በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ኢየሱስ ለመጨረሻ ጊዜ ወደ ኢየሩሳሌም ሲጓዝ አሥር የሥጋ ደዌ በሽተኞች ተፈወሱ

ኢየሱስ ለመጨረሻ ጊዜ ወደ ኢየሩሳሌም ሲጓዝ አሥር የሥጋ ደዌ በሽተኞች ተፈወሱ

ምዕራፍ 92

ኢየሱስ ለመጨረሻ ጊዜ ወደ ኢየሩሳሌም ሲጓዝ አሥር የሥጋ ደዌ በሽተኞች ተፈወሱ

ኢየሱስ ኢየሩሳሌምን ለቆ ወደ ኤፍሬም ከተማ በመጓዝ የሳንሄድሪን ሸንጎ እሱን ለመግደል ያደረገውን ጥረት አከሸፈው። የኤፍሬም ከተማ ከኢየሩሳሌም በስተ ሰሜን ምሥራቅ የምትገኝ ስትሆን በመካከላቸው ያለው ርቀት 24 ኪሎ ሜትር ገደማ ቢሆን ነው። ኢየሱስ ከጠላቶቹ ርቆ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር በዚያ ተቀመጠ።

ይሁን እንጂ በ33 እንደ ዘመናችን አቆጣጠር የተከበረው የማለፍ በዓል እየተቃረበ ስለነበር ኢየሱስ ብዙም ሳይቆይ እንደገና መጓዝ ጀመረ። በሰማርያ አድርጎ ወደ ገሊላ ተጓዘ። ኢየሱስ ከመሞቱ በፊት ወደዚህ ቦታ ያደረገው የመጨረሻ ጉዞ ይህ ነበር። ኢየሱስና ደቀ መዛሙርቱ በገሊላ ሳሉ የማለፍ በዓልን ለማክበር ወደ ኢየሩሳሌም በመጓዝ ላይ ካሉ ሌሎች ሰዎች ጋር ሳይቀላቀሉ አልቀረም። ከዮርዳኖስ ወንዝ በስተ ምሥራቅ በምትገኘው የፍርጊያ አውራጃ በኩል በሚወስደው መንገድ ተጓዙ።

ኢየሱስ በጉዞው መጀመሪያ አካባቢ ወይ በሰማርያ አለዚያም ደግሞ በገሊላ ወደምትገኝ አንዲት መንደር ሲገባ የሥጋ ደዌ የያዛቸው አሥር ሰዎች አገኙት። ይህ አስከፊ በሽታ የአንድን ሰው የአካል ክፍሎች ማለትም የእጆቹንና የእግሮቹን ጣቶች፣ ጆሮዎቹን፣ አፍንጫውንና ከንፈሮቹን ቀስ በቀስ ይቆማምጣቸዋል። ሌሎች ሰዎች በዚህ በሽታ እንዳይያዙ ለመከላከል የአምላክ ሕግ አንድን የሥጋ ደዌ በሽተኛ በተመለከተ እንዲህ ይላል:- “ከንፈሩንም ይሸፍን፤ ርኩስ ርኩስ ነኝ ይበል። ደዌው ባለበት ዘመን ሁሉ ርኩስ ይሆናል፤ . . . ብቻውን ይቀመጣል።”

የሥጋ ደዌ የያዛቸው አሥሩ ሰዎች ሕጉ የሥጋ ደዌ ለያዛቸው ሰዎች ያወጣውን ዕገዳ በማክበር ከኢየሱስ በጣም ርቀው ነበር። ሆኖም ድምፃቸውን ከፍ አድርገው “ኢየሱስ ሆይ፣ አቤቱ፣ ማረን” በማለት ጮኹ።

ኢየሱስ በርቀት ቆመው አያቸውና “ሂዱ፣ ራሳችሁን ለካህናት አሳዩ” ሲል አዘዛቸው። ኢየሱስ እንዲህ ብሎ የተናገረው የአምላክ ሕግ ከሕመማቸው የዳኑ የሥጋ ደዌ በሽተኞች የተፈወሱ መሆናቸውን የመናገር ሥልጣን የሰጠው ለካህናት በመሆኑ ነው። በዚህ መንገድ እንዲህ ዓይነቶቹ ሰዎች ጤናማ ከሆኑ ሰዎች ጋር ተቀላቅለው እንደገና አብረው የመኖር ፈቃድ ያገኛሉ።

የሥጋ ደዌ የያዛቸው አሥሩ ሰዎች በኢየሱስ ተአምራዊ ኃይል ላይ ሙሉ እምነት ነበራቸው። ስለዚህ ገና ያልተፈወሱ ቢሆንም እንኳ በፍጥነት ወደ ካህናቱ ሄዱ። መንገድ ላይ ሳሉ፣ በኢየሱስ ላይ ያላቸው እምነት ወሮታውን አስገኝቶላቸዋል። ጤንነታቸው እንደተመለሰ ይታያቸውና ይሰማቸው ጀመር።

ከያዛቸው የሥጋ ደዌ ከነጹት ሰዎች መካከል ዘጠኙ መንገዳቸውን ቀጠሉ፤ ሳምራዊ የሆነው አንደኛው ግን ኢየሱስን ለመፈለግ ተመለሰ። እንዲህ ያደረገው ለምን ይሆን? ባገኘው ፈውስ በጣም ስለተደሰተ ማመስገን ፈልጎ ነው። ድምፁን ከፍ አድርጎ አምላክን አመሰገነ። ኢየሱስን ሲያገኘው ደግሞ እግሩ ፊት ወድቆ አመሰገነው።

ኢየሱስ እንዲህ ሲል መለሰ:- “አሥሩ አልነጹምን? ዘጠኙስ ወዴት አሉ? ከዚህ ከልዩ ወገን በቀር እግዚአብሔርን ሊያከብሩ የተመለሱ አልተገኙም።”

ከዚያም ሳምራዊውን ሰው “ተነሣና ሂድ፤ እምነትህ አድኖሃል” አለው።

ኢየሱስ የሥጋ ደዌ ይዟቸው የነበሩትን አሥሩን ሰዎች እንደፈወሰ የሚገልጸውን ታሪክ ስናነብ “ዘጠኙስ ወዴት አሉ?” የሚለው የኢየሱስ ጥያቄ በተዘዋዋሪ የሚያስተላልፈውን ትምህርት ልብ ማለት ይኖርብናል። ዘጠኙ አመስጋኝ አለመሆናቸው ከባድ ስህተት ነበር። አምላክ በሚያመጣው ጽድቅ በሚሰፍንበት አዲስ ዓለም ውስጥ ለዘላለም የመኖርን አስተማማኝ ተስፋ ጨምሮ ከአምላክ ለምናገኛቸው ነገሮች ልክ እንደ ሳምራዊው አመስጋኞች መሆናችንን እናሳያለንን? ዮሐንስ 11:​54, 55፤ ሉቃስ 17:​11-19፤ ዘሌዋውያን 13:​16, 17, 45, 46፤ ራእይ 21:​3, 4

▪ ኢየሱስ እሱን ለመግደል የተሸረበውን ሴራ ያከሸፈው እንዴት ነው?

▪ ኢየሱስ ከዚያ በኋላ የተጓዘው ወዴት ነው? የጉዞው መጨረሻስ የት ነው?

▪ የሥጋ ደዌ በሽተኞቹ ርቀው የቆሙት ለምንድን ነው? ኢየሱስ ወደ ካህናት እንዲሄዱ የነገራቸውስ ለምንድን ነው?

▪ ከዚህ ተሞክሮ ምን ትምህርት ማግኘት አለብን?