በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

አንድ ፈሪሳዊ ቤት ተጋበዘ

አንድ ፈሪሳዊ ቤት ተጋበዘ

ምዕራፍ 83

አንድ ፈሪሳዊ ቤት ተጋበዘ

ኢየሱስ አሁንም ያለው በአንድ የታወቀ ፈሪሳዊ ቤት ነው፤ ድሮፕሲ በተባለው በሽታ ይሠቃይ የነበረውን ሰው የፈወሰው ከጥቂት ጊዜ በፊት ነው። ሌሎቹ ተጋባዥ እንግዶች በግብዣው ላይ የከበሬታን ቦታ ሲመርጡ በማየቱ ስለ ትሕትና ትምህርት ሰጠ።

ኢየሱስ እንዲህ ሲል ገለጸ:- “ማንም ለሰርግ ቢጠራህ በከበሬታ ስፍራ አትቀመጥ፤ ምናልባት ከአንተ ይልቅ የከበረ ተጠርቶ ይሆናልና አንተን እርሱንም የጠራ መጥቶ:- ለዚህ ስፍራ ተውለት ይልሃል፣ በዚያን ጊዜም እያፈርህ በዝቅተኛው ስፍራ ልትሆን ትጀምራለህ።”

ስለዚህ ኢየሱስ የሚከተለውን ምክር ሰጠ:- “በተጠራህ ጊዜ፣ የጠራህ መጥቶ:- ወዳጄ ሆይ፣ ወደ ላይ ውጣ እንዲልህ፣ ሄደህ በዝቅተኛው ስፍራ ተቀመጥ፤ ያን ጊዜም ከአንተ ጋር በተቀመጡት ሁሉ ፊት ክብር ይሆንልሃል።” ኢየሱስ ሲደመድም እንዲህ አለ:- “ራሱን ከፍ የሚያደርግ ሁሉ ይዋረዳልና፣ ራሱንም የሚያዋርድ ከፍ ይላል።”​— ጋደል አድርገን የጻፍነው እኛ ነን።

ከዚህ በመቀጠል ኢየሱስ በአምላክ ዘንድ እውነተኛ ዋጋ የሚያስገኝ ግብዣ ማድረግ የሚቻለው እንዴት እንደሆነ ለጋበዘው ፈሪሳዊ ነገረው። “ምሳ ወይም እራት ባደረግህ ጊዜ፣ እነርሱ ደግሞ በተራቸው ምናልባት እንዳይጠሩህ ብድራትም እንዳይመልሱልህ፣ ወዳጆችህንና ወንድሞችህን ዘመዶችህንም ባለ ጠጎች ጎረቤቶችህንም አትጥራ። ነገር ግን ግብዣ ባደረግህ ጊዜ ድሆችንና ጕንድሾችን አንካሶችንም ዕውሮችንም ጥራ፤ የሚመልሱት ብድራት የላቸውምና ብፁዕ [“ደስተኛ፣” NW] ትሆናለህ።”

ከባድ ችግር ያለባቸውን ሰዎች እንዲህ ዓይነት ግብዣ መጋበዝ ለጋባዡ ደስታ ያመጣለታል። ኢየሱስ ምክንያቱን ለጋበዘው ሰው ሲገልጽ “በጻድቃን ትንሣኤ ይመለስልሃልና” ብሏል። ኢየሱስ የገለጸው ይህ ዋጋ የሚያሰጥ ግብዣ ከተጋበዙት እንግዶች መካከል አንዱ ሌላ ዓይነት ግብዣ እንዲያስታውስ አደረገው። “በእግዚአብሔር መንግሥት እንጀራ የሚበላ ብፁዕ [“ደስተኛ፣” NW] ነው” ሲል ተጋባዡ ተናገረ። ሆኖም ቀጥሎ ኢየሱስ በአንድ ምሳሌ ላይ እንዳመለከተው ይህን አስደሳች ተስፋ ከፍ አድርገው የሚመለከቱት ሁሉም አይደሉም።

