በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ኢየሱስን ማጥመድ ሳይችሉ ቀሩ

ኢየሱስን ማጥመድ ሳይችሉ ቀሩ

ምዕራፍ 108

ኢየሱስን ማጥመድ ሳይችሉ ቀሩ

ኢየሱስ በቤተ መቅደስ ስላስተማረና ከጥቂት ጊዜ በፊት ሦስት ምሳሌዎች በመናገር የሃይማኖታዊ ጠላቶቹን ክፋት ስላጋለጠ ፈሪሳውያን ተናደዱና እርሱን ለመያዝ የሚያስችላቸውን ነገር እንዲናገር በማድረግ ሊያጠምዱት ተማከሩ። አንድ ተንኮል ሸረቡና እሱን ለማጥመድ እንዲሞክሩ ደቀ መዝሙሮቻቸውን ከሄሮድስ የፖለቲካ ቡድን ተከታዮች ጋር ላኳቸው።

የተላኩት ሰዎች እንዲህ አሉት:- “መምህር ሆይ! አንተ እውነተኛ መሆንህንና የእግዚአብሔርን መንገድ በእውነት የምታስተምር መሆንህን እናውቃለን፤ ሰውንም በመፍራት የምታደርገው ነገር የለም፤ ምክንያቱም አንተ ለሰው አታደላም። በል እስቲ ንገረን ምን ይመስልሃል? ለቄሳር ግብር መክፈል ተገቢ ነውን ወይስ ተገቢ አይደለም?”​— የ1980 ትርጉም

ኢየሱስ በሽንገላቸው አልተታለለም። ‘የለም፣ ይህን ግብር መክፈል ተገቢ ወይም ትክክል አይደለም’ ብሎ ቢመልስ በሮም መንግሥት ላይ ዓመፅ አነሳስተሃል ተብሎ እንደሚወነጀል ያውቃል። ‘ተገቢ ነው፣ ይህን ግብር መክፈል አለባችሁ’ ብሎ ቢመልስ ደግሞ በሮም ቀንበር ሥር መውደቃቸውን ያልወደዱት አይሁዶች ሊጠሉት ነው። ስለዚህ ኢየሱስ “እናንተ ግብዞች፣ ስለ ምን ትፈትኑኛላችሁ? የግብሩን ብር አሳዩኝ” ብሎ መለሰላቸው።

አንድ ሳንቲም አምጥተው ሲያሳዩት “ይህች መልክ ጽሕፈቲቱስ የማን ናት?” ብሎ ጠየቃቸው።

“የቄሣር” ብለው መለሱለት።

“እንኪያስ የቄሣርን ለቄሣር የእግዚአብሔርንም ለእግዚአብሔር አስረክቡ” አላቸው። እነዚህ ሰዎች ኢየሱስ የሰጠውን ጥበብ የተሞላበት መልስ ሲሰሙ ተደነቁ። ከዚያም ትተውት ሄዱ።

ትንሣኤ የለም ብለው የሚያምኑት ሰዱቃውያን፣ ፈሪሳውያን ኢየሱስን ሊያስወነጅለው የሚችል ነገር ሊያገኙበት እንዳልቻሉ ሲመለከቱ ወደ ኢየሱስ ቀረቡና እንዲህ ሲሉ ጠየቁት:- “መምህር ሆይ፣ ሙሴ አንድ ሰው ልጅ ሳይወልድ ሲሞት ወንድሙ ሚስቱን አግብቶ ለወንድሙ ዘር ይተካ አለ። ሰባት ወንድማማች በእኛ ዘንድ ነበሩ፤ ፊተኛውም ሚስት አግብቶ ሞተ፣ ዘርም ስለሌለው ሚስቱን ለወንድሙ ተወለት፤ እንዲሁ ደግሞ ሁለተኛው ሦስተኛውም፣ እስከ ሰባተኛው ድረስ። ከሁሉም በኋላ ሴቲቱ ሞተች። ሁሉ አግብተዋታልና በትንሣኤ ቀንስ ከሰባቱ ለማናቸው ሚስት ትሆናለች?”

