በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ኢየሱስ ሰባዎቹን ላከ

ኢየሱስ ሰባዎቹን ላከ

ምዕራፍ 72

ኢየሱስ ሰባዎቹን ላከ

ጊዜው 32 እንደ ዘመናችን አቆጣጠር የመከር ወራት ሲሆን ኢየሱስ ከተጠመቀ ድፍን ሦስት ዓመት ሆኖታል። እርሱና ደቀ መዛሙርቱ በቅርቡ የዳስ በዓልን በኢየሩሳሌም አክብረዋል፤ አሁንም ያሉት በዚያው አካባቢ ሳይሆን አይቀርም። እንዲያውም ኢየሱስ የተቀሩትን ስድስት የአገልግሎት ወራት በአብዛኛው ያሳለፈው በይሁዳ አሊያም በዚያው አቅራቢያ ከዮርዳኖስ ወንዝ ባሻገር በሚገኘው በፍርጊያ አውራጃ ነው። ይህም ክልል መሸፈን ያስፈልገው ነበር።

እርግጥ ነው፣ ኢየሱስ በ30 እንደ ዘመናችን አቆጣጠር ከተከበረው የማለፍ በዓል በኋላ በይሁዳ ውስጥ ለስምንት ወራት ያህል ሰብኳል። ሆኖም በ31 እንደ ዘመናችን አቆጣጠር በተከበረው የማለፍ በዓል ወቅት በዚያ የሚገኙ አይሁዶች ሊገድሉት ከሞከሩ በኋላ በቀጣዩ አንድ ዓመት ተኩል ጊዜ ያስተማረው በገሊላ ብቻ ነበር ማለት ይቻላል። በዚያ ጊዜ በደንብ የሠለጠኑና የተደራጁ ብዙ ሰባኪዎች አፍርቶ ነበር፤ ከዚያ በፊት ግን እንዲህ አላደረገም ነበር። ስለዚህ አሁን በይሁዳ ውስጥ የመጨረሻ ሰፊ የስብከት ዘመቻ ጀመረ።

ኢየሱስ ይህን ዘመቻ የጀመረው 70 ደቀ መዛሙርትን መርጦ ሁለት ሁለት እያደረገ በመላክ ነው። ስለዚህ በጠቅላላ በክልሉ ውስጥ የሚሠሩ 35 የመንግሥቱ ሰባኪዎች ቡድኖች ነበሩ። እነዚህ ሰባኪዎች ኢየሱስ ከሐዋርያቱ ጋር ሆኖ ሊሄድ ወዳሰበባቸው ከተሞችና ቦታዎች ሁሉ አስቀድመው ተላኩ።

ኢየሱስ ሰባዎቹን ወደ ምኩራቦች እንዲሄዱ አላዘዛቸውም፤ ከዚህ ይልቅ “ወደምትገቡበት ቤት ሁሉ አስቀድማችሁ:- ሰላም ለዚህ ቤት ይሁን በሉ። በዚያም የሰላም ልጅ ቢኖር፣ ሰላማችሁ ያድርበታል” በማለት ወደ ግል ቤቶች እንዲገቡ አዟቸዋል። የሚያሰሙት መልእክትስ ምንድን ነው? ኢየሱስ “የእግዚአብሔር መንግሥት ወደ እናንተ ቀረበች በሉአቸው” ሲል ተናግሯል። ሰባዎቹ ያከናወኑትን ሥራ በተመለከተ የማቲው ሄንሪ ማብራሪያ (Matthew Henry’s Commentary) “ልክ እንደ ጌታቸው እነርሱም በሄዱበት ሁሉ ከቤት ወደ ቤት ሰብከዋል” ሲል ይገልጻል።

ኢየሱስ ለሰባዎቹ የሰጠው መመሪያ ከአንድ ዓመት በፊት አሥራ ሁለቱን በገሊላ የስብከት ዘመቻ እንዲያካሄዱ በላካቸው ጊዜ ከሰጣቸው መመሪያ ጋር ተመሳሳይ ነው። ለሚያገኟቸው የቤት ባለቤቶች መልእክቱን እንዲያቀርቡ ሰባዎቹን ሲያዘጋጃቸው ሊያጋጥማቸው የሚችለውን ተቃውሞ በመንገር ብቻ አላበቃም። ከዚህ ይልቅ ሕሙማንን የመፈወስ ሥልጣን ሰጥቷቸዋል። በመሆኑም ኢየሱስ ከጥቂት ጊዜ በኋላ ሲሄድ ብዙዎች እንዲህ ዓይነት አስደናቂ ነገሮች መፈጸም የሚችሉ ደቀ መዛሙርት ያሉትን ጌታ ለማግኘት በጣም ይጓጓሉ።