“አንድ ሰው ታላቅ እራት አድርጎ ብዙዎችን ጠራ፤ . . . የታደሙትን:- አሁን ተዘጋጅቶአልና ኑ እንዲላቸው ባሪያውን ላከ። ሁላቸውም በአንድነት ያመካኙ ጀመር። የፊተኛው:- መሬት ገዝቼአለሁ ወጥቼም ላየው በግድ ያስፈልገኛል ይቅር እንድትለኝ እለምንሃለሁ አለው። ሌላውም:- አምስት ጥምድ በሬዎች ገዝቼአለሁ ልፈትናቸውም እሄዳለሁ፤ ይቅር እንድትለኝ እለምንሃለሁ አለው። ሌላውም:- ሚስት አግብቼአለሁ ስለዚህም ልመጣ አልችልም አለው።”

እንዴት ያሉ ሰንካላ ምክንያቶች ናቸው! መሬትም ሆነ ከብቶች መጀመሪያ ሳይታዩና ሳይመረመሩ እንደማይገዙ የታወቀ ነው። ስለዚህ ከተገዙ በኋላ እነዚህን ነገሮች መመልከቱ አጣዳፊ የሚሆንበት ምክንያት የለም። በተመሳሳይም አንድ ሰው ማግባቱ እንዲህ ዓይነቱን ትልቅ ግብዣ ከመቀበል ሊያግደው አይገባም። ስለዚህ ጌታው ሰዎቹ የሰጡትን ሰበብ አስባብ ሲሰማ ተናደደና ባሪያውን እንዲህ ሲል አዘዘው:-

“ወደ ከተማ ጎዳናና ወደ ስላች ፈጥነህ ውጣ ድሆችንና ጕንድሾችን አንካሶችንና ዕውሮችንም ወደዚህ አግባ አለው። ባሪያውም:- ጌታ ሆይ፣ እንዳዘዝኸኝ ተደርጎአል፣ ገናም ስፍራ አለ አለው። ጌታውም ባሪያውን:- ቤቴ እንዲሞላ ወደ መንገድና ወደ ቅጥር ውጣና ይገቡ ዘንድ ግድ በላቸው፤ . . . ከታደሙቱ ከእነዚያ ሰዎች አንድ ስንኳ እራቴን አይቀምስም አለው።”

በዚህ ምሳሌ የተገለጸው ሁኔታ ምንድን ነው? ግብዣውን ያዘጋጀው “ጌታ” ይሖዋ አምላክን ያመለክታል፤ ጥሪውን ያስተላለፈው “ባሪያ” ደግሞ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፤ ‘ታላቁ እራት’ ደግሞ መንግሥተ ሰማያትን ለመውረስ የሚያስችሉት አጋጣሚዎች ናቸው።

ከሁሉም በፊት መንግሥቱን እንዲወርሱ የመጀመሪያው ጥሪ የቀረበላቸው በኢየሱስ ዘመን የነበሩት የአይሁድ ሃይማኖታዊ መሪዎች ናቸው። ይሁን እንጂ እነርሱ ግብዣውን አልተቀበሉም። ስለዚህ በተለይ በ33 እንደ ዘመናችን አቆጣጠር ከተከበረው የጰንጠቆስጤ ዕለት ጀምሮ በአይሁድ ሕዝብ መካከል ለሚገኙት የተናቁና በዝቅተኛ ደረጃ ላይ የሚገኙ ሰዎች ሁለተኛ ግብዣ ቀርቧል። ሆኖም ምላሽ የሰጡት ሰዎች በሰማያዊው የአምላክ መንግሥት ውስጥ ያሉትን 144,000 ቦታዎች ለመሙላት በቂ ሆነው አልተገኙም። ስለዚህ ከሦስት ዓመት ተኩል በኋላ በ36 እንደ ዘመናችን አቆጣጠር ላልተገረዙ አይሁዳውያን ያልሆኑ ሰዎች ሦስተኛና የመጨረሻ ጥሪ ቀረበ፤ እነዚህን ሰዎች የመሰብሰቡ ሥራ እስከ ዘመናችን ድረስ ቀጥሏል። ሉቃስ 14:​1-24

▪ ኢየሱስ ስለ ትሕትና ምን ትምህርት ሰጠ?

▪ አንድ ጋባዥ በአምላክ ዘንድ ዋጋ የሚያሰጥ ግብዣ ማድረግ የሚችለው እንዴት ነው? ደስታ የሚያስገኝለትስ ለምንድን ነው?

▪ የተጋበዙት እንግዶች ያቀረቧቸው ምክንያቶች ሰንካላ የሆኑት ለምንድን ነው?

▪ ኢየሱስ ስለ “ታላቅ እራት” የተናገረው ምሳሌ ምን ያመለክታል?