በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ኢየሱስ በቤተሰብ ውስጥ ያሳለፈው የልጅነት ሕይወት

ኢየሱስ በቤተሰብ ውስጥ ያሳለፈው የልጅነት ሕይወት

ምዕራፍ 9

ኢየሱስ በቤተሰብ ውስጥ ያሳለፈው የልጅነት ሕይወት

ኢየሱስ ያደገባት የናዝሬት ከተማ ትንሽና ተራ ከተማ ነበረች። ናዝሬት ከውቡ የኢዝራኤል ሸለቆ ብዙም ሳትርቅ ገሊላ ተብሎ በሚጠራው ኮረብታማ አገር የምትገኝ ከተማ ናት።

ዮሴፍና ማርያም ኢየሱስን ከግብፅ ወደዚህ ሥፍራ ይዘውት ሲመጡ ሁለት ዓመት ገደማ ሳይሆነው አይቀርም። በዚህ ጊዜ ማርያም የነበራት ልጅ ኢየሱስ ብቻ እንደነበረ ከሁኔታው መረዳት ይቻላል። ሆኖም በዚህ ሁኔታ ለረጅም ጊዜ አልቆየችም። ከጊዜ በኋላ ያዕቆብ፣ ዮሳ፣ ስምዖንና ይሁዳ ተወለዱ። በተጨማሪም ማርያምና ዮሴፍ ሴቶች ልጆችን ወልደዋል። በመጨረሻ ኢየሱስ ቢያንስ ቢያንስ ስድስት ታናናሽ ወንድሞችና እህቶች ነበሩት።

ኢየሱስ ሌሎች ዘመዶችም ነበሩት። ብዙ ኪሎ ሜትሮች ርቃ በምትገኘው በይሁዳ ስለሚኖረውና ከእሱ ቀደም ብሎ ስለተወለደው የዘመዱ ልጅ ስለ ዮሐንስ ቀደም ሲል ተምረናል። ሆኖም ያን ያህል ብዙም ሳትርቅ በገሊላ ውስጥ የምትኖር ሰሎሜ የምትባል ዘመድም ነበረችው። ሰሎሜ የማርያም እህት ሳትሆን አትቀርም። ሰሎሜ ዘብዴዎስን ያገባች በመሆኑ ሁለቱ ልጆቻቸው ማለትም ያዕቆብና ዮሐንስም የኢየሱስ የአክስት ልጆች ነበሩ። ኢየሱስ በልጅነቱ ከእነዚህ ልጆች ጋር ብዙ ጊዜ ያሳልፍ እንደነበረና እንዳልነበረ አናውቅም፤ ሆኖም ከጊዜ በኋላ የቅርብ ጓደኛሞች ሆነዋል።

ዮሴፍ በቁጥር እያደገ የመጣውን ቤተሰቡን ለማስተዳደር ተግቶ መሥራት ነበረበት። ዮሴፍ አናጢ ነበር። ኢየሱስን እንደ ራሱ ልጅ አድርጎ ስላሳደገው ኢየሱስ “የጸራቢ ልጅ” ተብሎ ተጠርቷል። ዮሴፍ ኢየሱስን የአናጢነት ሙያ አስተምሮታል፤ ኢየሱስም ይህን ሙያ በሚገባ ተምሯል። ከጊዜ በኋላ ሰዎች ኢየሱስን “ጸራቢው” ብለው የጠሩት ለዚህ ነው።

የዮሴፍ ቤተሰብ ኑሮ ከይሖዋ አምላክ አምልኮ ጋር የተሳሰረ ነበር። ዮሴፍና ማርያም የአምላክን ሕግ በማክበር ልጆቻቸውን ‘በቤታቸው ሲቀመጡ፣ በመንገድ ሲሄዱ፣ ሲተኙና ሲነሡ’ መንፈሳዊ ትምህርት ይሰጧቸው ነበር። ናዝሬት ውስጥ ምኩራብ ነበር፤ ስለዚህ ዮሴፍ በዚያ በሚካሄደው የአምልኮ ሥርዓት ላይ ለመካፈል ዘወትር ቤተሰቡን ይዞ ይሄድ እንደነበር እርግጠኞች መሆን እንችላለን። ሆኖም ከሁሉ የበለጠ ይደሰቱ የነበረው በኢየሩሳሌም ወደሚገኘው የይሖዋ ቤተ መቅደስ ይደረጉ በነበሩት መደበኛ ጉዞዎች እንደነበረ ምንም አያጠራጥርም። ማቴዎስ 13:​55, 56፤ 27:​56፤ ማርቆስ 15:​40፤ 6:​3፤ ዘዳግም 6:​6-9

▪ ኢየሱስ ቢያንስ ቢያንስ ስንት ታናናሽ ወንድሞችና እህቶች ነበሩት? የአንዳንዶቹስ ስም ማን ነው?

▪ በደንብ የሚታወቁት ሦስቱ የኢየሱስ ዘመዶች ልጆች እነማን ናቸው?

▪ ከጊዜ በኋላ ኢየሱስ ምን ሰብዓዊ ሥራ መሥራት ጀመረ? ለምንስ?

▪ ዮሴፍ ለቤተሰቡ ምን በጣም አስፈላጊ የሆነ ትምህርት ይሰጥ ነበር?