሐሳቦቹን በቀላሉ መረዳት እንዲችሉ ረድቷቸዋል።

እውነተኛ ደስታ ያላቸው እነማን ናቸው?

ሁሉም ሰው ደስተኛ መሆን ይፈልጋል። ኢየሱስ ይህን በመገንዘብ የተራራውን ስብከት የጀመረው እውነተኛ ደስታ ያላቸው እነማን እንደሆኑ በመግለጽ ነው። ይህ ወዲያውኑ ብዛት ያላቸውን አድማጮቹን ትኩረት እንደሚስብ መገመት እንችላለን። ሆኖም ብዙዎቹ ሰዎች የመክፈቻ ቃሎቹ እርስ በርሳቸው የሚጋጩ መስለው ሳይታዩአቸው አይቀርም።

ኢየሱስ ትኩረቱን ወደ ደቀ መዛሙርቱ በማዞር እንዲህ ሲል ንግግሩን ከፈተ:- “እናንተ ድሆች ደስተኞች ናችሁ፣ የአምላክ መንግሥት የእናንተ ነውና። እናንተ አሁን የምትራቡ ደስተኞች ናችሁ፣ ትጠግባላችሁና። እናንተ አሁን የምታለቅሱ ደስተኞች ናችሁ፣ ትስቃላችሁና። ሰዎች . . . ሲጠሉአችሁ . . . ደስተኞች ናችሁ። እነሆ፣ ዋጋችሁ በሰማይ ታላቅ ነውና በዚያን ቀን ደስ ይበላችሁ ዝለሉም።”​—NW

ይህ ሉቃስ የጻፈው የኢየሱስ ስብከት መግቢያ ነው። ሆኖም ማቴዎስ በጻፈው ዘገባ መሠረት ኢየሱስ የዋሆች፣ መሐሪዎች፣ ልበ ንጹሖችና ሰላማውያን የሆኑ ሰዎችም ደስተኞች እንደሆኑ ተናግሯል። ኢየሱስ እነዚህ ሰዎች ምድርን ስለሚወርሱ፣ ምሕረት ስለሚደረግላቸው፣ አምላክን ስለሚያዩና የአምላክ ልጆች ተብለው ስለሚጠሩ ደስተኞች እንደሆኑ ገልጿል።

ይሁን እንጂ ኢየሱስ ደስተኞች ይሆናሉ ሲል አንድ ሰው በቀልድና በጨዋታ የሚያገኘውን ዓይነት ላይ ላዩን ብቻ የሆነ ተራ የደስታ ስሜት ማመልከቱ አይደለም። እውነተኛ ደስታ ከዚህ የበለጠ ጥልቀት አለው። እርካታንና በሕይወት ስኬታማነት መደሰትን ያመለክታል።

ስለዚህ እውነተኛ ደስታ ያላቸው ሰዎች በመንፈሳዊ የጎደሏቸው ነገሮች እንዳሉ የሚታወቃቸው፣ በኃጢአተኝነታቸው ያዘኑ እና አምላክን አውቀው እሱን ማገልገል የጀመሩ ሰዎች እንደሆኑ ኢየሱስ አመልክቷል። የአምላክን ፈቃድ በማድረጋቸው ጥላቻ ቢደርስባቸውና ቢሰደዱም እንኳ አምላክን እያስደሰቱ እንዳሉና የዘላለም ሕይወት ሽልማት እንደሚቀበሉ ስለሚያውቁ ደስተኞች ናቸው።

ይሁን እንጂ ብዙዎቹ የኢየሱስ አድማጮች በዛሬው ጊዜ እንዳሉት አንዳንድ ሰዎች አንድን ሰው ደስተኛ የሚያደርገው ብልጽግናና ተድላ ነው የሚል እምነት ነበራቸው። ኢየሱስ ደስታ የሚገኘው ከዚህ በተቃራኒው እንደሆነ ያውቅ ነበር። ኢየሱስ ከአድማጮቹ መካከል ብዙዎቹን በሚያስገርም መንገድ ሁኔታውን በማነጻጸር እንዲህ አለ:-

“እናንተ ባለ ጠጎች ወዮላችሁ፣ መጽናናታችሁን ተቀብላችኋልና። እናንተ አሁን የጠገባችሁ ወዮላችሁ፣ ትራባላችሁና። እናንተ አሁን የምትስቁ ወዮላችሁ፣ ታዝናላችሁና ታለቅሱማላችሁ። ሰዎች ሁሉ መልካም ሲናገሩላችሁ፣ ወዮላችሁ አባቶቻቸው ለሐሰተኞች ነቢያት እንዲሁ ያደርጉላቸው ነበርና።”

