በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ተዘጋጅታችሁ ጠብቁ!

ተዘጋጅታችሁ ጠብቁ!

ምዕራፍ 78

ተዘጋጅታችሁ ጠብቁ!

ኢየሱስ ሕዝቡን ከመጎምጀት እንዲጠበቁ ካስጠነቀቃቸውና ደቀ መዛሙርቱ ለቁሳዊ ነገሮች ከልክ ያለፈ ትኩረት እንዳይሰጡ ካሳሰባቸው በኋላ የሚከተለውን ማበረታቻ ሰጠ:- “አንተ ታናሽ መንጋ፣ መንግሥትን ሊሰጣችሁ የአባታችሁ በጎ ፈቃድ ነውና አትፍሩ።” በዚህ መንገድ ኢየሱስ ሰማያዊውን መንግሥት የሚወርሱት በአንጻራዊ ሁኔታ ሲታይ ቁጥራቸው አነስተኛ የሆነ (ከጊዜ በኋላ ቁጥራቸው 144,000 እንደሆነ የተገለጸ) ሰዎች እንደሆኑ ጠቁሟል። ዘላለማዊ ሕይወት የሚያገኙት አብዛኞቹ ሰዎች የመንግሥቱ ምድራዊ ተገዥዎች ይሆናሉ።

‘መንግሥቱ’ እንዴት ያለ ግሩም ስጦታ ነው! ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱ ይህን ስጦታ ሲቀበሉ ሊያሳዩት የሚገባውን ትክክለኛ ምላሽ ሲገልጽ “ያላችሁን ሽጡ ምጽዋትም ስጡ” ሲል አጥብቆ አሳስቧቸዋል። አዎን፣ ሌሎችን በመንፈሳዊ ለመጥቀም ንብረቶቻቸውን መጠቀምና በዚህ መንገድ “በሰማያት የማያልቅ መዝገብ” ማከማቸት ይኖርባቸዋል።

ኢየሱስ በመቀጠል ደቀ መዛሙርቱ የሚመለስበትን ጊዜ ተዘጋጅተው እንዲጠብቁ መከራቸው። እንዲህ አለ:- “ወገባችሁ የታጠቀ መብራታችሁም የበራ ይሁን፤ እናንተም ጌታቸው መጥቶ ደጁን ሲያንኳኳ ወዲያው እንዲከፍቱለት ከሰርግ እስኪመለስ ድረስ የሚጠብቁ ሰዎችን ምሰሉ ጌታቸው በመጣ ጊዜ ሲተጉ የሚያገኛቸው እነዚያ ባሪያዎች ብፁዓን [“ደስተኞች፣” NW] ናቸው፤ እውነት እላችኋለሁ፣ ታጥቆ በማዕድ ያስቀምጣቸዋል ቀርቦም ያገለግላቸዋል።”

በዚህ ምሳሌ ላይ አገልጋዮቹ ዝግጁ ሆነው የጌታቸውን መመለስ ይጠባበቁ እንደነበረ የሚያሳየው ረጅሙን ቀሚሳቸውን ወደ ላይ ሰብስበው በመቀነታቸው በመታጠቅና በሚገባ ዘይት የተሞሉ ፋኖሶች በሚሰጡት መብራት በመጠቀም እስከ ሌሊት ድረስ ሥራቸውን ማከናወናቸውን መቀጠላቸው ነው። ኢየሱስ እንዲህ ሲል ገለጸ:- ‘ጌታቸው ከሌሊቱ በሁለተኛው ክፍል [ከምሽቱ ሦስት ሰዓት ገደማ ጀምሮ እስከ እኩለ ሌሊት] አልፎ ተርፎም በሦስተኛው ክፍል [ከእኩለ ሌሊት እስከ ዘጠኝ ሰዓት] ቢመጣና ዝግጁ ሆነው ሲጠብቁ ቢያገኛቸው ደስተኞች ናቸው!’

ጌታቸው አገልጋዮቹን ለየት ባለ መንገድ ወሮታውን ይከፍላቸዋል። በማዕድ አስቀምጦ ያገለግላቸዋል። እንደ ባሪያዎች ሳይሆን እንደ ታማኝ ወዳጆች አድርጎ ያስተናግዳቸዋል። አገልጋዮቹ የጌታቸውን መመለስ እየጠበቁ ሌሊቱን ሙሉ መሥራታቸውን በመቀጠላቸው ይህ እንዴት ያለ ግሩም ወሮታ ይሆንላቸዋል! ኢየሱስ “የሰው ልጅ ባላሰባችሁበት ሰዓት በድንገት ይመጣል፤ ስለዚህ እናንተም ተዘጋጅታችሁ ጠብቁ” (የ1980 ትርጉም፤ ጋደል አድርገን የጻፍነው እኛ ነን።) በማለት ደምድሟል።