ሰባዎቹ ያከናወኑት ስብከትና ኢየሱስ ከእነሱ በኋላ ያከናወነው ቀጣይ ሥራ በአንጻራዊ ሁኔታ ሲታይ ለአጭር ጊዜ የቆየ ነበር። ከጥቂት ጊዜ በኋላ 35ቱ የመንግሥቱ ሰባኪዎች ቡድኖች ወደ ኢየሱስ መመለስ ጀመሩ። በደስታ ተሞልተው “ጌታ ሆይ፣ አጋንንት ስንኳ በስምህ ተገዝተውልናል” አሉት። እንዲህ ዓይነቱ ጥሩ የአገልግሎት ሪፖርት ኢየሱስን እንዳስደሰተው ምንም አያጠራጥርም፤ በመሆኑም እንዲህ አላቸው:- “ሰይጣንን እንደ መብረቅ ከሰማይ ሲወድቅ አየሁ። እነሆ፣ እባቡንና ጊንጡን ትረግጡ ዘንድ፣ . . . ሥልጣን ሰጥቻችኋለሁ።”

ኢየሱስ በፍጻሜው ዘመን የአምላክ መንግሥት ከተወለደች በኋላ ሰይጣንና አጋንንቱ ከሰማይ እንደሚባረሩ ያውቅ ነበር። ሆኖም አሁን የማይታዩ አጋንንትን ተራ የሆኑ ሰዎች ማስወጣት መቻላቸው ወደፊት ለሚፈጸመው ለዚህ ድርጊት ተጨማሪ ማረጋገጫ ሆነለት። በዚህም የተነሣ ኢየሱስ ወደፊት ሰይጣን ከሰማይ እንደሚጣል በሙሉ እርግጠኝነት መናገሩ ነበር። ስለዚህ ሰባዎቹ እባቦችንና ጊንጦችን የመርገጥ ሥልጣን የተሰጣቸው በምሳሌያዊ አባባል ነበር። ሆኖም ኢየሱስ “መናፍስት ስለ ተገዙላችሁ በዚህ ደስ አይበላችሁ፣ ስማችሁ ግን በሰማያት ስለ ተጻፈ ደስ ይበላችሁ” አላቸው።

ኢየሱስ አባቱ እነዚህን ተራ አገልጋዮቹን በእንዲህ ዓይነት ውጤታማ መንገድ ስለተጠቀመባቸው በጣም ከመደሰቱም በላይ በሕዝብ ፊት አመስግኖታል። ወደ ደቀ መዛሙርቱ ዞር አለና እንዲህ አላቸው:- “እናንተ የምታዩትን የሚያዩ ዓይኖች ብፁዓን [“ደስተኞች፣” NW] ናቸው። እላችኋለሁና፣ እናንተ የምታዩትን ብዙዎች ነቢያትና ነገሥታት ሊያዩ ወደዱ አላዩምም፣ የምትሰሙትንም ሊሰሙ ወድደው አልሰሙም።” ሉቃስ 10:​1-24፤ ማቴዎስ 10:​1-42፤ ራእይ 12:​7-12

▪ ኢየሱስ በመጀመሪያዎቹ ሦስት የአገልግሎቱ ዓመታት የሰበከው የት ነው? በመጨረሻዎቹ ስድስት ወራት የሸፈነው ክልልስ የትኛው ነው?

▪ ኢየሱስ ሰባዎቹን የላከው ሰዎችን የት ሄደው እንዲያነጋግሩ ነው?

▪ ኢየሱስ ሰይጣን ከሰማይ ሲወረወር እንዳየ አድርጎ የተናገረው ለምንድን ነው?

▪ ሰባዎቹ እባቦችንና ጊንጦችን መርገጥ የሚችሉት ከምን አንጻር ነው?