በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ኢየሱስ ሕያው ሆነ!

ኢየሱስ ሕያው ሆነ!

ምዕራፍ 128

ኢየሱስ ሕያው ሆነ!

ሴቶቹ የኢየሱስ መቃብር ባዶ ሆኖ ሲያገኙት መግደላዊት ማርያም ለጴጥሮስና ለዮሐንስ ለመንገር እየሮጠች ሄደች። ይሁን እንጂ ከሁኔታው ለመረዳት እንደሚቻለው ሌሎቹ ሴቶች እዚያው መቃብሩ ያለበት ቦታ ቀሩ። ብዙም ሳይቆይ አንድ መልአክ ተገለጠና ወደ ውስጥ ጠራቸው።

ሴቶቹ መቃብሩ ውስጥ ሌላም መልአክ ተመለከቱ፤ ከመላእክቱ አንዱ እንዲህ አላቸው:- “እናንተስ አትፍሩ የተሰቀለውን ኢየሱስን እንድትሹ አውቃለሁና እንደ ተናገረ ተነሥቶአልና በዚህ የለም የተኛበትን ስፍራ ኑና እዩ። ፈጥናችሁም ሂዱና:- ከሙታን ተነሣ፣ . . . ብላችሁ ለደቀ መዛሙርቱ ንገሩአቸው።” ስለዚህ እነዚህም ሴቶች በፍርሃትና በከፍተኛ የደስታ ስሜት ተውጠው እየሮጡ ሄዱ።

በዚህ ጊዜ ማርያም ጴጥሮስንና ዮሐንስን አግኝታ “ጌታን ከመቃብር ወስደውታል ወዴትም እንዳኖሩት አናውቅም” አለቻቸው። ሁለቱ ሐዋርያት ወዲያውኑ መሮጥ ጀመሩ። ከሁኔታው መረዳት እንደሚቻለው ዮሐንስ ከጴጥሮስ በዕድሜ የሚያንስ በመሆኑ ይበልጥ ፈጥኖ በመሮጥ መቃብሩ ወዳለበት ቦታ ቀድሞት ደረሰ። በዚህ ጊዜ ሴቶቹ ሄደው ስለነበረ በቦታው ማንም አልነበረም። ዮሐንስ ጎንበስ ብሎ ወደ መቃብሩ ውስጥ አትኩሮ ሲመለከት ጨርቆቹ ተቀምጠው አየ፤ ሆኖም ወደ ውስጥ አልገባም።

ጴጥሮስ ወደ መቃብሩ ሲደርስ ወደ ውስጥ ለመግባት ምንም አላመነታም። የከፈኑን ጨርቅ አንድ ቦታ ተቀምጦ አየ፤ የኢየሱስ ራስ ተጠቅልሎበት የነበረውንም ጨርቅ አየ። አንድ ቦታ ላይ ተጠቅልሎ ተቀምጦ ነበር። አሁን ዮሐንስም ወደ መቃብሩ ገባ፤ በዚህ ጊዜ ማርያም የነገረቻቸውን አመነ። ሆኖም ጴጥሮስም ሆነ ዮሐንስ ምንም እንኳ ኢየሱስ ከሞት እንደሚነሳ ብዙ ጊዜ ደጋግሞ የነገራቸው ቢሆንም ኢየሱስ እንደተነሳ አልገባቸውም። በሁኔታው ግራ ተጋብተው ሁለቱም ወደ ቤት ተመለሱ፤ ወደ መቃብሩ ተመልሳ የመጣችው ማርያም ግን እዚያው ቆየች።

ይህ በእንዲህ እንዳለ ሌሎቹ ሴቶች መላእክቱ ባዘዟቸው መሠረት ኢየሱስ ከሞት መነሳቱን ለደቀ መዛሙርቱ ለመንገር እየተጣደፉ ነበር። የቻሉትን ያህል በፍጥነት እየሮጡ ሳለ ኢየሱስ አገኛቸውና “ሰላም ለእናንተ ይሁን” አላቸው። (የ1980 ትርጉም) እነርሱም እግሮቹ ላይ ወድቀው ሰገዱለት። ከዚያም ኢየሱስ “አትፍሩ ሄዳችሁ ወደ ገሊላ እንዲሄዱ ለወንድሞቼ ተናገሩ፣ በዚያም ያዩኛል” አላቸው።

ቀደም ሲል የምድር ነውጡ ሲከሰትና መላእክቱ ሲገለጡ በጥበቃ ላይ የነበሩት ወታደሮች በጣም ከመደንገጣቸው የተነሣ በድን ሆነው ነበር። ድንጋጤያቸው ለቀቅ ሲያደርጋቸው ወዲያውኑ ወደ ከተማይቱ ሄዱና የሆነውን ሁኔታ ለካህናት አለቆቹ ነገሯቸው። ከአይሁድ “ሽማግሌዎች” ጋር ከተማከሩ በኋላ ለወታደሮቹ ጉቦ በመስጠት ጉዳዩን በምሥጢር ለመያዝ ወሰኑ። “እኛ ተኝተን ሳለን ደቀ መዛሙርቱ በሌሊት መጥተው ሰረቁት በሉ” ብለው ወታደሮቹን አዘዟቸው።