ኢየሱስ ምን ማለቱ ነበር? ሀብት ማግኘት፣ በደስታ ስሜት እየተፍለቀለቁ ተድላን ማሳደድና በሰዎች ዘንድ መወደስ ወዮታ የሚያስከትለው ለምንድን ነው? አንድ ሰው እነዚህን ነገሮች ሲያገኝና ከፍ አድርጎ ሲመለከት እውነተኛ ደስታ ሊያስገኝለት የሚችለው ብቸኛው ነገር ማለትም ለአምላክ የሚያቀርበው አገልግሎት በሕይወቱ ውስጥ ቦታ ያጣል። ልክ እንደዚሁም ኢየሱስ አንድ ሰው ድሃ መሆኑ፣ መራቡና ማዘኑ ብቻ ደስተኛ ያደርገዋል ማለቱ አይደለም። ይሁን እንጂ ብዙውን ጊዜ በእንዲህ ዓይነት አስቸጋሪ ሁኔታ ሥር የሚኖሩ ሰዎች ለኢየሱስ ትምህርቶች ጥሩ ምላሽ ሊሰጡና እውነተኛ ደስታ በማግኘት ሊባረኩ ይችላሉ።

በመቀጠልም ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን “እናንተ የምድር ጨው ናችሁ” አላቸው። እርግጥ ቃል በቃል ጨው ናችሁ ማለቱ አይደለም። ጨው ምግብ ሳይበላሽ እንዲቆይ ለማድረግ ይረዳል። በይሖዋ ቤተ መቅደስ ውስጥ በመሠዊያው አጠገብ ትልቅ የጨው ክምር ይቀመጥ ነበር። በዚያ የሚሠሩት ካህናት ጨዉን መሥዋዕቶቹ እንዳይበላሹ ለማድረግ ይጠቀሙበት ነበር።

የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት የሰዎች ደህንነት እንዲጠበቅ የሚረዳ በጎ ተጽእኖ ስለሚያሳድሩ “የምድር ጨው” ናቸው ሊባል ይቻላል። በእርግጥም የያዙት መልእክት የሚቀበሉትን ሰዎች ሕይወት ደህንነት የሚጠብቅ ነው! ይህ መልእክት ሰዎቹ መንፈሳዊ ወይም ሥነ ምግባራዊ ብልሽት እንዳይደርስባቸው የሚከላከሉ ባሕርያትን ማለትም የአቋም ጽናትን፣ አለመክዳትንና የታመኑ ሆኖ መገኘትን የመሰሉ ባሕርያት በሕይወታቸው ውስጥ እንዲያፈሩ ያደርጋቸዋል።

ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን “እናንተ የዓለም ብርሃን ናችሁ” ብሏቸዋል። መብራት በመቅረዝ ላይ እንጂ ከዕንቅብ በታች አይቀመጥም፤ ስለዚህ ኢየሱስ እናንተም “ብርሃናችሁ እንዲሁ በሰው ፊት ይብራ” አላቸው። የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት ይህን የሚያደርጉት በሕዝብ ፊት በሚሰጡት ምሥክርነትና ከመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች ጋር በሚስማማ መንገድ በመኖር ረገድ ጎልተው የሚታዩ ምሳሌዎች በመሆን ነው።

ለተከታዮቹ ያወጣው ከፍተኛ የአቋም ደረጃ

የሃይማኖት መሪዎቹ ኢየሱስ የአምላክን ሕግ እንደሚጥስ አድርገው ይመለከቱት ነበር። እንዲያውም ከጥቂት ጊዜ በፊት እሱን ለመግደል አሲረው ነበር። ስለዚህ ኢየሱስ በተራራ ስብከቱ ላይ ቀጥሎ እንዲህ ሲል ገለጸ:- “እኔ ሕግንና ነቢያትን ለመሻር የመጣሁ አይምሰላችሁ፤ ልፈጽም እንጂ ለመሻር አልመጣሁም።”

ኢየሱስ የአምላክን ሕግ እጅግ ከፍ አድርጎ ይመለከት የነበረ ከመሆኑም በላይ ሌሎችም እንዲህ ዓይነት አመለካከት እንዲኖራቸው አበረታቷል። እንዲያውም እንዲህ ብሏል:- “እንግዲህ ከነዚህ ከሁሉ ካነሱት ትእዛዛት አንዲቱን የሚ⁠ሽር ለሰውም እንዲሁ የሚያስተምር ማንም ሰው በመንግሥተ ሰማያት ከሁሉ ታናሽ ይባላል።” ይህ ማለት እንዲህ ዓይነቱ ሰው ወደ አምላክ መንግሥት አይገባም ማለት ነው።