በዚህ ጊዜ ጴጥሮስ “ጌታ ሆይ፣ ይህን ምሳሌ ለእኛ ወይስ ደግሞ ለሁሉ ትናገራለህን?” ሲል ጠየቀው።

ኢየሱስ በቀጥታ ከመመለስ ይልቅ ሌላ ምሳሌ ሰጠ። “እንኪያስ ምግባቸውን በጊዜው ይሰጣቸው ዘንድ ጌታው በቤተ ሰዎቹ ላይ የሚሾመው ታማኝና ልባም መጋቢ ማን ነው?” ሲል ጠየቀ። “ጌታው መጥቶ እንዲህ ሲያደርግ የሚያገኘው ያ ባሪያ ብፁዕ [“ደስተኛ፣” NW] ነው። እውነት እላችኋለሁ፣ ባለው [“በንብረቱ፣” NW] ሁሉ ላይ ይሾመዋል።”

“ጌታው” የተባለው ኢየሱስ ክርስቶስ እንደሆነ ግልጽ ነው። ‘መጋቢው’ የደቀ መዛሙርቱን “ታናሽ መንጋ” በጥቅሉ እንደ አንድ አካል አድርጎ የሚያመለክት ነው፤ “ቤተ ሰዎቹ” የሚለው ደግሞ ሰማያዊ መንግሥት የሚቀበሉትን የእነዚሁ የ144,000 ቡድን የሚያመለክት ሲሆን ይኸኛው አባባል ግን በግለሰብ ደረጃ የሚያከናውኑትን ሥራ ጎላ አድርጎ የሚያሳይ ነው። ታማኙ መጋቢ እንዲጠብቀው የተሾመበት ‘ንብረት’ የመንግሥቱን ምድራዊ ተገዥዎች ጨምሮ ጌታው በምድር ላይ ያለው ሀብት ሁሉ ነው።

ኢየሱስ ምሳሌውን መናገሩን በመቀጠል ከመጋቢው ወይም ከባሪያው ክፍል አባላት መካከል ታማኝነታቸውን የሚያጎድሉ ሊኖሩ እንደሚችሉ ሲያመለክት እንዲህ ብሏል:- “ያ ባሪያ ግን:- ጌታዬ እስኪመጣ ይዘገያል ብሎ በልቡ ቢያስብ ሎሌዎችንና ገረዶችንም ይመታ ይበላም ይጠጣም ይሰክርም ዘንድ ቢጀምር፣ የዚያ ባሪያ ጌታ ባልጠበቃት ቀን . . . ይመጣል፣ ከሁለትም ይሰነጥቀዋል።”

ኢየሱስ ትምህርቱን አንዳንዶቹ ሲቀበሉት ሌሎቹ ያልተቀበሉት በመሆኑ የእሱ መምጣት ለአይሁዳውያን እሳት እንደጫረባቸው ገለጸ። ከሦስት ዓመታት በፊት በውኃ ተጠምቋል፤ ሆኖም አሁን ወደ ሞት የሚጠመቅበት ጊዜ ከምንጊዜውም የበለጠ ወደ ፍጻሜው በመቅረቡ “እስክትፈጸምም ድረስ እንዴት እጨነቃለሁ?” ሲል ተናገረ።

ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ እነዚህን ሐሳቦች ከሰጠ በኋላ እንደገና ለሕዝቡ መናገር ጀመረ። ማንነቱን ቁልጭ አድርጎ የሚያሳየውን ማስረጃና ማስረጃው የሚያስተላልፈውን መልእክት ለመቀበል አሻፈረኝ በማለት ባሳዩት ልበ ደንዳናነት የተሰማውን ሐዘን ገልጿል። እንዲህ አላቸው:- “ደመና ከምዕራብ ሲወጣ ባያችሁ ጊዜ፣ ወዲያው:- ዝናብ ይመጣል ትላላችሁ፣ እንዲሁም ይሆናል፤ በአዜብም ነፋስ ሲነፍስ:- ትኩሳት ይሆናል ትላላችሁ፣ ይሆንማል። እናንት ግብዞች፣ የምድሩንና የሰማዩን ፊት ልትመረምሩ ታውቃላችሁ፣ ነገር ግን ይህን ዘመን የማትመረምሩ እንዴት ነው?” ሉቃስ 12:​32-59

▪ ‘የታናሹ መንጋ’ አባላት ስንት ናቸው? የሚያገኙት ውርሻስ ምንድን ነው?

▪ ኢየሱስ አገልጋዮቹ ዝግጁ ሆነው መጠበቅ እንዳለባቸው ጎላ አድርጎ ያሳየው እንዴት ነው?

▪ በኢየሱስ ምሳሌ ላይ “ጌታ፣” “መጋቢ፣” “ቤተ ሰዎቹ” እና “ንብረቱ” የተባሉት እነማን ናቸው?