በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ተጨማሪ እርማት

ተጨማሪ እርማት

ምዕራፍ 63

ተጨማሪ እርማት

ኢየሱስና ሐዋርያቱ ቅፍርናሆም በሚገኘው ቤት ውስጥ ተቀምጠው ሳሉ ሐዋርያቱ ታላቅ የሚሆነው ማን ነው በሚል ያካሄዱትን ክርክር በተመለከተ ከተደረገው ውይይት በተጨማሪ ሌላ ጉዳይም ተነስቶ ነበር። ይኸኛውም ሁኔታ የተከሰተው ከቅፍርናሆም ሲመለሱ ሳይሆን አይቀርም፤ ኢየሱስ በዚህ ወቅት በቦታው አልነበረም። ሐዋርያው ዮሐንስ “አንድ ሰው በስምህ አጋንንትን ሲያወጣ አየነው፣ ስለማይከተለንም ከለከልነው” ሲል ገለጸ።

ዮሐንስ የመፈወስ ሥልጣን ያላቸው ሐዋርያት ብቻ ናቸው የሚል አመለካከት እንደነበረው ከሁኔታው መረዳት ይቻላል። ስለዚህ ተአምራት ሲፈጽም የነበረው ሰው የእነሱ ቡድን አባል ስላልሆነ ይህን ማድረጉ ትክክል አይደለም የሚል ስሜት አድሮበት ነበር።

ይሁን እንጂ ኢየሱስ የሚከተለውን ምክር ሰጠ:- “በስሜ ተአምር ሠርቶ በቶሎ በእኔ ላይ ክፉ መናገር የሚችል ማንም የለምና አትከልክሉት፤ የማይቃወመን እርሱ ከእኛ ጋር ነውና። የክርስቶስ ስለሆናችሁ በስሜ ጽዋ ውኃ የሚያጠጣችሁ ሁሉ፣ ዋጋው እንዳይጠፋበት እውነት እላችኋለሁ።”

ይህ ሰው ከኢየሱስ ጎን ለመቆም የግድ ኢየሱስን በአካል መከተል አያስፈልገውም። በወቅቱ የክርስቲያን ጉባኤ ገና አልተቋቋመም ነበር፤ ስለዚህ የቡድናቸው አባል አለመሆኑ የሌላ የተለየ ጉባኤ አባል ነው አያሰኘውም። ሰውየው በኢየሱስ ስም ላይ እምነት ነበረው፤ በመሆኑም አጋንንትን ማው​ጣት ችሏል። ኢየሱስ ዋጋ ሊከፈለው የሚገባ ተግባር ነው ብሎ ከጠቀሰው ነገር የማይተናነስ ተግባር እያከናወነ ነበር። ኢየሱስ ይህን በማድረጉ ዋጋ የሚከፈለው መሆኑን አመልክቷል።

ሆኖም ሰውየው ሐዋርያቱ በተናገሩትና ባደረጉት ነገር ተሰናክሎ ቢሆን ኖሮስ? ይህ በጣም ከባድ መዘዝ ሊያስከትል ይችል ነበር! ኢየሱስ እንዲህ አለ:- “ከሚያምኑት ከእነዚህ ከታናናሾቹ አንዱን የሚያሰናክል ሁሉ ትልቅ የወፍጮ ድንጋይ በአንገቱ ታስሮ ወደ ባሕር ቢጣል ይሻለው ነበር።”

ኢየሱስ ተከታዮቹ የእጅን፣ የእግርን ወይም የዓይንን ያህል ውድ የሆነ ማንኛውም ነገር እንቅፋት የሚሆንባቸው ከሆነ ከሕይወታቸው ውስጥ ሊያስወግዱት እንደሚገባ ተናግሯል። እንዲህ ዓይነቱን ነገር ይዞ ዘላለማዊ ጥፋትን ወደሚያመለክተው ወደ ገሃነም (በኢየሩሳሌም አቅራቢያ የሚገኝ የቆሻሻ ማቃጠያ) ከመጣል ይህን ውድ ነገር አጥቶ ወደ አምላክ መንግሥት መግባት ይሻላል።

ኢየሱስ የሚከተለውንም ማስጠንቀቂያ ሰጥቷል:- “ከነዚህ ከታናናሾቹ አንዱን እንዳትንቁ ተጠንቀቁ፤ መላእክቶቻቸው በሰማያት ዘወትር በሰማያት ያለውን የአባቴን ፊት ያያሉ እላችኋለሁና።” ከዚያም መቶ በጎች ስላሉትና ከመቶዎቹ አንዷ ስለጠፋችበት ሰው በተናገረ ጊዜ “ታናናሾቹ” ምን ያህል ውድ እንደሆኑ ገልጿል። ኢየሱስ ሰውየው ዘጠና ዘጠኙን ትቶ የጠፋችውን በግ ፍለጋ እንደሚሄድ ገልጿል፤ በጓን ሲያገኛትም ከዘጠና ዘጠኙ ይበልጥ በእሷ ይደሰታል። ከዚ​ያም ኢየሱስ “እንደዚሁ ከእነዚህ ከታናናሾቹ አንዱ እንዲጠፋ በሰማያት ያለው አባታችሁ ፈቃድ አይደለም” ሲል ደመደመ።

