በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

አልፎ መሰጠትና መወሰድ

አልፎ መሰጠትና መወሰድ

ምዕራፍ 124

አልፎ መሰጠትና መወሰድ

ጲላጦስ፣ ኢየሱስ ብዙ ሥቃይ ቢደርስበትም እንኳ ያሳየው ግርማ ሞገስ ስሜቱን በጣም ስለነካው እሱን ለማስለቀቅ እንደገና ሙከራ ሲያደርግ የካህናት አለቆቹ ከበፊቱ ይበልጥ ተቆጡ። የክፋት ዓላማቸውን ምንም ነገር እንዳያስተጓጉልባቸው ለመከላከል ቆርጠዋል። ስለዚህ እንደገና “ስቀለው ስቀለው” እያሉ መጮኽ ጀመሩ።

ጲላጦስ “እናንተ ወስዳችሁ ስቀሉት” ሲል መለሰላቸው። (አይሁዶች ቀደም ሲል ከተናገሩት ሐሳብ በተቃራኒ፣ ለሞት የሚያበቃ አንድ ዓይነት ሃይማኖታዊ ጥፋት የፈጸሙ ወንጀለኞችን የማስገደል ሥልጣን ሊኖራቸው ይችላል።) ከዚያም ጲላጦስ ቢያንስ ለአምስተኛ ጊዜ ኢየሱስ ንጹሕ መሆኑን በመግለጽ “እኔስ አንዲት በደል ስንኳ አላገኘሁበትም” አላቸው።

አይሁዶቹ የሰነዘሯቸው የፖለቲካ ክሶች ምንም ውጤት እንዳላስገኙ በመገንዘብ ከተወሰኑ ሰዓታት በፊት ኢየሱስ በሳንሄድሪን ችሎት ፊት ቀርቦ በነበረ ጊዜ ተጠቅመውበት የነበረውን አምላክን ተሳድቧል የሚለውን ሃይማኖታዊ ክሳቸውን እንደገና አነሱ። “እኛ ሕግ አለን፣ እንደ ሕጋችንም ሊሞት ይገባዋል፣ ራሱን የእግዚአብሔር ልጅ አድርጎአልና” አሉ።

ይህ ክስ ለጲላጦስ አዲስ ከመሆኑም በላይ ይበልጥ እንዲፈራ አደረገው። ጲላጦስ አሁን ኢየሱስ ተራ ሰው አለመሆኑን ተገነዘበ፤ የሚስቱ ሕልምና ኢየሱስ ያሳየው አስደናቂ የመንፈስ ጥንካሬም ይህን የሚያመለክት ነበር። ግን እንዴት “የእግዚአብሔር ልጅ” ሊሆን ይችላል? ጲላጦስ ኢየሱስ የገሊላ ሰው መሆኑን ያውቃል። ሆኖም ምናልባት ከዚያ በፊት በሕይወት ይኖር የነበረ ሰው ይሆን? ጲላጦስ እንደገና ወደ ቤተ መንግሥቱ ይዞት ገባና “አንተ ከወዴት ነህ?” ሲል ጠየቀው።

ኢየሱስ መልስ አልሰጠም። ኢየሱስ ንጉሥ እንደሆነ፣ ሆኖም መንግሥቱ ከዚህ ዓለም እንዳልሆነ ቀደም ሲል ለጲላጦስ ነግሮታል። አሁን ሌላ ተጨማሪ ማብራሪያ መስጠቱ ምንም ፋይዳ የለውም። ይሁን እንጂ ጲላጦስ ኢየሱስ መልስ አለመስጠቱ ክብሩን ዝቅ እንዳደረገበት ሆኖ ስለተሰማው ድንገት ግንፍል ብሎ “አትነግረኝምን? ልሰቅልህ ሥልጣን እንዳለኝ ወይም ልፈታህ ሥልጣን እንዳለኝ አታውቅምን?” አለው።

ኢየሱስ “ከላይ ካልተሰጠህ በቀር በእኔ ላይ ምንም ሥልጣን ባልነበረህም” በማለት በአክብሮት መለሰለት። ኢየሱስ ምድራዊ ጉዳዮችን እንዲያስተዳድሩ አምላክ ለሰብዓዊ ገዥዎች የሰጠውን ሥልጣን መጥቀሱ ነበር። ኢየሱስ “ስለዚህ ለአንተ አሳልፎ የሰጠኝ ኃጢአቱ የባሰ ነው” ሲል አክሎ ተናገረ። በእርግጥም ሊቀ ካህናቱ ቀያፋና ግብረ አበሮቹ እንዲሁም የአስቆሮቱ ይሁዳ በኢየሱስ ላይ ለደረሰው ኢሰብዓዊ ድርጊት ከጲላጦስ የበለጠ ከባድ ኃላፊነት አለባቸው።

ጲላጦስ ከበፊቱ ይበልጥ በኢየሱስ በመደነቅና መለኮታዊ አመጣጥ ሊኖረው ይችላል ብሎ በመስጋት እሱን ለማስለቀቅ እንደገና ጥረት ማድረግ ጀመረ። ይሁን እንጂ አይሁዶቹ ጲላጦስን አልተቀበሉትም። የፖለቲካ ክሳቸውን በድጋሚ በማንሳት እንዲህ ሲሉ በተንኮል አስፈራሩት:- “ይህንስ ብትፈታው የቄሣር ወዳጅ አይደለህም፤ ራሱን ንጉሥ የሚያደርግ ሁሉ የቄሣር ተቃዋሚ ነው።”

