በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ኢየሱስና አንድ ሀብታም የሆነ ወጣት የሕዝብ አለቃ

ኢየሱስና አንድ ሀብታም የሆነ ወጣት የሕዝብ አለቃ

ምዕራፍ 96

ኢየሱስና አንድ ሀብታም የሆነ ወጣት የሕዝብ አለቃ

ኢየሱስ በፍርጊያ አውራጃ አድርጎ ወደ ኢየሩሳሌም እየተጓዘ ሳለ አንድ ወጣት ሮጦ መጣና በፊቱ ተንበረከከ። ሰውየው አለቃ ተብሎ ተጠርቷል። ምናልባት በአካባቢው በሚገኝ ምኩራብ ከፍተኛ ቦታ የነበረው አለዚያም የሳንሄድሪን ሸንጎ አባል ሊሆን ይችላል። በተጨማሪም ሰውየው ሀብታም ነበር። “ቸር መምህር ሆይ፣ የዘላለም ሕይወትን እወርስ ዘንድ ምን ላድርግ? ብሎ ጠየቀው።”

“ስለ ምን ቸር ትለኛለህ?” በማለት ኢየሱስ መለሰለት። “ከአንዱ ከእግዚአብሔር በቀር ቸር ማንም የለም።” ወጣቱ “ቸር” የሚለውን ቃል የተጠቀመበት እንደ ማዕረግ ስም አድርጎ ሳይሆን አይቀርም፤ ስለዚህ ኢየሱስ እንዲህ ዓይነቱ የማዕረግ ስም የሚሰጠው ለአምላክ ብቻ እንደሆነ ገለጸለት።

ኢየሱስ በመቀጠል “ወደ ሕይወት መግባት ብትወድ ግን ትእዛዛትን ጠብቅ” አለው።

ሰውየው “የትኞቹን?” ሲል ጠየቀው።

ኢየሱስ ከአሥርቱ ትእዛዛት አምስቱን በመጥቀስ እንዲህ ሲል መለሰለት:- “አትግደል፣ አታመንዝር፣ አትስረቅ፣ በሐሰት አትመስክር፣ አባትህንና እናትህን አክብር።” ኢየሱስ ይበልጥ አስፈላጊ የሆነ አንድ ትእዛዝ በማከል “ባልንጀራህንም እንደ ራስህ ውደድ” አለው።

ሰውየው ቅንነት በተሞላበት ሁኔታ “ይህንማ ሁሉ ከሕፃንነቴ ጀምሬ ጠብቄአለሁ” ሲል መለሰለት። “ደግሞስ የሚጐድለኝ ምንድር ነው?” አለው።

ኢየሱስ ሰውየው ቅንነት በተሞላበት ሁኔታ ያቀረበውን ልባዊ ልመና ሲሰማ ለሰውየው ፍቅር አደረበት። ሆኖም ኢየሱስ ሰውየው ከቁሳዊ ንብረቶች ጋር ያለውን ቁርኝት በማስተዋል ማድረግ ያለበትን ነገር እንዲህ ሲል ገለጸለት:- “አንዲት ገና ቀርታሃለች፤ ያለህን ሁሉ ሽጠህ ለድሆች ስጥ፣ በሰማይም መዝገብ ታገኛለህ፣ መጥተህም ተከተለኝ።”

ሰውየው በጣም ቅር ተሰኝቶ ተነስቶ ሲሄድ ኢየሱስ በአዘኔታ እንደተመለከተው ምንም አያጠራጥርም። ብልጽግናው እውነተኛው ውድ ሀብት ያለውን ዋጋ እንዳያስተውል አሳውሮት ነበር። ኢየሱስ “ገንዘብ ላላቸው ወደ እግዚአብሔር መንግሥት መግባት እንዴት ጭንቅ ይሆናል” በማለት የተሰማውን ሐዘን ገለጸ።

ደቀ መዛሙርቱ የኢየሱስን ቃል ሲሰሙ በጣም ተገረሙ። ሆኖም ኢየሱስ በመቀጠል አንድ አጠቃላይ የሆነ ደንብ በተናገረ ጊዜ ይበልጥ ተደነቁ:- “ባለ ጠጋ ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ከሚገባ ይልቅ ግመል በመርፌ ቀዳዳ ሊገባ ይቀላል” አለ።

ደቀ መዛሙርቱ “እንግዲህ ማን ሊድን ይችላል?” ብለው ጠየቁት።

ኢየሱስ በቀጥታ ወደ እነሱ እየተመለከተ “ይህ በሰው ዘንድ አይቻልም በእግዚአብሔር ዘንድ ግን ሁሉ ይቻላል” በማለት መለሰላቸው።

ጴጥሮስ ሀብታሙ ወጣት አለቃ ከመረጠው ነገር በጣም የተለየ ምርጫ እንዳደረጉ በመጥቀስ “እነሆ፣ እኛ ሁሉን ትተን ተከተልንህ” ሲል ተናገረ። “እንኪያስ ምን እናገኝ ይሆን?” ሲል ጠየቀው።

