በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

አንዲት ሳምራዊት ሴት አስተማረ

አንዲት ሳምራዊት ሴት አስተማረ

ምዕራፍ 19

አንዲት ሳምራዊት ሴት አስተማረ

ኢየሱስና ደቀ መዛሙርቱ ከይሁዳ ወደ ገሊላ ሲመለሱ በሰማርያ አውራጃ በኩል አለፉ። ጉዞው ስላደከማቸው እኩለ ቀን ገደማ ላይ ሲካር በምትባል ከተማ አቅራቢያ በአንድ የውኃ ጉድጓድ አጠገብ አረፉ። ይህ ጉድጓድ ከብዙ መቶ ዘመናት በፊት ያዕቆብ የቆፈረው ሲሆን እስከ አሁንም ድረስ ናብለስ ተብላ በምትጠራው ዘመናዊ ከተማ አቅራቢያ ይገኛል።

ኢየሱስ በዚህ ስፍራ አረፍ ሲል ደቀ መዛሙርቱ ምግብ ለመግዛት ወደ ከተማይቱ ሄዱ። አንዲት ሳምራዊት ሴት ውኃ ለመቅዳት ስትመጣ “ውኃ አጠጪኝ” ብሎ ጠየቃት።

በመካከላቸው በነበረው ሥር የሰደደ ወገናዊ ጥላቻ ምክንያት አይሁዶች ከሳምራውያን ጋር ምንም ዓይነት ግንኙነት አልነበራቸውም። ስለዚህ ሴትዮዋ በመገረም “አንተ የይሁዳ ሰው ስትሆን ሳምራዊት ሴት ከምሆን ከእኔ መጠጥ እንዴት ትለምናለህ?” ብላ ጠየቀችው።

ኢየሱስም “ውኃ አጠጪኝ የሚልሽ ማን መሆኑንስ ብታውቂ፣ አንቺ ትለምኚው ነበርሽ የሕይወትም ውኃ ይሰጥሽ ነበር” አላት።

እርሷም “ጌታ ሆይ፣ መቅጃ የለህም ጉድጓዱም ጥልቅ ነው፤ እንግዲህ የሕይወት ውኃ ከወዴት ታገኛለህ? በእውኑ አንተ ይህን ጉድጓድ ከሰጠን ከአባታችን ከያዕቆብ ትበልጣለህን? ራሱም ልጆቹም ከብቶቹም ከዚህ ጠጥተዋል” አለችው።

ኢየሱስ “ከዚህ ውኃ የሚጠጣ ሁሉ እንደ ገና ይጠማል” አላት። “እኔ ከምሰጠው ውኃ የሚጠጣ ሁሉ ግን ለዘላለም አይጠማም፣ እኔ የምሰጠው ውኃ በእርሱ ውስጥ ለዘላለም ሕይወት የሚፈልቅ የውኃ ምንጭ ይሆናል እንጂ” ሲል ገለጸላት።

ሴትዮዋም መልሳ “ጌታ ሆይ፣ እንዳልጠማ ውኃም ልቀዳ ወደዚህ እንዳልመጣ ይህን ውኃ ስጠኝ” አለችው።

በዚህ ጊዜ ኢየሱስ “ሂጂና ባልሽን ጠርተሽ ወደዚህ ነዪ” አላት።

“ባል የለኝም” ብላ መለሰችለት።

ኢየሱስ የተናገረችው ትክክል መሆኑን ተናገረ። “ባል የለኝም በማለትሽ መልካም ተናገርሽ፤ አምስት ባሎች ነበሩሽና፣ አሁን ከአንቺ ጋር ያለው ባልሽ አይደለም።”