የሮማ ወታደሮች በጥበቃ ሥራ ላይ እያሉ ካንቀላፉ በሞት ሊቀጡ ይችሉ ስለነበረ ካህናቱ “ይህም [እንዳንቀላፋችሁ የሚገልጸው ወሬ] በገዢው ዘንድ የተሰማ እንደ ሆነ፣ እኛ እናስረዳዋለን እናንተም ያለ ሥጋት እንድትሆኑ እናደርጋለን” ብለው ቃል ገቡላቸው። የተሰጣቸው ጉቦ ጠቀም ያለ ስለነበረ ወታደሮቹ እንደተባሉት አደረጉ። በዚህም ምክንያት የኢየሱስ አስከሬን እንደተሰረቀ የሚገልጸው የሐሰት ወሬ በአይሁዶች መካከል በስፋት ተሰራጨ።

በመቃብሩ ቦታ የቀረችው መግደላዊት ማርያም በሐዘን ተውጣለች። ኢየሱስ የት ይሆን? ጎንበስ ብላ ወደ መቃብሩ ውስጥ ስትመለከት እንደገና የተገለጡትን ነጫጭ ልብስ የለበሱ ሁለት መላእክት ተመለከተች! አንዱ የኢየሱስ አስከሬን ተቀምጦበት በነበረው ቦታ ራስጌ ሌላው ደግሞ በግርጌው በኩል ተቀምጠው ነበር። “አንቺ ሴት፣ ስለ ምን ታለቅሻለሽ?” ብለው ጠየቋት።

ማርያም “ጌታዬን ወስደውታል” ስትል መለሰችላቸው፤ “ወዴትም እንዳኖሩት አላውቅም” አለቻቸው። ከዚያም ዞር ስትል ሌላ ሰው ተመለከተች፤ እርሱም “አንቺ ሴት፣ ስለ ምን ታለቅሻለሽ?” በማለት ያንኑ ጥያቄ ደግሞ ጠየቃት። አክሎም “ማንንስ ትፈልጊያለሽ?” አላት።

እርስዋም ይህ ሰው መቃብሩ በሚገኝበት ሥፍራ ያለውን አትክልት የሚጠብቅ አትክልተኛ መስሎአት “ጌታ ሆይ፣ አንተ ወስደኸው እንደ ሆንህ ወዴት እንዳኖርኸው ንገረኝ እኔም እወስደዋለሁ” አለችው።

ሰውዬው “ማርያም” አላት። በዚህ ጊዜ ማርያም እሷን ያነጋግርበት በነበረው የተለመደ አነጋገሩ ወዲያውኑ ኢየሱስ መሆኑን አወቀች። “ረቡኒ” (“መምህር ሆይ” ማለት ነው) አለችው። (ጋደል አድርገን የጻፍነው እኛ ነን።) በጣም ከመደሰቷ የተነሣ ተጠመጠመችበት። ሆኖም ኢየሱስ እንዲህ አላት:- “ገና ወደ አባቴ አላረግሁምና አትንኪኝ፤ ነገር ግን ወደ ወንድሞቼ ሄደሽ:- እኔ ወደ አባቴና ወደ አባታችሁ ወደ አምላኬና ወደ አምላካችሁም ዐርጋለሁ ብለሽ ንገሪአቸው።”

በዚህ ጊዜ ማርያም ሐዋርያትና ሌሎች ደቀ መዛሙርት ወደተሰበሰቡበት ቦታ እየሮጠች ሄደች። ሌሎቹ ሴቶች ከሞት የተነሣውን ኢየሱስ እንዳዩ በተናገሩት ሪፖርት ላይ የእሷን ታሪክ አከለችበት። ሆኖም፣ የመጀመሪያዎቹን ሴቶች ያላመኑት እነዚህ ሰዎች ማርያምንም ያመኗት አይመስልም። ማቴዎስ 28:​3-15፤ ማርቆስ 16:​5-8፤ ሉቃስ 24:​4-12፤ ዮሐንስ 20:​2-18

▪ መግደላዊት ማርያም መቃብሩን ባዶ ሆኖ ካገኘችው በኋላ ምን አደረገች? ሌሎቹ ሴቶችስ ምን ሁኔታ አጋጠማቸው?

▪ ጴጥሮስና ዮሐንስ መቃብሩ ባዶ ሆኖ ሲያገኙት ምን ተሰማቸው?

▪ ሌሎቹ ሴቶች ኢየሱስ ከሞት መነሣቱን ለደቀ መዛሙርቱ ሊነግሩ እየሄዱ ሳለ መንገድ ላይ ምን አጋጠማቸው?

▪ ሲጠብቁ የነበሩት ወታደሮች የደረሰባቸው ነገር ምንድን ነው? የተፈጸመውን ሁኔታ ለካህናቱ ሲናገሩ የተሰጣቸው ምላሽ ምን ነበር?

▪ መግደላዊት ማርያም ብቻዋን በመቃብሩ ቦታ ሳለች ምን ሁኔታ ተፈጸመ? ሴቶቹ ላቀረቡት ሪፖርት ደቀ መዛሙርቱ ያሳዩት ምላሽ ምን ነበር?