ኢየሱስ ሐዋርያቱ ያደረጉትን ክርክር በአእምሮው ይዞ ሳይሆን አይቀርም፣ እንዲህ ሲል አጥብቆ መከራቸው:- “በነፍሳችሁ ጨው ይኑርባችሁ፣ እርስ በርሳችሁም ተስማሙ።” ምንም ጣዕም የሌላቸው ምግቦች ጣፋጭ እንዲሆኑ ጨው ይጨመርባቸዋል። ምሳሌያዊ ጨውም አንድ ሰው የሚናገረው ነገር በቀላሉ ተቀባይነት እንዲያገኝ ያደርገዋል። እንዲህ ዓይነት ጨው መኖሩ ሰላምን ለመጠበቅ ይረዳል።

ሆኖም በሰብዓዊ አለፍጽምና ምክንያት አንዳንድ ጊዜ የከረረ አለመግባባት ይነሳል። ኢየሱስ ይህ ሁኔታ ሲፈጠር ምን ማድረግ እንደሚገባ የሚጠቁሙ መመሪያዎችም ሰጥቷል። ኢየሱስ እንዲህ አለ:- “ወንድምህም ቢበድልህ፣ ሄደህ አንተና እርሱ ብቻችሁን ሆናችሁ ውቀሰው። ቢሰማህ፣ ወንድምህን ገንዘብ አደረግኸው።” ባይሰማ ግን “በሁለት ወይም በሦስት ምስክር አፍ ነገር ሁሉ እንዲጸና፣ ዳግመኛ አንድ ወይም ሁለት ከአንተ ጋር ውሰድ” በማለት ኢየሱስ መደረግ ያለበትን ነገር ገልጿል።

ኢየሱስ የመጨረሻው አማራጭ ጉዳዩን “ለቤተ ክርስቲያን” ማቅረብ እንደሆነ ተናግሯል። ይህም ጉዳዩን የፍርድ ውሳኔ መስጠት ለሚችሉት ኃላፊነት ያላቸው የጉባኤ የበላይ ተመልካቾች ማቅረብ ማለት ነው። በደለኛው ውሳኔያቸውን የማያከብር ከሆነ “እንደ አረመኔና እንደ ቀራጭ ይሁንልህ” በማለት ኢየሱስ ደምድሟል።

የበላይ ተመልካቾች እንዲህ ዓይነት ውሳኔ በሚሰጡበት ጊዜ በይሖዋ ቃል ውስጥ ያሉትን መመሪያዎች በጥብቅ መከተል ይኖርባቸዋል። በዚህ መንገድ ግለሰቡ ጥፋተኛና ቅጣት የሚገባው ሆኖ ካገኙት ፍርዱ አስቀድሞ “በሰማይ የታሰረ ይሆናል።” ‘በምድር ሲፈቱት’ ደግሞ ማለትም ግለሰቡን ንጹሕ ሆኖ ሲያገኙት አስቀድሞ “በሰማይ የተፈታ ይሆናል።” እንዲህ ዓይነት የፍርድ ጉዳዮች በሚታዩበት ጊዜ ኢየሱስ “ሁለት ወይም ሦስት በስሜ በሚሰበሰቡበት በዚያ በመካከላቸው እሆናለሁ” ብሏል። ማቴዎስ 18:​6-20፤ ማርቆስ 9:​38-50፤ ሉቃስ 9:​49, 50

▪ በኢየሱስ ዘመን ከእሱ ጋር አብሮ መጓዝ የግድ አስፈላጊ ያልነበረው ለምንድን ነው?

▪ አንድን ታናሽ ሰው ማሰናከል የሚያስከትለው መዘዝ ምን ያህል ከባድ ነው? ኢየሱስ የእነዚህን ታናናሽ ሰዎች ዋጋማነት በምሳሌ ያስረዳውስ እንዴት ነው?

▪ ኢየሱስ ሐዋርያቱን በመካከላቸው ጨው እንዲኖር ለማበረታታት ያነሳሳው ምን ሊሆን ይችላል?

▪ ‘ማሰር’ እና ‘መፍታት’ የሚሉት ቃሎች ምን ያመለክታሉ?