ኢየሱስ የአምላክን ሕግ ፈጽሞ አላቃለለም። እንዲያውም አንድ ሰው ሕጉን እንዲጥስ አስተዋጽኦ የሚያደርግ አስተሳሰብ መያዙን እንኳ አውግዟል። ኢየሱስ ሕጉ “አትግደል” እንደሚል ከገለጸ በኋላ “እኔ ግን እላችኋለሁ፣ በወንድሙ ላይ የሚቆጣ [“እንደተቆጣ የሚቀጥል፣” NW] ሁሉ ፍርድ ይገባዋል” ብሏል።

በባልንጀራ ላይ እንደተቆጡ መቀጠል ምናልባትም ነፍስ ወደ መግደል ሊያደርስ የሚችል በጣም ከባድ ጉዳይ በመሆኑ ኢየሱስ አንድ ሰው ሰላምን ለመፍጠር ምን ያህል ጥረት ማድረግ እንዳለበት አብራርቷል። የሚከተለውን መመሪያ ሰጥቷል:- “እንግዲህ መባህን [ለመሥዋዕትነት የቀረበ ስጦታ] በመሠዊያው ላይ ብታቀርብ፣ በዚያም ወንድምህ አንዳች በአንተ ላይ እንዳለው ብታስብ፣ በዚያ በመሠዊያው ፊት መባህን ትተህ ሂድ፣ አስቀድመህም ከወንድምህ ጋር ታረቅ፣ በኋላም መጥተህ መባህን አቅርብ።”

ኢየሱስ በአሥርቱ ትእዛዛት ላይ የተገለጸውን ሰባተኛውን ትእዛዝ በመጥቀስ “አታመንዝር እንደ ተባለ ሰምታችኋል” በማለት ንግግሩን ቀጠለ። ይሁን እንጂ ኢየሱስ ያለማቋረጥ ስለ ምንዝር ማውጠንጠን ራሱ ትክክል እንዳልሆነ ተናግሯል። “እኔ ግን እላችኋለሁ፣ ሴትን በፍትወት ስሜት ትኩር ብሎ ያየ ሁሉ ያን ጊዜ በልቡ ከእርስዋ ጋር አመንዝሮአል።”​—NW

ኢየሱስ እዚህ ላይ እየተናገረ ያለው በአእምሮ ውስጥ ብልጭ ብሎ ስለሚጠፋ ጊዜያዊ የጾታ ስሜት ሳይሆን ‘በቀጣይነት ትኩር ብሎ ስለ ማየት’ ነው። በእንዲህ ዓይነት ሁኔታ መመልከቱን የቀጠለ ሰው የጾታ ፍላጎቱ ሊቀሰቀስና በመጨረሻም አጋጣሚው ከፈቀደለት ምንዝር ሊፈጽም ይችላል። አንድ ሰው ይህ እንዳይሆን መከላከል የሚችለው እንዴት ነው? ኢየሱስ ምን ያህል ከባድ እርምጃዎች መውሰድ ሊያስፈልግ እንደሚችል ሲያብራራ “ቀኝ ዓይንህም ብታሰናክልህ አውጥተህ ከአንተ ጣላት፤ . . . ቀኝ እጅህም ብታሰናክልህ ቆርጠህ ከአንተ ጣላት” ብሏል።

ሰዎች ብዙውን ጊዜ ሕይወታቸውን ለማዳን ሲሉ የታመመ እግራቸውን ወይም እጃቸውን በማስቆረጥ መሥዋዕት ለመክፈል ፈቃደኞች ይሆናሉ። ሆኖም ኢየሱስ በተናገረው መሠረት ከሥነ ምግባር ውጭ የሆነን አስተሳሰብና ድርጊት ለመከላከል ማንኛውንም ነገር የዓይንን ወይም የእጅን ያህል በጣም ውድ የሆነ ነገር ቢሆንም እንኳ አውጥቶ ወይም ‘ቆርጦ መጣሉ’ ይበልጥ አስፈላጊ ነው። አለበለዚያ ግን እንዲህ ዓይነቶቹ ሰዎች ዘላለማዊ ጥፋትን ወደሚያመለክተው ገሃነም (በኢየሩሳሌም አቅራቢያ የሚገኝ የቆሻሻ ማቃጠያ) እንደሚጣሉ ኢየሱስ ገልጿል።

