በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ኢየሱስን ሳያስሩት ቀሩ

ኢየሱስን ሳያስሩት ቀሩ

ምዕራፍ 67

ኢየሱስን ሳያስሩት ቀሩ

የዳስ በዓል እየተከበረ ሳለ የሃይማኖት መሪዎቹ ኢየሱስን እንዲይዙት የፖሊስ መኮንኖችን ላኩ። ኢየሱስ ለመደበቅ አልሞከረም። ከዚህ ይልቅ ኢየሱስ እንዲህ በማለት በሕዝብ ፊት ማስተማሩን ቀጠለ:- “ገና ጥቂት ጊዜ ከእናንተ ጋር እቆያለሁ ወደ ላከኝም እሄዳለሁ። ትፈልጉኛላችሁ አታገኙኝምም፤ እኔም ወዳለሁበት እናንተ ልትመጡ አትችሉም።”

አይሁዶች ምን ማለቱ እንደሆነ አልገባቸውም፤ ስለዚህ እንዲህ እያሉ መጠያየቅ ጀመሩ:- “እኛ እንዳናገኘው ይህ ወዴት ይሄድ ዘንድ አለው? በግሪክ ሰዎች መካከል ተበትነው ወደሚኖሩት [“አይሁዳውያን፣” የ1980 ትርጉም] ሊሄድና የግሪክን ሰዎች ሊያስተምር አለውን? እርሱ:- ትፈልጉኛላችሁ አታገኙኝምም እኔም ወዳለሁበት እናንተ ልትመጡ አትችሉም የሚለው ይህ ቃል ምንድር ነው?” እርግጥ ኢየሱስ እየቀረበ ስላለው ሞቱና ከሞት ተነሥቶ ስለሚያገኘው ሰማያዊ ሕይወት መናገሩ ነበር። ጠላቶቹ ደግሞ ተከትለውት ወደ ሰማይ መሄድ አይችሉም።

ሰባተኛውና የመጨረሻው የበዓሉ ቀን ደረሰ። በእያንዳንዱ የበዓሉ ቀን ጠዋት ጠዋት አንድ ካህን ከሰሊሆም መጥመቂያ ውኃ አምጥቶ ያፈስ ነበር፤ ያፈሰሰውም ውኃ ወደ መሠዊያው ሥር ይወርድ ነበር። ኢየሱስ እንደሚከተለው በማለት ጮክ ብሎ ሲናገር ሕዝቡ በየዕለቱ የሚፈጸመውን ይህን ሥርዓት እንዲያስታውሱ ሳያደርጋቸው አልቀረም:- “ማንም የተጠማ ቢኖር ወደ እኔ ይምጣና ይጠጣ። በእኔ የሚያምን፣ መጽሐፍ እንዳለ፣ የሕይወት ውኃ ወንዝ ከሆዱ ይፈልቃል።”

እዚህ ላይ ኢየሱስ መንፈስ ቅዱስ ሲወርድ ስለሚያስገኛቸው ታላላቅ ውጤቶች መናገሩ ነበር። በዚሁ መሠረት በሚቀጥለው ዓመት በጰንጠቆስጤ ዕለት መንፈስ ቅዱስ ወርዷል። በዚያም 120ዎቹ ደቀ መዛሙርት ሕዝቡን ማገልገል ሲጀምሩ የሕይወት ውኃ ምንጮች መፍለቅ ጀመሩ። እስከዚያ ጊዜ ድረስ ግን የክርስቶስ ደቀ መዛሙርት በመንፈስ ቅዱስ ተቀብተው ለሰማያዊ ሕይወት ስላልተጠሩ በዚህ መልኩ የወረደ መንፈስ አልነበረም።

አንዳንዶች ለኢየሱስ ትምህርት አዎንታዊ ምላሽ በመስጠት “ይህ በእውነት ነቢዩ ነው” አሉ፤ እንደሚመጣ አስቀድሞ ቃል የተገባለትን ከሙሴ የሚበልጠውን ነቢይ ማመልከታቸው እንደሆነ ከሁኔታው መረዳት ይቻላል። ሌሎች ደግሞ “ይህ ክርስቶስ ነው አሉ።” ሆኖም ሌሎች እንዲህ ሲሉ ተቃወሙ:- “ክርስቶስ በእውኑ ከገሊላ ይመጣልን? ክርስቶስ ከዳዊት ዘር ዳዊትም ከነበረባት መንደር ከቤተ ልሔም እንዲመጣ መጽሐፍ አላለምን?”

