በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ኢየሱስን ለመግደል የተደረጉ ሌሎች ሙከራዎች

ኢየሱስን ለመግደል የተደረጉ ሌሎች ሙከራዎች

ምዕራፍ 81

ኢየሱስን ለመግደል የተደረጉ ሌሎች ሙከራዎች

ጊዜው ክረምት ስለነበረ ኢየሱስ የሰሎሞን ደጅ መመላለሻ ተብሎ በሚጠራው መጠለያ ሥር ይመላለስ ነበር። ይህ መጠለያ የሚገኘው ከቤተ መቅደሱ ጎን ነበር። እዚያ ሳለ አይሁዶች ከበቡትና “እስከ መቼ ድረስ በጥርጣሬ ታቆየናለህ? አንተ ክርስቶስ እንደ ሆንህ ገልጠህ ንገረን” አሉት።

“ነገርኋችሁ አታምኑምም” በማለት ኢየሱስ መለሰላቸው። ኢየሱስ በውኃው ጉድጓድ አጠገብ ላገኛት ሴት እንደነገራት በቀጥታ እኔ ክርስቶስ ነኝ ብሎ አልነገራቸውም። ሆኖም ከላይኛው ዓለም የመጣ መሆኑንና ከአብርሃም በፊት ይኖር እንደነበረ በነገራቸው ጊዜ ማንነቱን ገልጾላቸዋል ማለት ይቻላል።

ይሁን እንጂ ኢየሱስ ሕዝቡ እሱ ያከናወናቸውን ሥራዎች መጽሐፍ ቅዱስ ክርስቶስ ሲመጣ ምን እንደሚያከናውን አስቀድሞ በትንቢት ከገለጻቸው ነገሮች ጋር በማወዳደር ራሳቸው ክርስቶስ ነው ወደሚል መደምደሚያ እንዲደርሱ ፈልጎ ነበር። ቀደም ሲል እርሱ ክርስቶስ መሆኑን ለማንም እንዳይናገሩ ደቀ መዛሙርቱን ያስጠነቀቃቸው ለዚህ ነው። አሁንም በመቀጠል ጠላቶቹ የሆኑትን እነዚህን አይሁዶች እንዲህ ያላቸው በዚህ ምክንያት ነው:- “እኔ በአባቴ ስም የማደርገው ሥራ ይህ ስለ እኔ ይመሰክራል፤ እናንተ ግን . . . አታምኑም።”

ያላመኑት ለምንድን ነው? ኢየሱስ፣ ክርስቶስ መሆኑን የሚያሳይ ማስረጃ በመጥፋቱ ነው? አይደለም፤ ከዚህ ይልቅ ኢየሱስ እንዲህ ባላቸው ጊዜ ምክንያቱ ምን እንደሆነ ገልጿል:- “ከበጎቼ ስላልሆናችሁ አታምኑም። በጎቼ ድምፄን ይሰማሉ እኔም አውቃቸዋለሁ ይከተሉኝማል፤ እኔም የዘላለም ሕይወትን እሰጣቸዋለሁ፣ ለዘላለምም አይጠፉም፣ ከእጄም ማንም አይነጥቃቸውም። የሰጠኝ አባቴ ከሁሉ ይበልጣል፣ ከአባቴም እጅ ሊነጥቃቸው ማንም አይችልም።”

ከዚያም ኢየሱስ “እኔና አብ አንድ ነን” በማለት ከአባቱ ጋር ያለውን የቀረበ ዝምድና ገለጸ። ኢየሱስ በምድር ስለነበረና አባቱ ደግሞ ያለው በሰማይ ስለሆነ ቃል በቃል ወይም በአካል ከአባቴ ጋር አንድ ነን ማለቱ እንዳልሆነ ግልጽ ነው። ከዚህ ይልቅ በዓላማ አንድ ነን ማለቱ ነው፤ አንድነት እንዳላቸው መግለጹ ነበር።

አይሁዶች ኢየሱስ በተናገረው ቃል በመናደድ ከዚህ ቀደም በዳስ በዓል ወቅት እንዳደረጉት አሁንም ሊወግሩት ድንጋይ አነሱ። ኢየሱስ ሊገድሉት የፈለጉትን ሰዎች በድፍረት በመጋፈጥ “ከአባቴ ብዙ መልካም ሥራ አሳየኋችሁ፤ ከእነርሱ ስለ ማናቸው ሥራ ትወግሩኛላችሁ?” አላቸው።

“ስለ መልካም ሥራ አንወግርህም” ብለው መለሱለት፤ “ስለ ስድብ፤ አንተም ሰው ስትሆን ራስህን አምላክ ስለ ማድረግህ ነው እንጂ” አሉት። ኢየሱስ ፈጽሞ አምላክ ነኝ አላለም፤ ታዲያ አይሁዶች እንዲህ ያሉት ለምንድን ነው?