ምንም እንኳ ሁኔታው መጥፎ ትርጉም ሊያሰጥ የሚችል ቢሆንም ጲላጦስ ዳግመኛ ኢየሱስን ወደ ውጪ አወጣው። “እነሆ ንጉሣችሁ” በማለት አሁንም ሕዝቡን ለማግባባት ሞከረ።

“አስወግደው፣ አስወግደው፣ ስቀለው” አሉ።

ጲላጦስ ተስፋ በመቁረጥ “ንጉሣችሁን ልስቀለውን?” ሲል ጠየቃቸው።

አይሁዶች የሮማውያን አገዛዝ አስመርሯቸዋል። እንዲያውም የሮምን አገዛዝ በጣም ጠልተውታል! ሆኖም የካህናት አለቆቹ በግብዝነት “ከቄሣር በቀር ሌላ ንጉሥ የለንም” አሉ።

ጲላጦስ ለፖለቲካ ሥልጣኑና ለስሙ በመስጋት በመጨረሻ አይሁዶች ያለማቋረጥ ያሰሙት ለነበረው ጥያቄ ተንበረከከ። ኢየሱስን አሳልፎ ሰጣቸው። ወታደሮቹ ሐምራዊውን ጨርቅ ከኢየሱስ ላይ አወለቁና የራሱን ልብስ አለበሱት። ኢየሱስ ሊሰቀል ሲወሰድ የራሱን የመከራ እንጨት እንዲሸከም ተደረገ።

አሁን ዕለቱ ዓርብ ኒሳን 14 ሲሆን የጠዋቱ ክፍለ ጊዜ ተጋምሷል፤ ምናልባትም ወደ እኩለ ቀን እየተቃረበ ሳይሆን አይቀርም። ኢየሱስ ከሐሙስ ማለዳ ጀምሮ አልተኛም፤ በተጨማሪም ሥቃይ ሲፈራረቅበት ቆይቷል። ስለዚህ የተሸከመው እንጨት ከጥቂት ጊዜ በኋላ ኃይሉን ሁሉ እንደሚያሟጥጠው ግልጽ ነው። ስለዚህ በአፍሪካ ውስጥ ከምትገኘው ከቀሬና የመጣ አንድ ስምዖን የተባለ መንገደኛ በዚያ ሲያልፍ እንጨቱን እንዲሸከምለት አስገደዱት። ጉዞአቸውን ሲቀጥሉ ለኢየሱስ ዋይ ዋይ የሚሉና ሙሾ የሚያወጡ ሴቶችን ጨምሮ ብዙ ሰዎች ተከተሏቸው።

ኢየሱስ ወደ ሴቶቹ ዞረና እንዲህ አላቸው:- “እናንተ የኢየሩሳሌም ልጆች፣ ለእኔስ አታልቅሱልኝ፤ ዳሩ ግን:- መካኖችና ያልወለዱ ማኅፀኖች ያላጠቡ ጡቶችም ብፁዓን [“ደስተኞች፣” NW] ናቸው የሚሉበት ጊዜ እነሆ ይመጣልና ለራሳችሁና ለልጆቻችሁ አልቅሱ። . . . በእርጥብ እንጨት እንዲህ የሚያደርጉ ከሆኑ፣ በደረቀውስ እንዴት ይሆን?”

ኢየሱስ እሱ እዚያ በመገኘቱና በእሱ የሚያምኑ ጥቂት ቀሪዎች በመኖራቸው የተነሳ ትንሽ የሕይወት እርጥበት ሊኖረው ስለቻለው የአይሁድን ሕዝብ ስለሚያመለክተው ዛፍ መናገሩ ነበር። ሆኖም እነዚህ ሰዎች ከሕዝቡ መካከል በሚወጡበት ጊዜ በመንፈሳዊ የሞተ ዛፍ ማለትም የደረቀ ብሔራዊ ኅብረተሰብ ብቻ ይቀራል። የሮማ ሠራዊት የአምላክ ፍርድ አስፈጻሚ ሆኖ የአይሁድን ሕዝብ በሚያጠፋበት ጊዜ እንዴት ያለ ሐዘን ይሆናል! ዮሐንስ 19:​6-17፤ 18:​31፤ ሉቃስ 23:​24-31፤ ማቴዎስ 27:​31, 32፤ ማርቆስ 15:​20, 21

▪ የሃይማኖት መሪዎቹ በኢየሱስ ላይ ያነሷቸው ፖለቲካዊ ክሶች ምንም ውጤት ሳያስገኙ ሲቀሩ ምን ክስ አቀረቡ?

▪ ጲላጦስ ከበፊቱ የበለጠ ፍርሃት ያደረበት ለምንድን ነው?

▪ በኢየሱስ ላይ ለደረሰው ነገር ይበልጥ ኃጢአቱን የሚሸከመው ማን ነው?

▪ ካህናቱ በመጨረሻ ጲላጦስ ኢየሱስን ለሞት አሳልፎ እንዲሰጥ ያደረጉት እንዴት ነው?

▪ ኢየሱስ ያለቀሱለትን ሴቶች ምን አላቸው? ስለ ዛፉ “እርጥብ” መሆን ከዚያም ‘መድረቅ’ ሲናገር ምን ማመልከቱ ነበር?