በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

አስፈሪ ማዕበል ጸጥ ማሰኘት

አስፈሪ ማዕበል ጸጥ ማሰኘት

ምዕራፍ 44

አስፈሪ ማዕበል ጸጥ ማሰኘት

ኢየሱስ ቀኑን ያሳለፈው በሥራ ተወጥሮ ነበር። ይህም በባሕሩ ዳርቻ የነበሩትን ብዙ ሕዝብ ማስተማርንና ከዚያም በኋላ ምሳሌዎቹን በግል ለደቀ መዛሙርቱ ማብራራትን ያካተተ ነበር። ቀኑ ሲመሽ “ወደ ማዶ እንሻገር አላቸው።”

ከገሊላ ባሕር በስተ ምሥራቅ በኩል ባለው ዳርቻ ዲካፖሊስ የሚባል ክልል አለ። ይህ ቃል የመጣው “አሥር” የሚል ትርጉም ካለው ዲካ ከተባለው የግሪክኛ ቃልና “ከተማ” የሚል ትርጉም ካለው ፖሊስ ከተባለው የግሪክኛ ቃል ነው። የዲካፖሊስ ከተሞች የብዙ አይሁዳውያን መኖሪያ ቢሆኑም እንኳ የግሪክ ባሕል ማዕከል ነበሩ። ይሁን እንጂ ኢየሱስ በዚህ ክልል ያደረገው እንቅስቃሴ በጣም ውስን ነበር። ቆየት ብለን እንደምንመለከተው በዚህኛው ጉብኝቱ ወቅት እንኳ ለረጅም ጊዜ ሊቆይ አልቻለም።

ኢየሱስ ወደ ሌላኛው የባሕሩ ዳርቻ እንሂድ ሲላቸው ደቀ መዛሙርቱ ጀልባቸው ላይ አሳፈሩት። ይሁን እንጂ ሕዝቡ አካባቢውን ለቅቀው ሊሄዱ እንደሆነ ተገንዝቦ ነበር። ብዙም ሳይቆይ ሌሎች በጀልባዎቻቸው ላይ ተሳፍረው አብረዋቸው መጓዝ ጀመሩ። ጉዞው በጣም ረጅም አልነበረም። የገሊላ ባሕር 21 ኪሎ ሜትር ገደማ ርዝመት ያለውና በዛ ቢባል 12 ኪሎ ሜትር ስፋት ያለው አንድ ትልቅ ሐይቅ ነው።

ኢየሱስ እንደደከመው አያጠራጥርም። ስለዚህ መቅዘፍ ከጀመሩ በኋላ ብዙም ሳይቆይ በጀልባዋ በስተጀርባ በኩል ትራስ ተንተርሶ ተኛና ከባድ እንቅልፍ ወሰደው። በርከት ያሉት ሐዋርያት በገሊላ ባሕር ላይ በብዛት ዓሣ ያጠምዱ የነበሩ ልምድ ያላቸው መርከበኞች ነበሩ። ስለዚህ ጀልባዋን የመቅዘፉን ኃላፊነት ወስደው ነበር።

ሆኖም ይህ ጉዞ ቀላል አልነበረም። ከባሕር ወለል በታች 213 ሜትር ገደማ ዝቅ ብሎ የሚገኘው የሐይቁ የላይኛው ክፍል ባለው ሞቃታማ የአየር ንብረትና በአቅራቢያ በሚገኙት ተራሮች ላይ ባለው ቀዝቃዛ አየር ምክንያት አንዳንድ ጊዜ ኃይለኛ ንፋስ ይነፍስና በሐይቁ ላይ በድንገት ኃይለኛ ማዕበል እንዲፈጠር ያደርጋል። በዚህ ጊዜም የተከሰተው ይኸው ነበር። ብዙም ሳይቆይ የባሕሩ ሞገድ ከጀልባዋ ጋር እየተጋጨ ጀልባዋ ውስጥ መግባት ሲጀምር ጀልባዋ ልትሰምጥ ደረሰች። ኢየሱስ ግን አሁንም እንደተኛ ነበር!

ልምድ ያካበቱት ባሕረተኞች ጀልባዋን ለመቅዘፍ ባለ በሌለ ኃይላቸው መታገል ጀመሩ። ከዚህ ቀደም በማዕበል ውስጥ በተሳካ ሁኔታ ቀዝፈው የወጡበት ጊዜ እንደሚኖር ምንም ጥርጥር የለውም። አሁን ግን ሁሉ ነገር ከአቅማቸው በላይ ሆነ። ሕይወታቸው እንዳይጠፋ በመስጋት ኢየሱስን ቀሰቀሱት። ‘መምህር ሆይ፣ ዝም ትላለህ? እየሰመጥን እኮ ነው!’ ሲሉ ጮኹ። ‘አድነን፤ ልንሰምጥ ነው!’

ኢየሱስ ተነሳና ነፋሱንና ባሕሩን “ዝም በል፣ ፀጥ በል” ብሎ አዘዘው። ዓውሎ ነፋሱ ቆመ፤ ባሕሩም ፀጥ አለ። ወደ ደቀ መዛሙርቱ ዞረና ‘ይህን ያህል የፈራችሁት ለምንድን ነው? አሁንም ምንም እምነት የላችሁም ማለት ነው?’ ሲል ጠየቃቸው።

በዚህ ጊዜ ደቀ መዛሙርቱ ከዚህ በፊት ተሰምቷቸው የማያውቅ ዓይነት ፍርሃት አደረባቸው። ‘ይህ ሰው ማን ነው?’ ብለው እርስ በርሳቸው ተጠያየቁ። ‘ነፋስንና ባሕርን እንኳ ሳይቀር ያዝዛል፤ እነርሱም ይታዘዙለታል።’

ኢየሱስ እንዴት ያለ ታላቅ ኃይል አሳይቷል! ንጉሣችን በተፈጥሮ ኃይሎች ላይ ሥልጣን እንዳለውና በመንግሥቱ አገዛዝ ወቅት ሙሉ ትኩረቱን ወደ ምድራችን በሚያደርግበት ጊዜ ሁሉም ሰዎች አስፈሪ ከሆኑ የተፈጥሮ አደጋዎች ተጠብቀው ያለ ሥጋት እንደሚኖሩ ማወቁ ምንኛ የሚያጽናና ነው!

ማዕበሉ ካቆመ ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ኢየሱስና ደቀ መዛሙርቱ ወደ ምሥራቃዊው የባሕሩ ዳርቻ በሰላም ደረሱ። ሌሎቹ ጀልባዎችም ምናልባት ከኃይለኛው ማዕበል ተርፈው በደህና ወደ ቤታቸው ተመልሰው ይሆናል። ማርቆስ 4:​35 እስከ 5:​1፤ ማቴዎስ 8:​18, 23-27፤ ሉቃስ 8:​22-26

ዲካፖሊስ ምንድን ነው? የሚገኘውስ የት ነው?

▪ በገሊላ ባሕር ላይ ኃይለኛ ማዕበል እንዲከሰት የሚያደርጉ አንዳንድ ተፈጥሮአዊ ሁኔታዎች ምንድን ናቸው?

▪ ደቀ መዛሙርቱ የመርከበኝነት ችሎታቸው ሊያድናቸው ሳይችል ሲቀር ምን አደረጉ?