በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ኢየሱስ በኢያሪኮ አስተማረ

ኢየሱስ በኢያሪኮ አስተማረ

ምዕራፍ 99

ኢየሱስ በኢያሪኮ አስተማረ

ኢየሱስና አብረውት የሚጓዙት ብዙ ሰዎች ከጥቂት ጊዜ በኋላ ኢያሪኮ ደረሱ። ኢያሪኮ ከኢየሩሳሌም የአንድ ቀን መንገድ ያህል ርቃ የምትገኝ ከተማ ነች። ኢያሪኮ ሁለት ከተሞችን አጣምራ የያዘች ይመስላል፤ የጥንቱ የአይሁዶች ከተማ ከአዲሱ የሮማውያን ከተማ አንድ ኪሎ ሜትር ተኩል ገደማ ርቆ ይገኛል። ሕዝቡ ከጥንቱ ከተማ ወጥተው ወደ አዲሱ ከተማ ሲቃረቡ ሁለት ዓይነ ስውር ለማኞች ውካታውን ሰሙ። ከዓይነ ስውሮቹ አንዱ በርጤሜዎስ ይባላል።

በርጤሜዎስና ጓደኛው ኢየሱስ በዚያ በኩል እያለፈ መሆኑን ሲረዱ “ጌታ ሆይ፣ የዳዊት ልጅ ማረን” እያሉ መጮኽ ጀመሩ። ሕዝቡ ተቆጥተው ዝም እንዲሉ ሲነግሯቸው ጭራሽ ድምፃቸውን ከፍ አድርገው “ጌታ ሆይ፣ የዳዊት ልጅ፣ ማረን” እያሉ ጮኹ።

ኢየሱስ ረብሻውን ሰማና ቆመ። የሚጮኹትን ሰዎች እንዲያመጧቸው አብረውት የነበሩትን ሰዎች አዘዛቸው። ሰዎቹ ዓይነ ስውር ወደሆኑት ለማኞች ሄዱና አንደኛውን “አይዞህ፣ ተነሣ፣ ይጠራሃል” አሉት። ዓይነ ስውሩ በጣም ከመደሰቱ የተነሣ ከላይ የደረበውን ልብስ ጥሎ በመዝለል ወደ ኢየሱስ መጣ።

ኢየሱስ “ምን ላደርግላችሁ ትወዳላችሁ?” ሲል ጠየቃቸው።

ሁለቱ ዓይነ ስውሮች “ጌታ ሆይ፣ ዓይኖቻችን ይከፈቱ ዘንድ” ብለው ለመኑት።

ኢየሱስ አዘነላቸውና ዓይኖቻቸውን ዳሰሰ። የማርቆስ ዘገባ በሚገልጸው መሠረት ኢየሱስ ከሁለቱ ለአንዱ “ሂድ፤ እምነትህ አድኖሃል” አለው። ዓይነ ስውራኑ ለማኞች ወዲያውኑ ማየት ቻሉ፤ ሁለቱም አምላክን እንዳከበሩ ጥርጥር የለውም። ሰዎቹ ሁሉ የተፈጸመውን ነገር ሲመለከቱ እነርሱም አምላክን አመሰገኑ። በርጤሜዎስና ጓደኛው ምንም ሳያመነቱ ኢየሱስን ተከተሉት።

ኢየሱስ በኢያሪኮ በኩል ሲያልፍ በጣም ብዙ ሕዝብ ይከተለው ነበር። ሁሉም ሰው ዓይነ ስውሮቹን የፈወሰውን ሰው ለማየት ፈልጓል። ሰዎቹ ኢየሱስን ዙሪያውን ከበው ተጨናንቀው ይሄዱ ስለነበር አንዳንዶች በጨረፍታ እንኳ ሊያዩት አልቻሉም። ከእነዚህ ሰዎች አንዱ በኢያሪኮና በአካባቢዋ የተሰማሩት ቀረጥ ሰብሳቢዎች አለቃ የሆነው ዘኬዎስ ነበር። በጣም አጭር ስለነበረ ምን እየተከናወነ እንዳለ ማየት አልቻለም።

ስለዚህ ዘኬዎስ ቀድሟቸው ሮጠና ኢየሱስ በሚያልፍበት መንገድ አጠገብ ባለ አንድ ሾላ ላይ ወጣ። እዚህ ምቹ ቦታ ላይ ሆኖ ሁሉንም ነገር በደንብ መመልከት ይችላል። ሕዝቡ ዘኬዎስ ወዳለበት ቦታ ሲቃረቡ ኢየሱስ ወደ ዛፉ ቀና ብሎ “ዘኬዎስ ሆይ፣ ዛሬ በቤትህ እውል ዘንድ ይገባኛልና ፈጥነህ ውረድ” አለው። ዘኬዎስ በጣም ተደስቶ ከዛፉ ላይ ወረደና ወደ ቤቱ ለሚመጣው ታላቅ እንግዳ አንዳንድ ነገሮች ለማዘጋጀት በፍጥነት ወደ ቤቱ ሄደ።