በተጨማሪም ኢየሱስ ጉዳት ያደረሱብንንና ጥቃት የፈጸሙብንን ሰዎች እንዴት ልንይዛቸው እንደሚገባ አብራርቷል። “ክፉውን አትቃወሙ፤ ዳሩ ግን ቀኝ ጉንጭህን ለሚመታህ ሁሉ ሁለተኛውን ደግሞ አዙርለት” የሚል ምክር ሰጥ​ቷል። ኢየሱስ አንድ ሰው በራሱ ወይም በቤተሰቡ ላይ ጥቃት በሚሰነዘርበት ጊዜ መከላከል የለበትም ማለቱ አይደለም። ጥፊ በአንድ ሰው ላይ አካላዊ ጉዳት ለማድረስ የሚሰነዘር ሳይሆን አንድን ሰው ለማዋረድ የሚፈጸም ድርጊት ነው። ስለዚህ ኢየሱስ ለመግለጽ የፈለገው አንድ ሰው ቃል በቃል እጁን ሰንዝሮ በጥፊ በመማታትም ሆነ የሚናደፉ የስድብ ቃላት በመሰንዘር ጠብ ወይም ክርክር ለማነሳሳት ቢሞክር አጸፋዊ እርምጃ መውሰድ ትክክል አለመሆኑን ነው።

ኢየሱስ ጎረቤትህን ውደድ የሚለውን የአምላክ ሕግ ከጠቀሰ በኋላ እንዲህ አለ:- “እኔ ግን እንዲህ እላችኋለሁ፣ ጠላቶቻችሁን ውደዱ፤ ስደትና መከራ ለሚያደርሱባችሁም ጸልዩላቸው።” ይህን ማድረግ አስፈላጊ የሆነበትን አሳማኝ ምክንያት ሲገልጽ እንዲህ ብሏል:- “ይህን ብታደርጉ በሰማይ ላለው አባታችሁ ልጆች ትሆናላችሁ። እርሱ ለክፉዎችና ለቅኖች ፀሐዩን ያወጣል።”​—የ1980 ትርጉም

ኢየሱስ ይኸኛውን የስብከቱን ክፍል ያጠቃለለው የሚከተለውን ምክር በመስጠት ነበር:- “የሰማዩ አባታችሁ ፍጹም እንደ ሆነ እናንተ ፍጹማን ሁኑ።” ኢየሱስ ሰዎች ያላንዳች እንከን ፍጹም መሆን ይችላሉ ማለቱ አይደለም። ከዚህ ይልቅ አምላክን በመምሰል ፍቅራቸው ጠላቶቻቸውንም ጭምር እንዲያቅፍ ሊያሰፉት ይችላሉ። ሉቃስ ይህንኑ ጉዳይ አስመልክቶ ባሰፈረው ዘገባ ላይ የኢየሱስን ቃል እንዲህ ሲል ገልጾታል:- “አባታችሁ ርኅሩኅ እንደ ሆነ ርኅርኆች ሁኑ።”

ጸሎት እና በአምላክ መተማመን

ኢየሱስ ሰዎች ለአምላክ ያደሩ መስለው ለመታየት የሚፈጽሙትን የግብዝነት ድርጊት በማውገዝ ስብከቱን ቀጠለ። “ምጽዋት ስታደርግ ግብዞች . . . እንደሚያደርጉ በፊትህ መለከት አታስነፋ” ሲል ተናገረ።

ኢየሱስ በመቀጠል እንዲህ አለ:- “ስትጸልዩም እንደ ግብዞች አትሁኑ፤ ለሰው ይታዩ ዘንድ በምኩራብና በመንገድ ማዕዘን ቆመው መጸለይ ይወዳሉና።” ከዚህ ይልቅ ምን ማድረግ እንደሚገባ ሲገልጽ እንዲህ ብሏል:- “አንተ ግን ስትጸልይ፣ ወደ እልፍኝህ ግባ መዝጊያህንም ዘግተህ በስውር ላለው አባትህ ጸልይ።” ኢየሱስ በሕዝብ ፊት መጸለይ ስህተት ነው ማለቱ አይደለም፤ እሱ ራሱም በሕዝብ ፊት ጸልዮአል። ኢየሱስ ያወገዘው የአድማጮችን ስሜት ለመማረክና አድናቆታቸውን ለማትረፍ የሚቀርቡትን ጸሎቶች ነው።