ሴትዮዋ በመገረም “ጌታ ሆይ፣ አንተ ነቢይ እንደ ሆንህ አያለሁ” አለችው። ከዚያም ሳምራውያን “በዚህ ተራራ [በአቅራቢያቸው በሚገኘው በገሪዛን ተራራ] ሰገዱ፤ እናንተም [አይሁዳውያን]:- ሰው ሊሰግድበት የሚገባው ስፍራ በኢየሩሳሌም ነው ትላላችሁ” በማለት ለመንፈሳዊ ነገሮች ፍላጎት ያላት መሆኑን ገለጸች።

ሆኖም ኢየሱስ ትልቁ ነገር የአምልኮ ሥፍራው እንዳልሆነ ገለጸላት። እንዲህ አለ:- “በእውነት የሚሰግዱ ለአብ በመንፈስና በእውነት የሚሰግዱበት ጊዜ ይመጣል አሁንም ሆኖአል፤ አብ ሊሰግዱለት እንደ እነዚህ ያሉትን ይሻልና፤ እግዚአብሔር መንፈስ ነው፣ የሚሰግዱለትም በመንፈስና በእውነት ሊሰግዱለት ያስፈልጋቸዋል።”

ሴትዮዋ በጣም ተደነቀች። “ክርስቶስ የሚባል መሲሕ እንዲመጣ አውቃለሁ፤ እርሱ ሲመጣ ሁሉን ይነግረናል” አለችው።

ኢየሱስ “የምናገርሽ እኔ እርሱ ነኝ” ሲል ገለጸላት። እስቲ አስበው! ይህች ሴት ውኃ ለመቅዳት እኩለ ቀን ላይ የመጣችው ምናልባት በአኗኗሯ ምክንያት ከሚንቋት የከተማው ሴቶች ጋር ላለመገናኘት ሊሆን ይችላል፤ ኢየሱስ ግን በጥሩ ሁኔታ ተቀብሎ አነጋገራት። ለሌላ ለማንም በግልጽ ያልተናገረውን ነገር ለእሷ በቀጥታ ነገራት። ይህስ ምን ውጤት አስገኘ?

ብዙ ሳምራውያን አመኑ

ደቀ መዛሙርቱ ምግብ ገዝተው ከሲካር ሲመለሱ ኢየሱስ እነሱ ሲሄዱ ተቀምጦበት በነበረው በዚያው በያዕቆብ የውኃ ጉድጓድ አጠገብ ከአንዲት ሳምራዊት ሴት ጋር ሲነጋገር አገኙት። ደቀ መዛሙርቱ ሲመጡ ሴትዮዋ የውኃ እንስራዋን እዚያው ትታ ወደ ከተማ ሄደች።

ኢየሱስ የነገራት ነገር ስሜቷን በጣም ስለማረከው ለከተማይቱ ሰዎች “ያደረግሁትን ሁሉ የነገረኝን ሰው ኑና እዩ” አለቻቸው። ከዚያም የማወቅ ጉጉት በሚያሳድር አነጋገር “እንጃ እርሱ ክርስቶስ ይሆንን?” ብላ ጠየቀቻቸው። ጥያቄው የተፈለገውን ግብ መትቷል፤ ሰዎቹ ራሳቸው ለማየት ሄዱ።

ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ ደቀ መዛሙርቱ ከከተማ ያመጡትን ምግብ ኢየሱስ እንዲበላ ለመኑት። ኢየሱስ ግን “እናንተ የማታውቁት የምበላው መብል ለእኔ አለኝ” ሲል መለሰላቸው።

ደቀ መዛሙርቱ “የሚበላው አንዳች ሰው አምጥቶለት ይሆንን?” ብለው እርስ በርሳቸው ተጠያየቁ። ኢየሱስ እንዲህ ሲል ገለጸላቸው:- “የእኔስ መብል የላከኝን ፈቃድ አደርግ ዘንድ ሥራውንም እፈጽም ዘንድ ነው። እናንተ:- ገና አራት ወር ቀርቶአል መከርም ይመጣል ትሉ የለምን?” ይሁን እንጂ ኢየሱስ መንፈሳዊውን መከር አስመልክቶ እንዲህ አለ:- “ዓይናችሁን አንሡ አዝመራውም አሁን እንደ ነጣ እርሻውን ተመልከቱ። የሚያጭድ ደመወዝን ይቀበላል፣ የሚዘራና የሚያጭድም አብረው ደስ እንዲላቸው ለዘላለም ሕይወት ፍሬን ይሰበስባል።”