ይሁን እንጂ ሰዎቹ ምን እየተከናወነ እንዳለ ሲመለከቱ ሁሉም ማጉረምረም ጀመሩ። ኢየሱስ በእንዲህ ዓይነት ሰው ቤት በእንግድነት መስተናገዱ ተገቢ አይደለም የሚል ስሜት አደረባቸው። ዘኬዎስ ሀብታም የሆነው በቀረጥ ሰብሳቢነት ሥራው በማጭበርበር ገንዘብ አለአግባብ እያስከፈለ ይወስድ ስለነበረ ነው።

ኢየሱስን ብዙ ሰዎች ተከተሉት፤ ወደ ዘኬዎስ ቤት ሲገባም “ከኃጢአተኛ ሰው ጋር ሊውል ገባ” በማለት አጉረመረሙ። ሆኖም ኢየሱስ ዘኬዎስ ንስሐ ሊገባ እንደሚችል አስተውሎ ነበር። ደግሞም ኢየሱስ የጠበቀው ነገር ተፈጽሟል። ዘኬዎስ ተነስቶ ቆመና እንዲህ አለ:- “ጌታ ሆይ! እነሆ ካለኝ ሀብት ሁሉ እኩሌታውን ለድኾች እሰጣለሁ፤ በማታለል ከሰው ላይ የወሰድኩትም ገንዘብ ቢኖር፣ አራት እጥፍ አድርጌ እመልሳለሁ።”​— የ1980 ትርጉም

ዘኬዎስ ካለው ንብረት ውስጥ ግማሹን ለድሆች በመስጠትና የተቀረውን ደግሞ ገንዘብ ላጭበረበራቸው ሰዎች መልሶ ለመክፈል በመጠቀም እውነተኛ ንስሐ መግባቱን አሳይቷል። ከእነዚህ ሰዎች የወሰደው ገንዘብ ምን ያህል እንደሆነ ቀረጥ ከሰበሰበበት መዝገብ ላይ ማስላት ሳይችል አይቀርም። ስለዚህ ‘ሰው በግ ቢሰርቅ፣ በበጉም ፋንታ አራት በጎች ይክፈል’ ከሚለው የአምላክ ሕግ ጋር በመስማማት አራት እጥፍ አድርጎ ለመመለስ ቃል ገባ።

ዘኬዎስ ንብረቱን ለማከፋፈል ቃል የገባበት መንገድ ኢየሱስን አስደሰተው፤ በመሆኑም እንዲህ አለ:- “እርሱ ደግሞ የአብርሃም ልጅ ነውና ዛሬ ለዚህ ቤት መዳን ሆኖለታል፤ የሰው ልጅ የጠፋውን ሊፈልግና ሊያድን መጥቶአልና።”

ከጥቂት ጊዜ በፊት ኢየሱስ ስለ አባካኙ ልጅ በተናገረው ታሪክ ላይ ‘የጠፉ ሰዎችን’ ሁኔታ በምሳሌ አስረድቶ ነበር። አሁን ግን ጠፍቶ የነበረና እንደገና የተገኘን ሰው እውነተኛ የሕይወት ታሪክ ምሳሌ ተመልክተናል። ምንም እንኳ ሃይማኖታዊ መሪዎቹና እነርሱን የሚከተሉት ሰዎች ኢየሱስ እንደ ዘኬዎስ ላሉ ሰዎች ትኩረት በመስጠቱ ቢያጉረመርሙና ቢቃወሙም ኢየሱስ እነዚህን የጠፉ የአብርሃም ልጆች መፈለጉንና መመለሱን ቀጥሏል። ማቴዎስ 20:​29-34፤ ማርቆስ 10:​46-52፤ ሉቃስ 18:​35 እስከ 19:​10፤ ዘጸአት 22:​1

▪ ኢየሱስ ዓይነ ስውሮቹን ለማኞች ያገኛቸው የት ሳይሆን አይቀርም? ምንስ አደረገላቸው?

▪ ዘኬዎስ ማን ነው? ዛፍ ላይ የወጣውስ ለምንድን ነው?

▪ ዘኬዎስ ንስሐ መግባቱን ያሳየው እንዴት ነው?

▪ ኢየሱስ ለዘኬዎስ ካደረገለት ነገር ምን ትምህርት ልናገኝ እንችላለን?