በተጨማሪም ኢየሱስ የሚከተለውን ምክር ሰጠ:- “ስትጸልዩ እንደ [አሕዛብ] በከንቱ አትድገሙ።” ኢየሱስ መደጋገም በራሱ ስህተት ነው ማለቱ አይደለም። አንድ ጊዜ እሱ ራሱ ሲጸልይ ‘ያንኑ ቃል’ ደጋግሞ በመጥቀስ ጸልዮአል። ይሁን እንጂ ኢየሱስ የተቃወመው መቁጠሪያ ይዘው ጸሎታቸውን በቃል የሚደግሙ ሰዎች እንደሚያደርጉት በቃል የተጠኑ ሐረጎችን ‘እየደጋገሙ’ መጥራትን ነው።

ኢየሱስ አድማጮቹ እንዴት መጸለይ እንደሚችሉ ለማስተማር ሰባት ዓይነት ልመናዎችን ያካተተ የናሙና ጸሎት ሰጣቸው። የመጀመሪያዎቹ ሦስት ልመናዎች ለአምላክ ሉዓላዊነትና ለዓላማዎቹ ትክክለኛ እውቅና የሚሰጡ ናቸው። የአምላክ ስም እንዲቀደስ፣ መንግሥቱ እንዲመጣና ፈቃዱ እንዲፈጸም የሚቀርቡ ልመናዎች ናቸው። የቀሩት አራት ልመናዎች ለዕለታዊ ምግብ፣ ለኃጢአት ይቅርታ፣ ከአቅም በላይ ላለመፈተንና ከክፉው ለመዳን የሚቀርቡ የግል ሁኔታን የሚመለከቱ ልመናዎች ናቸው።

ኢየሱስ በመቀጠል ቁሳዊ ንብረቶችን ከሚገባው በላይ ከፍ አድርጎ መመልከት ወጥመድ እንደሚያ⁠ስ​ከትል ተናገረ። እንዲህ ሲል አጥብቆ መክሯል:- “ብልና ዝገት በሚያጠፉት ሌቦችም ቆፍረው በሚሠርቁት ዘንድ ለእናንተ በምድር ላይ መዝገብ አትሰብስቡ።” እንዲህ ያለው ሀብት ጠፊም ብቻ ሳይሆን በአምላክ ዘንድ ምንም የሚያስገኝልን ዋጋ የለም።

በመሆኑም ኢየሱስ “ነገር ግን . . . ለእናንተ በሰማይ መዝገብ ሰብስቡ” ብሏል። ይህን ማድረግ የምትችለው ለአምላክ የምታቀርበውን አገልግሎት በሕይወትህ ውስጥ በአንደኛ ቦታ በማስቀመጥ ነው። በዚህ መንገድ በአምላክ ዘንድ የምናከማቸውን ዋጋ ወይም እንዲህ ማድረጋችን የሚያስገኝልንን ታላቅ ሽልማት ማንም ሊወስድብን አይችልም። ከዚያም ኢየሱስ “መዝገብህ ባለበት ልብህ ደግሞ በዚያ ይሆናልና” ሲል አክሎ ተናግሯል።

ከዚህም በተጨማሪ ኢየሱስ ፍቅረ ነዋይ ስለሚያስከትለው ወጥመድ ሲናገር የሚከተለውን ምሳሌ ሰጥቷል:- “የሰውነት መብራት ዓይን ናት። ዓይንህ እንግዲህ ጤናማ [“ቀና፣” NW] ብትሆን፣ ሰውነትህ ሁሉ ብሩህ ይሆናል፤ ዓይንህ ግን ታማሚ [“ክፉ፣” NW] ብትሆን፣ ሰውነትህ ሁሉ የጨለመ ይሆናል።” በትክክል የሚያይ ዓይን ለሰውነት በጨለማ ቦታ እንደ በራ መብራት ነው። ሆኖም ዓይን በትክክል ማየት እንዲችል ቀና መሆን ማለትም በአንድ ነገር ላይ ማተኮር አለበት። አዛብቶ የሚያይ ዓይን ነገሮችን በተሳሳተ መንገድ እንድንመዝንና ቁሳዊ ነገሮችን ከአምላክ አገልግሎት በማስቀደም እንድናሳድድ ያደርገናል። ይህም ‘ሰውነታችን በሙሉ’ እንዲጨልም ያደርገዋል።