ኢየሱስ እነርሱ ለአምላክ ብቻ የተወሰነ ነው ብለው የሚያምኑት ኃይል እንዳለው በመናገሩ መሆኑን ከሁኔታው መረዳት ይቻላል። ለምሳሌ ያህል ‘ለበጎቹ የዘላለም ሕይወት እንደሚሰጣቸው’ ተናግሮ ነበር፤ ይህን ደግሞ ማንም ሰብዓዊ ሰው ሊያደርገው አይችልም። ይሁን እንጂ አይሁዶች ኢየሱስ ሥልጣኑን የተቀበለው ከአባቱ መሆኑን አምኖ መናገሩን ሳያስተውሉ ቀርተዋል።

ኢየሱስ ቀጥሎ የሚከተለውን ጥያቄ በማቅረብ ከአምላክ የሚያንስ መሆኑን አሳይቷል:- “እኔ:- አማልክት ናችሁ አልሁ ተብሎ በሕጋችሁ [በመዝሙር 82:​6 ላይ] የተጻፈ አይደለምን? . . . እነዚያን የእግዚአብሔር ቃል የመጣላቸውን አማልክት ካላቸው፣ የእግዚአብሔር ልጅ ነኝ ስላልሁ እናንተ አብ የቀደሰውን ወደ ዓለምም የላከውን:- ትሳደባለህ ትሉታላችሁን?”

ቅዱሳን ጽሑፎች ፍርደ ገምድል መሳፍንቶችን እንኳ “አማልክት” ብለው የሚጠሩ ከሆነ እነዚህ አይሁዶች ኢየሱስ “የእግዚአብሔር ልጅ ነኝ” በማለቱ ምን ብለው ሊተቹት ይችላሉ? ኢየሱስ እንዲህ ሲል አክሎ ተናገረ:- “እኔ የአባቴን ሥራ ባላደርግ አትመኑኝ፤ ባደርገው ግን፣ እኔን ስንኳ ባታምኑ አብ በእኔ እንደ ሆነ እኔም በአብ እንደ ሆንሁ ታውቁና ታስተውሉ ዘንድ ሥራውን እመኑ።”

ኢየሱስ ይህን ሲናገር አይሁዶች ሊይዙት ሞከሩ። ሆኖም ቀደም ሲል በዳስ በዓል ላይ እንዳደረገው አሁንም አመለጣቸው። ኢየሩሳሌምን ለቆ ወጣና ዮሐንስ ከአራት ዓመት ገደማ በፊት ማጥመቅ ወደ ጀመረበት ወደ ዮርዳኖስ ወንዝ ማዶ ተሻገረ። ይህ ቦታ ከደቡባዊው የገሊላ ባሕር ዳርቻ ብዙም የሚርቅ አይመስልም። ከኢየሩሳሌም የሁለት ቀን ገደማ መንገድ ነው።

ብዙ ሰዎች ኢየሱስ ወዳለበት ወደዚህ ሥፍራ መጥተው “ዮሐንስ አንድ ምልክት ስንኳ አላደረገም፣ ነገር ግን ዮሐንስ ስለዚህ ሰው የተናገረው ሁሉ እውነት ነበረ” በማለት ተናገሩ። ስለዚህ በዚህ ሥፍራ ብዙዎች በኢየሱስ አመኑ። ዮሐንስ 10:​22-42፤ 4:​26፤ 8:​23, 58፤ ማቴዎስ 16:​20

▪ ኢየሱስ ሰዎች ክርስቶስ መሆኑን በምን አማካኝነት እንዲያውቁ ፈልጎ ነበር?

▪ ኢየሱስና አባቱ አንድ የሆኑት እንዴት ነው?

▪ ከሁኔታው መረዳት እንደሚቻለው አይሁዶች ኢየሱስ ራሱን አምላክ አድርጓል እንዲሉ ያደረጋቸው ምንድን ነው?

▪ ኢየሱስ ከመዝሙር የጠቀሰው ጥቅስ ከአምላክ ጋር እኩል ነኝ አለማለቱን የሚያሳየው እንዴት ነው?