ምናልባት ኢየሱስ ከሳምራዊቷ ሴት ጋር መገናኘቱ ታላቅ ውጤት እንደሚያስገኝና በሴትዮዋ ምሥክርነት ብዙ ሰዎች በእሱ እንደሚያምኑ ከወዲሁ አስተውሎ ይሆናል። ሴትዮዋ ለከተማይቱ ሰዎች “ያደረግሁትን ሁሉ ነገረኝ” ብላ መሥክራላቸው ነበር። ስለዚህ የሲካር ሰዎች እሱ ወዳለበት ወደ ውኃው ጉድጓድ ሲመጡ ከእነርሱ ጋር እንዲቆይና ተጨማሪ ነገር እንዲነግራቸው ለመኑት። ኢየሱስ ግብዣውን ተቀብሎ ሁለት ቀን ቆየ።

ሳምራውያን የኢየሱስን ቃል ሲሰሙ ሌሎች ብዙ ሰዎችም አመኑ። ከዚያም ሴትዮዋን እንዲህ አሏት:- “አሁን የምናምን ስለ ቃልሽ አይደለም፣ እኛ ራሳችን ሰምተነዋልና፤ እርሱም በእውነት ክርስቶስ የዓለም መድኃኒት እንደ ሆነ እናውቃለን።” በእርግጥም ሳምራዊቷ ሴት ሰዎች ተጨማሪ ነገር ለማወቅ እንዲነሳሱ በውስጣቸው ጉጉት በመቀስቀስ እንዴት ስለ ክርስቶስ መመሥከር እንደምንችል የሚያሳይ ጥሩ ምሳሌ ትታልናለች!

ይህ የሆነው የአጨዳ (የገብስ አጨዳ) ወቅት ከመድረሱ ከአራት ወር በፊት እንደሆነ አስታውስ። በፍልስጤም ምድር የገብስ አጨዳ የሚካሄደው በጸደይ ወራት ነበር። ስለዚህ ይህ የሆነው በኅዳር ወይም በታኅሣሥ ወር ላይ ሳይሆን አይቀርም። ይህ ማለት ኢየሱስና ደቀ መዛሙርቱ በ30 እንደ ዘመናችን አቆጣጠር ከተከበረው የማለፍ በዓል በኋላ በይሁዳ እያስተማሩና እያጠመቁ ስምንት ወር ገደማ አሳልፈዋል ማለት ነው። አሁን መኖሪያቸው ወደሆነው ወደ ገሊላ እየተመለሱ ነው። እዚያ ምን ያጋጥማቸው ይሆን? ዮሐንስ 4:​3-43

▪ ሳምራዊቷ ሴት ኢየሱስ እሷን በማነጋገሩ የተደነቀችው ለምንድን ነው?

▪ ኢየሱስ የሕይወት ውኃንና የአምልኮ ቦታን በተመለከተ ምን አስተማራት?

▪ ኢየሱስ ማን መሆኑን የገለጸላት እንዴት ነው? በዚህ መንገድ ራሱን መግለጹስ የሚያስደንቀው ለምንድን ነው?

▪ ሳምራዊቷ ሴት ምን ምሥክርነት ሰጠች? ይህስ ምን ውጤት አስገኘ?

▪ የኢየሱስ ምግብ ከመከሩ ጋር የተያያዘው እንዴት ነው?

▪ ኢየሱስ በ30 እንደ ዘመናችን አቆጣጠር ከተከበረው የማለፍ በዓል በኋላ በይሁዳ በማገልገል ያሳለፈው ጊዜ ምን ያህል እንደሆነ ማስላት የምንችለው እንዴት ነው?