ኢየሱስ ይህን ጉዳይ የደመደመው የሚከተለውን ኃይለኛ ምሳሌ በመናገር ነው:- “ለሁለት ጌቶች መገዛት የሚቻለው ማንም የለም፤ ወይም አንዱን ይጠላል ሁለተኛውንም ይወዳል፤ ወይም ወደ አንዱ ይጠጋል ሁለተኛውንም ይንቃል፤ ለእግዚአብሔርና ለገንዘብ መገዛት አትችሉም።”

ኢየሱስ ይህን ምክር ከሰጠ በኋላ አድማጮቹ የአምላክን አገልግሎት ካስቀደሙ ለሚያስፈልጓቸው ቁሳዊ ነገሮች መጨነቅ እንደሌለባቸው አረጋገጠላቸው። “ወደ ሰማይ ወፎች ተመልከቱ፤ አይዘሩም አያጭዱምም በጎተራም አይከቱም፣ የሰማዩ አባታችሁም ይመግባቸዋል” አላቸው። ከዚያም “እናንተ ከእነርሱ እጅግ አትበልጡምን?” ሲል ጠየቃቸው።

ቀጥሎም ኢየሱስ የሜዳ አበቦችን ጠቀሰና “ሰሎሞንስ እንኳ በክብሩ ሁሉ ከነዚህ እንደ አንዱ አልለበሰም” ሲል ገለጸ። ከዚያም እንዲህ ሲል ቀጠለ:- “እግዚአብሔር . . . የሜዳን ሣር እንዲህ የሚያለብሰው ከሆነ፣ እናንተ እምነት የጎደላችሁ፣ እናንተንማ ይልቁን እንዴት?” ስለዚህ ኢየሱስ እንዲህ በማለት ደመደመ:- “ምን እንበላለን? ምንስ እንጠጣለን? ምንስ እንለብሳለን? ብላችሁ አትጨነቁ፤ . . . ይህ ሁሉ እንዲያስፈልጋችሁ የሰማዩ አባታችሁ ያውቃልና። ነገር ግን አስቀድማችሁ የእግዚአብሔርን መንግሥት ጽድቁንም ፈልጉ፣ ይህም ሁሉ ይጨመርላችኋል።”

ወደ ሕይወት የሚወስደው መንገድ

ወደ ሕይወት በሚወስደው መንገድ መጓዝ ማለት የኢየሱስን ትምህርቶች መከተል ነው። ሆኖም ይህን ማድረጉ ቀላል አይደለም። ለምሳሌ ያህል ፈሪሳውያን በሌሎች ላይ ያላንዳች ርኅራኄ የመፍረድ ዝንባሌ ነበራቸው፤ ብዙዎችም ይህን የእነሱን መጥፎ ምሳሌ ሳይከተሉ አልቀረም። ስለዚህ ኢየሱስ የተራራ ስብከቱን በመቀጠል የሚከተለውን ምክር ሰጠ:- “እንዳይፈረድባችሁ አትፍረዱ፤ በምትፈርዱበት ፍርድ ይፈረድባችኋልና።”

ከሚገባው በላይ ነቃፊ የነበሩትን ፈሪሳውያን አመራር መከተሉ አደገኛ ነበር። ሉቃስ ባሰፈረው ዘገባ መሠረት ኢየሱስ የሚከተለውን ምሳሌ በመስጠት ይህ አደገኛ መሆኑን ገልጿል:- “ዕውር ዕውርን ሊመራ ይችላልን? ሁለቱ በጉድጓድ አይወድቁምን?”

የሌሎችን ስህተት አጉልተን በመመልከትና ስህተቶቻቸውን በመለቃቀም ከሚገባው በላይ ነቃፊዎች መሆን ከባድ በደል ነው። ስለዚህ ኢየሱስ የሚከተለውን ጥያቄ አቀረበ:- “ወንድምህን:- ከዓይንህ ጉድፍ ላውጣ ፍቀድልኝ እንዴትስ ትለዋለህ? እነሆም በዓይንህ ምሰሶ አለ። አንተ ግብዝ፣ አስቀድመህ ከዓይንህ ምሰሶውን አውጣ፣ ከዚያም በኋላ ከወንድምህ ዓይን ጉድፉን ታወጣ ዘንድ አጥርተህ ታያለህ።”

