በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ኒቆዲሞስን አስተማረ

ኒቆዲሞስን አስተማረ

ምዕራፍ 17

ኒቆዲሞስን አስተማረ

ኢየሱስ በ30 እንደ ዘመና​­ችን አቆጣጠር በተከበረው የማለፍ በዓል ላይ ተገኝቶ በነበረበት ጊዜ አስደናቂ ምልክቶች ወይም ተአምራት ፈጽሟል። በዚህም ምክንያት ብዙ ሰዎች በእሱ አመኑ። ሳንሄድሪን የተባለው የአይሁድ ከፍተኛ የፍርድ ሸንጎ አባል የሆነው ኒቆዲሞስ በጣም ስለተደነቀ ይበልጥ ለማወቅ ፈለገ። ስለዚህ ሌሊት ጨለማን ተገን አድርጎ ወደ ኢየሱስ ሄደ። ምናልባትም እንዲህ ያደረገው ከታየሁ በሌሎች የአይሁድ መሪዎች ዘንድ ያለኝን መልካም ስም አጣለሁ የሚል ስጋት አድሮበት ይሆናል።

ኒቆዲሞስ “መምህር ሆይ፣ እግዚአብሔር ከእሱ ጋር ከሆነ በቀር አንተ የምታደርጋቸውን እነዚህን ምልክቶች ሊያደርግ የሚችል የለምና መምህር ሆነህ ከእግዚአብሔር ዘንድ እንደመጣህ እናውቃለን” አለው። ኢየሱስም በምላሹ አንድ ሰው ወደ አምላክ መንግሥት መግባት እንዲችል ‘ዳግም መወለድ’ እንዳለበት ለኒቆዲሞስ ነገረው።

ይሁን እንጂ አንድ ሰው እንዴት ዳግም ሊወለድ ይች⁠ላል? “ሁለተኛ ወደ እናቱ ማኅፀን ገብቶ፤ ይወለድ ዘንድ ይችላልን?” ሲል ኒቆ​­ዲሞስ ጠየቀው።

የለም፤ ዳግም መወለድ ማለት እን​­ደዚያ ማለት አይደለም። “ሰው ከው⁠ኃና ከመንፈስ ካልተወለደ በቀር ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ሊገባ አይችልም” ሲል ኢየሱስ ነገሩን አብራራለት። ኢየሱስ ሲጠመቅና መንፈስ ቅዱስ ሲወርድበት “ከውኃና ከመንፈስ” ተወልዷል። ‘በእርሱ ደስ የሚለኝ ልጄ ይህ ነው’ በሚለው ከዚያ ጋር ተያይዞ በተሰጠው መግለጫ አማካኝነት አምላክ ወደ ሰማያዊ መንግሥት የመግባት ተስፋ ያለው መንፈሳዊ ልጅ እንደወለደ ገለጸ። ከጊዜ በኋላ በ33 እንደ ዘመናችን አቆጣጠር በጰንጠቆስጤ ዕለት ሌሎች የተጠመቁ ሰዎችም መንፈስ ቅዱስ በመቀበል የአምላክ መንፈሳዊ ልጆች ሆነው ዳግም ይወለዳሉ።

ሆኖም የአምላክ ልዩ ሰብዓዊ ልጅ በጣም ወሳኝ የሆነ ሚና ይጫወታል። ኢየሱስ ለኒቆዲሞስ “ሙሴም በምድረ በዳ እባብን እንደ ሰቀለ እንዲሁ በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ የሰው ልጅ ይሰቀል ይገባዋል” አለው። አዎን፣ በመርዘኛ እባቦች ተነድፈው የነበሩት እስራኤላውያን ለመዳን ከነሐስ የተሠራውን እባብ መመልከት እንደነበረባቸው ሁሉ የሰው ልጆችም ከሟችነት ሁኔታቸው ለመዳን በአምላክ ልጅ ማመን አለባቸው።

በዚህ ረገድ ይሖዋ ያሳየውን ፍቅር ጎላ አድርጎ በመግለጽ ኢየሱስ ኒቆዲሞስን እንዲህ አለው:- “በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ እግዚአብሔር አንድያ ልጁን እስኪሰጥ ድረስ ዓለሙን እንዲሁ ወዶአልና።” በዚህ መንገድ ይሖዋ አምላክ የሰው ልጆችን ­ለማዳን የሚጠቀመው በእሱ አማካኝነት መሆኑን ኢየሱስ አገልግሎቱን ­በጀመረ ገና በስድስተኛው ወር እዚያው ኢየሩሳሌም ውስጥ ግልጽ አድርጓል።

በመቀጠልም ኢየሱስ ለኒቆዲሞስ እንዲህ ሲል ገለጸለት:- “ዓለም በልጁ እንዲድን ነው እንጂ፣ በዓለም እንዲፈርድ እግዚአብሔር ወደ ዓለም አልላከውም።” እዚህ ላይ ኢየሱስ፣ አምላክ የላከው በሰው ዘር ላይ የጥፋት ፍርድ እንዲፈርድ አለመሆኑን መግለጹ ነበር።

ኒቆዲሞስ ፈርቶ ስለነበረ ወደ ኢየሱስ የመጣው ጨለማን ተገን አድርጎ ነው። ስለዚህ ኢየሱስ ውይይቱን በሚከተሉት ቃላት መደምደሙ ትኩረትን የሚስብ ነገር ነው:- “ብርሃንም [ኢየሱስ በአኗኗሩና በትምህርቶቹ በሚገባ ያንጸባረቀው ብርሃን ማለት ነው] ወደ ዓለም ስለ መጣ ሰዎችም ሥራቸው ክፉ ነበርና ከብርሃን ይልቅ ጨለማን ስለ ወደዱ ፍርዱ ይህ ነው። ክፉ የሚያደርግ ሁሉ ብርሃንን ይጠላልና፣ ሥራውም እንዳይገለጥ ወደ ብርሃን አይመጣም፤ እውነትን የሚያደርግ ግን ሥራው በእግዚአብሔር ተደርጎ እንደ ሆነ ይገለጥ ዘንድ ወደ ብርሃን ይመጣል።” ዮሐንስ 2:​23 እስከ 3:​21፤ ማቴዎስ 3:​16, 17፤ ሥራ 2:​1-4፤ ዘኍልቁ 21:​9

▪ ኒቆዲሞስ ወደ ኢየሱስ እንዲሄድ ያነሳሳው ምንድን ነው? በሌሊት የሄደውስ ለምንድን ነው?

▪ ‘ዳግም መወለድ’ ማለት ምን ማለት ነው?

▪ ኢየሱስ በእኛ መዳን ረገድ የሚጫወተውን ሚና በምሳሌ ያስረዳው እንዴት ነው?

▪ ኢየሱስ የመጣው በዓለም ላይ ለመፍረድ አይደለም ሲባል ምን ማለት ነው?