በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

አንድ የሠራዊት አለቃ ያሳየው ትልቅ እምነት

አንድ የሠራዊት አለቃ ያሳየው ትልቅ እምነት

ምዕራፍ 36

አንድ የሠራዊት አለቃ ያሳየው ትልቅ እምነት

ኢየሱስ የተራራ ስብከቱን በሰጠበት ወቅት ሕዝባዊ አገልግሎት የሚያከናውንበትን ጊዜ ወደ ማጋመሱ ተቃርቦ ነበር። ይህ ማለት ኢየሱስ በምድር ላይ የሚያከናውነውን ሥራ ለመፈጸም የቀረው ጊዜ አንድ ዓመት ከዘጠኝ ወር ገደማ ብቻ ነበር ማለት ነው።

አሁን ኢየሱስ እንደ መኖሪያና የሥራው ማዕከል ሆና ወደምታገለግለው ወደ ቅፍርናሆም ከተማ ገባ። እዚያም አይሁዳውያን ሽማግሌዎች ወደ እሱ ቀረቡና አንድ ነገር ለመኑት። እነዚህ ሰዎች አንድ አይሁዳዊ ያልሆነና ከአሕዛብ ወገን የተወለደ የሮማ ሠራዊት አለቃ የላካቸው ሰዎች ነበሩ።

የሠራዊቱ አለቃ በጣም የሚወደው አገልጋዩ በጠና ታሞ በሞት አፋፍ ላይ ስለነበር ኢየሱስ አገልጋዩን እንዲፈውስለት ፈልጎ ነበር። አይሁዶቹ “ይህን ልታደርግለት ይገባዋል፤ ሕዝባችንን ይወዳልና ምኩራብም ራሱ ሠርቶልናል” ብለው ለሠራዊቱ አለቃ አጥብቀው ለመኑለት።

ኢየሱስ ያላንዳች ማመንታት ሰዎቹን ተከትሎ ሄደ። ይሁን እንጂ ወደ ቤቱ አቅራቢያ ሲደርሱ የሠራዊቱ አለቃ እንዲህ ብለው እንዲነግሩት ጓደኞቹን ላካቸው:- “ጌታ ሆይ፣ በቤቴ ጣራ በታች ልትገባ አይገባኝምና አትድከም፤ ስለዚህም ወደ አንተ ልመጣ እንዲገባኝ ሰውነቴን አልቆጠርሁትም።”

ሌሎችን ማዘዝ የለመደ አንድ የሠራዊት አለቃ እንዲህ ብሎ የተናገረው ምን ያህል ትሑት ቢሆን ነው! ሆኖም ባህሉ አንድ አይሁዳዊ፣ አይሁዳውያን ካልሆኑ ሰዎች ጋር ማኅበራዊ ግንኙነት እንዳያደርግ የሚከለክል መሆኑን ተገንዝቦ ለኢየሱስ በማሰብ ያደረገውም ሊሆን ይችላል። ጴጥሮስም እንኳ “አይሁዳዊ ሰው ከሌላ ወገን ጋር ይተባበር ወይም ይቃረብ ዘንድ እንዳልተፈቀደ እናንተ ታውቃላችሁ” ብሏል።

የሠራዊቱ አለቃ ኢየሱስ ይህን ልማድ በመጣስ ችግር ውስጥ እንዳይገባ ያሰበለት ይመስላል። ስለዚህ የሚከተለውን ልመና እንዲያቀርቡለት ጓደኞቹን ላካቸው:- “ቃል ተናገር፣ ብላቴናዬም ይፈወሳል። እኔ ደግሞ ከሌሎች በታች የምገዛ ሰው ነኝ፣ ከእኔም በታች ወታደሮች አሉኝ፣ አንዱንም:- ሂድ ብለው ይሄዳል፣ ሌላውንም:- ና ብለው ይመጣል፣ ባሪያዬንም:- ይህን አድርግ ብለው ያደርጋል።”

ኢየሱስ ይህን ሲሰማ በጣም ተደነቀ። “እላችኋለሁ፣ በእስራኤልስ እንኳ እንዲህ ያለ ትልቅ እምነት አላገኘሁም” አላቸው። ኢየሱስ የሠራዊቱን አለቃ አገልጋይ ከፈወሰ በኋላ እምነት ያሳዩ አይሁዳውያን ያልሆኑ ሰዎች እምነተ ቢስ የሆኑት አይሁዳውያን አንፈልግም ያሉትን በረከት እንደሚያገኙ ለመግለጽ አጋጣሚውን ተጠቀመበት።

ኢየሱስ እንዲህ አለ:- “ብዙዎች ከምሥራቅና ከምዕራብ ይመጣሉ ከአብርሃምና ከይስሐቅ ከያዕቆብም ጋር በመንግሥተ ሰማያት ይቀመጣሉ፤ የመንግሥት ልጆች ግን በውጭ ወደ አለው ጨለማ ይጣላሉ፤ በዚያ ልቅሶና ጥርስ ማፋጨት ይሆናል።”

‘በውጭ ወዳለው ጨለማ የሚጣሉት የመንግሥት ልጆች’ መጀመሪያ ለእነሱ የቀረበውን ከክርስቶስ ጋር የመግዛት አጋጣሚ ያልተቀበሉ ሥጋዊ አይሁዶች ናቸው። አብርሃም፣ ይስሐቅና ያዕቆብ የአምላክን መንግሥታዊ ዝግጅት ይወክላሉ። ኢየሱስ አሕዛብ “በመንግሥተ ሰማያት” በሰማያዊ ማዕድ ዙሪያ የመቀመጥ አጋጣሚ የሚያገኙት እንዴት እንደሆነ በዚህ መንገድ ገልጿል። ሉቃስ 7:​1-10፤ ማቴዎስ 8:​5-13፤ ሥራ 10:​28

▪ አይሁዳውያን ከአሕዛብ ወገን የሆነን አንድ የሠራዊት አለቃ ወክለው ልመና ያቀረቡት ለምንድን ነው?

▪ የሠራዊቱ አለቃ ኢየሱስ ወደ ቤቱ እንዲገባ ያላደረገበትን ምክንያት ሊገልጽልን የሚችለው ነገር ምንድን ነው?

▪ ኢየሱስ መደምደሚያ ላይ የሰጠውን ሐሳብ ሲናገር ምን ማለቱ ነበር?