ይህ ማለት ግን የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት የሌሎች ሰዎችን ሁኔታ ማስተዋል የለባቸውም ማለት አይደለም፤ ምክንያቱም ኢየሱስ “የተቀደሰውን ለውሾች አትስጡ፣ ዕንቁዎቻችሁንም በእሪያዎች ፊት አትጣሉ” ብሏል። በአምላክ ቃል ውስጥ ያሉት እውነቶች ቅዱስ ናቸው። እነዚህ እውነቶች ምሳሌያዊ ዕንቁዎች ናቸው። ሆኖም እንደ ውሻ ወይም እርያ ያሉ አንዳንድ ሰዎች ለእነዚህ ውድ እውነቶች ምንም ዓይነት አድናቆት የማያሳዩ ከሆነ የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት እነዚህን ሰዎች ትተው ለመቀበል ፈቃደኛ የሆኑ ሰዎችን መፈለግ አለባቸው።

ምንም እንኳ ኢየሱስ በተራራ ስብከቱ ላይ ቀደም ሲል ስለ ጸሎት አስፈላጊነት ያብራራ ቢሆንም አሁን ደግሞ በጸሎት የመጽናትን አስፈላጊነት ጠበቅ አድርጎ ገለጸ። “ያለማቋረጥ ለምኑ፣ ይሰጣችሁማል” (NW) ሲል አጥብቆ አሳስቧል። አምላክ ለጸሎቶች መልስ ለመስጠት የቱን ያህል ዝግጁ መሆኑን በምሳሌ ለማስረዳት ኢየሱስ የሚከተለውን ጥያቄ አቀረበ:- “ልጁ እንጀራ ቢለምነው፣ ድንጋይን የሚሰጠው ከእናንተ ማን ሰው ነው? . . . እንኪያስ እናንተ ክፉዎች ስትሆኑ ለልጆቻችሁ መልካም ስጦታ መስጠትን ካወቃችሁ፣ በሰማያት ያለው አባታችሁ ለሚለምኑት እንዴት አብልጦ መልካም ነገርን ይሰጣቸው?”

ኢየሱስ በመቀጠል ብዙውን ጊዜ ወርቃማው ሕግ እየተባለ የሚጠራውን አንድ ዝነኛ የሥነ ምግባር ደንብ ሰጠ። እንዲህ አለ:- “እንግዲህ ሰዎች ሊያደርጉላችሁ የምትወዱትን ሁሉ እናንተ ደግሞ እንዲሁ አድርጉ​ላቸው።” ከዚህ ደንብ ጋር ተስማምቶ መኖር ለሌሎች መልካም በመሥራትና ሰዎች ለእኛ እንዲያሳዩን የምንፈልገውን ባሕርይ ለእነርሱ በማሳየት ተጨባጭ ነገር ማድረግን ይጠይቃል።

ወደ ሕይወት በሚወስደው መንገድ መጓዝ ቀላል እንዳልሆነ በሚከተለው የኢየሱስ መመሪያ ላይ ተገልጿል:- “በጠበበው ደጅ ግቡ፤ ወደ ጥፋት የሚወስደው ደጅ ሰፊ፣ መንገዱም ትልቅ ነውና፣ ወደ እርሱም የሚገቡ ብዙዎች ናቸው፤ ወደ ሕይወት የሚወስደው ደጅ የጠበበ፣ መንገዱም የቀጠነ ነውና፣ የሚያገኙትም ጥቂቶች ናቸው።”

በቀላሉ የመታለል አደጋ ያለ በመሆኑ ኢየሱስ እንዲህ ሲል አስጠንቅቋል:- “የበግ ለምድ ለብሰው ከሚመጡባችሁ በውሥጣቸው ግን ነጣቂዎች ተኩላዎች ከሆኑ ከሐሰተኞች ነቢያት ተጠንቀቁ።” ጥሩ ዛፎችና መጥፎ ዛፎች በፍሬያቸው ተለይተው ሊታወቁ እንደሚችሉ ሁሉ ሐሰተኛ ነቢያትም በምግባራቸውና በትምህርታቸው ተለይተው ሊታወቁ እንደሚችሉ ኢየሱስ ገልጿል።

ኢየሱስ በመቀጠል አንድን ሰው የእርሱ ደቀ መዝሙር የሚያሰኘው የሚናገረው ነገር ሳይሆን የሚያደርገው ነገር እንደሆነ ገልጿል። አንዳንድ ሰዎች ጌታችን ኢየሱስ ነው ይላሉ፤ ሆኖም የአባቱን ፈቃድ የማያደርጉ ከሆነ “ከቶ አላወቅኋችሁም፤ እናንተ ዓመፀኞች፣ ከእኔ ራቁ ብዬ እመሰክርባቸዋለሁ” ብሏል።