ኢየሱስ የሚከተለውን ተስፋ ሰጠ:- “እናንተስ የተከተላችሁኝ፣ በዳግመኛ ልደት የሰው ልጅ በክብሩ ዙፋን በሚቀመጥበት ጊዜ፣ እናንተ ደግሞ በአሥራ ሁለቱ የእስራኤል ነገድ ስትፈርዱ በአሥራ ሁለት ዙፋን ትቀመጣላችሁ።” አዎን፣ ኢየሱስ በምድር ላይ ያሉት ሁኔታዎች ወደ ቀድሞ ሁኔታቸው ተመልሰው በኤደን የአትክልት ሥፍራ የነበረውን መልክ እንደሚይዙ ማመልከቱ ነበር። ጴጥሮስና ሌሎቹ ደቀ መዛሙርትም ይህችን ምድር አቀፍ ገነት ከክርስቶስ ጋር የመግዛት ሽልማት ያገኛሉ። በእርግጥም እንዲህ ዓይነቱ ታላቅ ሽልማት ማንኛውም ዓይነት መሥዋዕትነት ሊከፈልለት የሚገባው ነው!

ይሁን እንጂ አሁንም ቢሆን ሽልማቶች እንዳሉ ኢየሱስ እንዲህ ሲል ጠበቅ አድርጎ ገልጿል:- “ስለ እኔና ስለ ወንጌል ቤትን ወይም ወንድሞችን ወይም እኅቶችን ወይም አባትን ወይም እናትን ወይም ሚስትን ወይም ልጆችን ወይም እርሻን የተወ፣ አሁን በዚህ ዘመን ከስደት ጋር ቤቶችን ወንድሞችንም እኅቶችንም እናቶችንም ልጆችንም እርሻንም መቶ እጥፍ፣ በሚመጣውም ዓለም የዘላለም ሕይወት የማይቀበል ማንም የለም።”

ኢየሱስ ቃል በገባው መሠረት ደቀ መዛሙርቱ ወደ የትኛውም የዓለም ክፍል ቢሄዱ ከሥጋዊ የቤተሰብ አባሎቻቸው ጋር ካላቸው ዝምድና ይበልጥ የጠበቀና ውድ የሆነ ዝምድና ከመሰል ክርስቲያኖች ያገኛሉ። ሀብታሙ ወጣት አለቃ ይኸኛውን ሽልማትም ሆነ በአምላክ ሰማያዊ መንግሥት የዘላለም ሕይወት የማግኘት አጋጣሚ ያጣ ይመስላል።

ከዚያ በኋላ ኢየሱስ “ነገር ግን ብዙዎቹ ፊተኞች ኋለኞች፣ ኋለኞችም ፊተኞች ይሆናሉ” ሲል አክሎ ተናግሯል። ምን ማለቱ ነበር?

ልክ እንደ ሀብታሙ ወጣት አለቃ ሃይማኖታዊ መብቶችን በማግኘት “ፊተኞች” የሆኑ ብዙ ሰዎች ወደ መንግሥቱ እንደማይገቡ መናገሩ ነበር። “ኋለኞች” ይሆናሉ። ሆኖም በዝቅተኛ ደረጃ ላይ የሚገኙትን የኢየሱስን ደቀ መዛሙርት ጨምሮ ራሳቸውን በሚያመጻድቁት ፈሪሳውያን ዘንድ “ኋለኞች” ማለትም የምድር ሰዎች ወይም አምሃሬትስ በመባል ዝቅ ተደርገው በመታየት የሚናቁት ሰዎች “ፊተኞች” ይሆናሉ። “ፊተኞች” ይሆናሉ ማለት ከክርስቶስ ጋር በመንግሥቱ ተባባሪ ገዥዎች የመሆን መብት ያገኛሉ ማለት ነው። ማርቆስ 10:​17-31፤ ማቴዎስ 19:​16-30፤ ሉቃስ 18:​18-30

▪ ከሁኔታው መረዳት እንደሚቻለው ሀብታሙ ወጣት ምን ዓይነት አለቃ ነበር?

▪ ኢየሱስ ቸር ተብሎ መጠራቱን የተቃወመው ለምንድን ነው?

▪ የወጣቱ አለቃ ተሞክሮ ሀብታም መሆን ያለውን አደጋ የሚያሳየው እንዴት ነው?

▪ ኢየሱስ ተከታዮቹ ምን ዋጋ እንደሚያገኙ ቃል ገብቷል?

▪ ፊተኞች ኋለኞች፣ ኋለኞች ደግሞ ፊተኞች የሚሆኑት እንዴት ነው?