ኢየሱስ እንዲህ ሲል መለሰላቸው:- “መጻሕፍትንና የእግዚአብሔርን ኃይል አታውቁምና ስለዚህ የምትስቱ አይደለምን? ከሙታንስ ሲነሡ በሰማያት እንዳሉ መላእክት ይሆናሉ እንጂ አያገቡም፣ አይጋቡምም። ስለ ሙታን ግን እንዲነሡ እግዚአብሔር:- እኔ የአብርሃም አምላክ የይስሐቅም አምላክ የያዕቆብም አምላክ ነኝ እንዳለው በሙሴ መጽሐፍ በቍጥቋጦው ዘንድ የተጻፈውን አላነበባችሁምን? የሕያዋን አምላክ ነው እንጂ የሙታን አይደለም። እንግዲህ እጅግ ትስታላችሁ።”

አሁንም ሕዝቡ በኢየሱስ መልስ በጣም ተደነቁ። እንዲያውም ከጻፎቹ አንዳንዶቹ “መምህር ሆይ፣ መልካም ተናገርህ” ለማለት ተገደዋል።

ፈሪሳውያን ኢየሱስ ሰዱቃውያንን ዝም እንዳሰኛቸው ተመለከቱና አንድ ግንባር ፈጥረው ወደ እሱ መጡ። ኢየሱስን እንደገና ለመፈተን ከመካከላቸው አንዱ ጸሐፊ “መምህር ሆይ፣ ከሕግ ማናቸይቱ ትእዛዝ ታላቅ ናት?” ብሎ ጠየቀው።

ኢየሱስ እንዲህ ሲል መለሰለት:- “ከትእዛዛቱ ሁሉ ፊተኛይቱ:- እስራኤል ሆይ፣ ስማ፤ ጌታ አምላካችን አንድ ጌታ ነው፣ አንተም በፍጹም ልብህ በፍጹምም ነፍስህ በፍጹምም አሳብህ በፍጹምም ኃይልህ ጌታ አምላክህን ውደድ የምትል ናት። ፊተኛይቱ ትእዛዝ ይህች ናት። ሁለተኛይቱም:- ባልንጀራህን እንደ ራስህ ውደድ የምትል እርስዋን የምትመስል ይህች ናት። ከእነዚህ የምትበልጥ ሌላ ትእዛዝ የለችም።” እንዲያውም ኢየሱስ “የሙሴ ሕግና የነቢያት ትምህርት ሁሉ የተመሠረቱት በእነዚህ በሁለቱ ትእዛዞች ላይ ነው” ሲል አክሎ ተናግሯል።​— የ1980 ትርጉም

ጸሐፊው እንዲህ በማለት በነገሩ መስማማቱን ገለጸ:- “መልካም ነው፣ መምህር ሆይ፤ አንድ ነው ከእርሱም በቀር ሌላ የለም ብለህ በእውነት ተናገርህ፤ በፍጹም ልብ በፍጹም አእምሮም በፍጹም ነፍስም በፍጹም ኃይልም እርሱን መውደድ፣ ባልንጀራህንም እንደ ራስ መውደድ በሙሉ ከሚቃጠል መሥዋዕትና ከሌላው መሥዋዕት ሁሉ የሚበልጥ ነው።”

ኢየሱስ ጸሐፊው አስተዋይነት የተንጸባረቀበት መልስ እንደሰጠ በመረዳት “አንተ ከእግዚአብሔር መንግሥት የራቅህ አይደለህም” አለው።

ኢየሱስ አሁን ለሦስት ቀናት ማለት እሁድ፣ ሰኞና ማክሰኞ በቤተ መቅደሱ ሲያስተምር ቆይቷል። ሕዝቡ በትምህርቱ የተደሰቱ ቢሆንም የሃይማኖት መሪዎቹ ግን ሊገድሉት ፈልገዋል። ሆኖም እስካሁን ድረስ ያደረጓቸው ሙከራዎች ከሽፈዋል። ማቴዎስ 22:​15-40፤ ማርቆስ 12:​13-34፤ ሉቃስ 20:​20-40

▪ ፈሪሳውያን ኢየሱስን ለማጥመድ ምን ተንኮል ሸርበው ነበር? አዎ ወይም አይደለም የሚል ቀጥተኛ መልስ ቢሰጥ ኖሮስ ምን ውጤት ያስከትል ነበር?

▪ ኢየሱስ ሰዱቃውያን እሱን ለማጥመድ ያደረጉትን ጥረት ያጨናገፈው እንዴት ነው?

▪ ፈሪሳውያን ኢየሱስን ለመፈተን ምን ተጨማሪ ሙከራ አድርገዋል? ውጤቱስ ምን ነበር?

▪ ኢየሱስ በኢየሩሳሌም ባከናወነው የመጨረሻ አገልግሎት ወቅት በቤተ መቅደሱ ያስተማረው ለስንት ቀናት ነበር? ይህስ ምን ውጤት አስከትሏል?