በመጨረሻም ኢየሱስ ፈጽሞ የማይረሳውን የስብከቱን መደምደሚያ ሐሳብ ተናገረ። እንዲህ አለ:- “ይህን ቃሌን ሰምቶ የሚያደርገው ሁሉ ቤቱን በዓለት ላይ የሠራ ልባም ሰውን ይመስላል። ዝናብም ወረደ ጎርፍም መጣ ነፋስም ነፈሰ ያንም ቤት ገፋው፣ በዓለት ላይም ስለ ተመሠረተ አልወደቀም።”

በሌላ በኩል ደግሞ ኢየሱስ እንዲህ ሲል ገለጸ:- “ይህንም ቃሌን ሰምቶ የማያደርገው ሰው ሁሉ ቤቱን በአሸዋ ላይ የሠራ ሰነፍ ሰውን ይመስላል። ዝናብም ወረደ ጎርፍም መጣ ነፋስም ነፈሰ ያንም ቤት መታው፣ ወደቀም፣ አወ​ዳደቁም ታላቅ ሆነ።”

ኢየሱስ እንደ ሃይማኖት መሪዎቻቸው ሳይሆን እንደ ባለ ሥልጣን ሆኖ ያስተምራቸው ስለነበር ስብከቱን ሲጨርስ ሕዝቡ በማስተማር ችሎታው በጣም ተገረሙ። ሉቃስ 6:​12-23፤ ማቴዎስ 5:​1-12፤ ሉቃስ 6:​24-26፤ ማቴዎስ 5:​13-48፤ 6:​1-34፤ 26:​36-45፤ 7:​1-29፤ ሉቃስ 6:​27-49

▪ ኢየሱስ እጅግ ዝነኛ የሆነውን ስብከቱን የሰጠው የት ሆኖ ነው? እነማን በቦታው ተገኝተው ነበር? ስብከቱን ከመስጠቱ በፊትስ ምን ተከናውኖ ነበር?

▪ ሉቃስ በስብከቱ ላይ የተሰጡትን አንዳንድ ትምህርቶች ከሌላ ሁኔታ አንፃር የዘገበው ለምንድን ነው?

▪ የኢየሱስን ስብከት በጣም ጠቃሚ ያደረገው ምንድን ነው?

▪ እውነተኛ ደስታ ያላቸው እነማን ናቸው? ለምንስ?

▪ ወዮላችሁ የተባሉት እነማን ናቸው? ለምንስ?

▪ የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት “የምድር ጨው” እና “የዓለም ብርሃን” የሆኑት እንዴት ነው?

▪ ኢየሱስ የአምላክን ሕግ ከፍ አድርጎ የተመለከተው እንዴት ነው?

▪ ኢየሱስ የነፍሰ ገዳይነትና የምንዝር መንስኤ የሆኑትን ነገሮች ከሥሩ ነቅሎ ለመጣል የሚያስችል ምን መመሪያ ሰጥቷል?

▪ ኢየሱስ ሁለተኛውን ጉንጭ ስለማዞር ሲናገር ምን ማለቱ ነበር?

▪ አምላክ ፍጹም እንደሆነ ሁሉ እኛም ፍጹማን ልንሆን የምንችለው በምን መንገድ ነው?

▪ ኢየሱስ ጸሎትን በተመለከተ ምን መመሪያ ሰጥቷል?

▪ ሰማያዊ ውድ ሃብቶች የላቀ ዋጋ ያላቸው ለምንድን ነው? ሊገኙ የሚችሉትስ እንዴት ነው?

▪ አንድ ሰው ፍቅረ ነዋይን ማስወገድ እንዲችል ለመርዳት ምን ምሳሌዎች ቀርበዋል?

▪ ኢየሱስ መጨነቅ አስፈላጊ እንዳልሆነ የተናገረው ለምንድን ነው?

▪ ኢየሱስ በሌሎች ላይ መፍረድን በተመለከተ ምን አለ? ሆኖም ደቀ መዛሙርቱ ሰዎችን በተመለከተ አስተዋዮች መሆን እንዳለባቸው ያመለከተው እንዴት ነው?

▪ ኢየሱስ ጸሎትን በተመለከተ ምን ተጨማሪ ሐሳብ ሰጥቷል? ሥነ ምግባርን በተመለከተ ያወጣውስ ደንብ ምንድን ነው?

▪ ኢየሱስ ወደ ሕይወት በሚወስደው መንገድ ላይ መጓዝ ቀላል እንዳልሆነና የመታለል አደጋ እንዳለ ያመለከተው እንዴት ነው?

▪ ኢየሱስ ስብከቱን የደመደመው እንዴት ነው? ስብከቱስ ምን ውጤት አስገኝቷል?