በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ኢየሱስ በሺህ የሚቆጠሩ ሰዎችን በተአምር መገበ

ኢየሱስ በሺህ የሚቆጠሩ ሰዎችን በተአምር መገበ

ምዕራፍ 52

ኢየሱስ በሺህ የሚቆጠሩ ሰዎችን በተአምር መገበ

አሥራ ሁለቱ ሐዋርያት በመላዋ ገሊላ አስደናቂ የስብከት ጉዞ አደረጉ። ዮሐንስ ከተገደለ ከጥቂት ጊዜ በኋላ ወደ ኢየሱስ ተመለሱና ያጋጠሟቸውን አስደሳች ተሞክሮዎች ነገሩት። ኢየሱስ በጣም እንደደከማቸውና ብዙ ሰዎች ይመጡና ይሄዱ ስለነበረ ምግብ እንኳ መብላት እንዳልቻሉ በማስተዋል ‘ማረፍ እንድትችሉ ብቻችንን ወደ ምድረ በዳ እንሂድ’ አላቸው።

በጀልባቸው ተሳፈሩና ራቅ ብሎ ወደሚገኝ አንድ ሥፍራ ሄዱ። ይህ ሥፍራ የሚገኘው ከዮርዳኖስ በስተ ምሥራቅ ከቤተ ሳይዳ ባሻገር በቅፍርናሆም አቅራቢያ ሳይሆን አይቀርም። ይሁን እንጂ ወደዚያ ቦታ ሲሄዱ ብዙ ሰዎች አይተዋቸው ነበር፤ ሌሎችም ወደዚያ እንደሄዱ አወቁ። እነዚህ ሁሉ በባሕሩ ዳር ዳር በፍጥነት በእግር ተጉዘው ቀድመዋቸው ቦታው ስለ ደረሱ ጀልባዋ ቦታው ደርሳ ስትቆም ሰዎቹ እነርሱን ለማግኘት እየተጠባበቁ ነበር።

ኢየሱስ ከጀልባዋ ወርዶ የተሰበሰበውን ብዙ ሕዝብ ሲመለከት ሰዎቹ እረኛ እንደሌላቸው በጎች ስለነበሩ አዘነላቸው። ስለዚህ የታመሙትን ፈወሰና ብዙ ነገር ያስተምራቸው ጀመር።

ጊዜው በፍጥነት ነጎደ። የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት ወደ እሱ መጡና እንዲህ አሉት:- “ቦታው ምድረ በዳ ነው አሁንም መሽቶአል፤ የሚበሉት የላቸውምና በዙሪያ ወዳሉ ገጠሮችና መንደሮች ሄደው እንጀራ ለራሳቸው እንዲገዙ አሰናብታቸው።”

ይሁን እንጂ ኢየሱስ መልሶ “እናንተ የሚበሉትን ስጡአቸው” አላቸው። ከዚያም ኢየሱስ ሊያደርገው ያሰበውን ነገር በልቡ ይዞ ፊልጶስን ለመፈተን “እነዚህ እንዲበሉ እንጀራ ከወዴት እንገዛለን?” ብሎ ጠየቀው።

ከፊልጶስ አመለካከት አንፃር ነገሩ የማይቻል ነበር። ወደ 5,000 የሚጠጉ ወንዶች ነበሩ፤ ሴቶቹንና ልጆቹን ጨምሮ ደግሞ የሰዉ ቁጥር ከ10,000 ሳይበልጥ አይቀርም! ፊልጶስ “እያንዳንዳቸው ትንሽ ትንሽ እንኳ እንዲቀበሉ የሁለት መቶ ዲናር [በዚያ ዘመን አንድ ዲናር የአንድ ቀን ደሞዝ ነበር] እንጀራ አይበቃቸውም” ብሎ መለሰለት።

እንድርያስ ይህን ሁሉ ሰው መመገብ የማይቻል መሆኑን ለማመልከት ሳይሆን አይቀርም፣ ቀበል አደረገና “አምስት የገብስ እንጀራና ሁለት ዓሣ የያዘ ብላቴና በዚህ አለ” ሲል ገለጸ፤ “ነገር ግን እነዚህን ለሚያህሉ ሰዎች ይህ ምን ይሆናል?” በማለት አክሎ ተናገረ።

ጊዜው በ32 እንደ ዘመናችን አቆጣጠር ከተከበረው የማለፍ በዓል ጥቂት ቀደም ብሎ በነበረው የጸደይ ወቅት ላይ ስለነበረ በሜዳው ላይ ብዙ ሣር ነበር። ስለዚህ ኢየሱስ ሰዎቹን 50 እና 100 እያደረጉ በቡድን በቡድን ሣሩ ላይ እንዲያስቀምጧቸው ደቀ መዛሙርቱን አዘዘ። አምስቱን እንጀራና ሁለቱን ዓሦች ወሰደና ወደ ሰማይ አሻቅቦ ባረከ። ከዚያም እንጀራውንና ዓሣውን ቆራረሰ። ለደቀ መዛሙርቱ ሰጣቸውና ለሰዎቹ አከፋፈሉ። ሰዎቹ ሁሉ እስኪጠግቡ ድረስ መብላታቸው እጅግ የሚያስደንቅ ነበር!

ከዚያ በኋላ ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን “አንድ ስንኳ እንዳይጠፋ የተረፈውን ቁርስራሽ አከማቹ አላቸው።” ደቀ መዛሙርቱ እንደተባሉት ሲያደርጉ ከበሉት የተረፈው ቁርስራሽ 12 መሶብ ሙሉ ሆነ! ማቴዎስ 14:​13-21፤ ማርቆስ 6:​30-44፤ ሉቃስ 9:​10-17፤ ዮሐንስ 6:​1-13

▪ ኢየሱስ ሐዋርያቱን ብቻቸውን መሆን ወደሚችሉበት ቦታ ሊወስዳቸው የፈለገው ለምንድን ነው?

▪ ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን የት ወሰዳቸው? ለማረፍ የነበራቸው ፍላጎት ሊሳካ ያልቻለውስ ለምንድን ነው?

▪ ቀኑ ሲመሽ ደቀ መዛሙርቱ ምን ማሳሰቢያ ሰጡ? ሆኖም ኢየሱስ ሰዎቹ ያስፈልጋቸው የነበረውን ነገር ያሟላላቸው እንዴት ነው?