ስለዚህ በሕዝቡ መካከል ክፍፍል ተፈጠረ። አንዳንዶቹ ኢየሱስ እንዲያዝ ፈልገው ነበር፤ ሆኖም እጁን የጫነበት አልነበረም። የፖሊስ መኮንኖቹ ኢየሱስን ሳይዙ ሲመለሱ የካህናት አለቆቹና ፈሪሳውያን “ያላመጣችሁት ስለ ምን ነው?” ብለው ጠየቋቸው።

መኮንኖቹም “እንደዚህ ሰው ማንም እንዲሁ ከቶ አልተናገረም ብለው መለሱ።”

የሃይማኖት መሪዎቹ በጣም ተናደው በመሳለቅ፣ መኮንኖቹ የተናገሩትን ነገር በተሳሳተ መን​ገድ በመተርጎምና በመሳደብ ወራዳ ድርጊት ፈጸሙ። እንዲህ በማለት አንኳሰሷቸው:- “እናንተ ደግሞ ሳታችሁን? ከአለቆች ወይስ ከፈሪሳውያን በእርሱ ያመነ አለን? ነገር ግን ሕግን የማያውቀው ይህ ሕዝብ ርጉም ነው።”

በዚህ ጊዜ ኒቆዲሞስ የተባለ አንድ ፈሪሳዊና የአይሁድ ገዥ (የሳንሄድሪን የፍርድ ሸንጎ አባል ነው ማለት ነው) ኢየሱስን በመደገፍ በድፍረት ተናገረ። ከሁለት ዓመት ተኩል በፊት ኒቆዲሞስ በሌሊት ኢየሱስ ወዳለበት መጥቶ በእርሱ እንደሚያምን መግለጹን ታስታውስ ይሆናል። ኒቆዲሞስ እንዲህ አለ:- “ሕጋችን አስቀድሞ ከእርሱ ሳይሰማ ምንስ እንዳደረገ ሳያውቅ በሰው ይፈረዳልን?”

ፈሪሳውያን ከራሳቸው ወገን የሆነ ሰው ለኢየሱስ ጥብቅና ቆሞ መናገሩ ይበልጥ አናደዳቸው። “አንተም ደግሞ ከገሊላ ነህን?” በማለት በምጸት ተናገሩ። “ነቢይ ከገሊላ እንዳይነሣ መርምርና እይ አሉት።”

ምንም እንኳ ቅዱሳን ጽሑፎች ነቢይ ከገሊላ ይነሳል ብለው በቀጥታ ባይናገሩም በዚህ አውራጃ “ታላቅ ብርሃን” እንደሚታይ በመግለጽ ክርስቶስ ከዚያ እንደሚነሳ ይጠቁማሉ። ከዚህም በላይ ኢየሱስ የተወለደው በቤተ ልሔም ነው፤ እንዲሁም የዳዊት ዘር ነው። ፈሪሳውያን ይህን ሊያውቁ ቢችሉም እንኳ ሕዝቡ ስለ ኢየሱስ የተሳሳተ አስተሳሰብ እንዲያድርበት ወሬ ሳይነዙበት አልቀረም። ዮሐንስ 7:​32-52፤ ኢሳይያስ 9:​1, 2 የ1980 ትርጉምማቴዎስ 4:​13-17

▪ በዓሉ በሚከበርባቸው ቀናት ሁሉ ጠዋት ጠዋት ምን ይከናወናል? ኢየሱስ የሰዎችን ትኩረት ወደዚህ ነገር ስቦ ሊሆን የሚችለው እንዴት ነው?

▪ መኮንኖቹ ኢየሱስን ሳይዙ የቀሩት ለምንድን ነው? የሃይማኖት መሪዎቹስ ምን ምላሽ ሰጡ?

▪ ኒቆዲሞስ ማን ነው? ስለ ኢየሱስ ምን አመለካከት ነበረው? ፈሪሳውያን የሥራ ባልደረቦቹስ ኒቆዲሞስን ምን አሉት?

▪ ክርስቶስ ከገሊላ እንደሚነሣ የሚያሳይ ምን ማስረጃ አለ?