በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ኢየሱስ ተቃዋሚዎቹን አወገዘ

ኢየሱስ ተቃዋሚዎቹን አወገዘ

ምዕራፍ 109

ኢየሱስ ተቃዋሚዎቹን አወገዘ

ኢየሱስ ሃይማኖታዊ ተቃዋሚዎቹን አፋቸውን ስላስያዛቸው ሌላ ነገር ለመጠየቅ ፈሩ። ስለዚህ ራሱ ቅድሚያውን ወስዶ በማነጋገር ድንቁርናቸውን አጋለጠባቸው። “ስለ ክርስቶስ ምን ይመስላችኋል?” ሲል ጠየቃቸው። “የማንስ ልጅ ነው?”

ፈሪሳውያን “የዳዊት” ብለው መለሱለት።

ኢየሱስ ምንም እንኳ ዳዊት የክርስቶስ ወይም የመሲሑ ሥጋዊ ቅድመ አያት መሆኑን ባይክድም እንዲህ ሲል ጠየቃቸው:- “እንኪያስ ዳዊት:- ጌታ ጌታዬን:- ጠላቶችህን የእግርህ መረገጫ እስካደርግልህ ድረስ በቀኜ ተቀመጥ አለው ሲል እንዴት በመንፈስ [በ⁠መዝሙር 110 ላይ] ጌታ ብሎ ይጠራዋል? ዳዊትስ ጌታ ብሎ ከጠራው፣ እንዴት ልጁ ይሆናል?”

ፈሪሳውያን የክርስቶስን ወይም የተቀባውን እውነተኛ ማንነት ስለማያውቁ ዝም አሉ። ፈሪሳውያን መሲሑ የዳዊት ሰብዓዊ ዝርያ እንደሆነ ብቻ አድርገው ያምኑ የነበረ ይመስላል፤ ሆኖም መሲሑ የዳዊት ዝርያ ብቻ ሳይሆን በሰማይ ይኖር የነበረና የዳዊት የበላይ ወይም ጌታ ነው።

አሁን ኢየሱስ ወደ ሕዝቡና ወደ ደቀ መዛሙርቱ ዞረና ከጻፎችና ከፈሪሳውያን እንዲጠበቁ ማስጠንቀቂያ ሰጣቸው። ‘በሙሴ ወንበር ተቀምጠው’ የአምላክ ሕግ የሚያስተምሩ በመሆናቸው ኢየሱስ “ያዘዙአችሁን ሁሉ አድርጉ ጠብቁትም” በማለት አጥብቆ መከራቸው። ሆኖም “እየተናገሩ አያደርጉትምና እንደ ሥራቸው አታድርጉ” ሲል አክሎ ተናግሯል።

ግብዞች ናቸው። ኢየሱስ ከተወሰኑ ወራት በፊት በአንድ ፈሪሳዊ ቤት ተጋብዞ በነበረበት ጊዜ የተናገረውን አባባል በመጠቀም አወገዛቸው። “ለሰውም እንዲታዩ ሥራቸውን ሁሉ ያደርጋሉ” ሲል ተናገረ። በተጨማሪም የሚከተሉትን ምሳሌዎች አቀረበ:-

“አሸንክታባቸውን ያሰፋሉ።” እነዚህ በአንጻራዊ ሁኔታ ሲታዩ አነስተኛ የሆኑ በግንባር ላይ ወይም በክንድ ላይ የሚታሠሩ ክታቦች የሕጉን አራት ክፍሎች ይኸውም ዘጸአት 13:​1-10, ዘጸአት 13:11-16ን፣ ዘዳግም 6:​4-9⁠ንና ዘዳግም 11:​13-21ን የያዙ ናቸው። ሆኖም ፈሪሳውያን ለሕጉ ቀናተኞች ናቸው እንዲባሉ የእነዚህን ክታቦች መጠን አሳድገው ነበር።

ኢየሱስ በመቀጠል “የልብሳቸውን ዘርፍ ያስረዝማሉ” ሲል ተናገረ። (የ1980 ትርጉም) እስራኤላውያን በልብሶቻቸው ጫፍ ላይ ዘርፍ እንዲያበጁ በ⁠ዘኍልቁ 15:​38-40 ላይ ታዘው ነበር። ፈሪሳውያን ግን ዘርፋቸውን ሌላ ማንኛውም ሰው ከሚያደርገው የበለጠ ያስረዝሙ ነበር። ማንኛውንም ነገር የሚያደርጉት ለታይታ ነበር! ኢየሱስ ‘የከበሬታ ስፍራ እንደሚወዱ’ ተናገረ።

የሚያሳዝነው፣ የእሱም ደቀ መዛሙርት ልክ እንደዚሁ የላቀ ቦታ የማግኘት ፍላጎት ተጠናውቷቸው ነበር። ስለዚህ የሚከተለውን ምክር ሰጠ:- “እናንተ ግን:- መምህር ተብላችሁ አትጠሩ፤ መምህራችሁ አንድ ስለ ሆነ እናንተም ሁላችሁ ወንድማማች ናችሁ። አባታችሁ አንዱ እርሱም የሰማዩ ነውና በምድር ላይ ማንንም:- አባት ብላችሁ አትጥሩ። ሊቃችሁ አንድ እርሱም ክርስቶስ ነውና:- ሊቃውንት ተብላችሁ አትጠሩ።” ደቀ መዛሙርቱ አንደኛ የመሆንን ፍላጎት ማስወገድ ነበረባቸው! ኢየሱስ ‘ከእናንተም የሚበልጠው አገልጋያችሁ ይሁን’ ሲል አጥብቆ መከራቸው።

ኢየሱስ በመቀጠል ፈሪሳውያንንና ጻፎችን በተደጋጋሚ ግብዞች እያለ በመጥራት በእነርሱ ላይ የሚደርሱ ተከታታይ ወዮታዎችን ተናግሯል። “መንግሥተ ሰማያትን በሰው ፊት” እንደሚዘጉ ተናገረ። በተጨማሪም ‘በጸሎት ርዝመት እያመካኙ የመበለቶችን ቤት ይበዘብዛሉ።’

ኢየሱስ “እናንተ . . . ዕውሮች መሪዎች፣ ወዮላችሁ” ሲል ተናገረ። በገዛ ፈቃዳቸው በሚያወጧቸው ደንቦች ላይ እንደተንጸባረቀው መንፈሣዊ ነገሮችን ዝቅ አድርገው የሚመለከቱ በመሆኑ ኢየሱስ አውግዟቸዋል። ለምሳሌ ያህል ‘ማንም በቤተ መቅደሱ ቢምል ምንም አይደለም፤ በቤተ መቅደሱ ወርቅ የሚምል ግን በመሐላው ይያዛል’ ይሉ ነበር። የአምልኮ ቦታው ከነበረው መንፈሳዊ ዋጋ ይበልጥ የቤተ መቅደሱን ወርቅ ከፍ አድርገው በመመልከታቸው በመንፈስ ዕውሮች መሆናቸውን አሳይተዋል።

ከዚያም ኢየሱስ ከዚህ ቀደም እንዳደረገው ሁሉ አሁንም ፈሪሳውያን ከትናንሽ ተክሎች አሥራት ማውጣትን ወይም አንድ አሥረኛውን መክፈልን ከፍ አድርገው እየተመለከቱ ‘በሕግ ውስጥ የሚገኙትን ዋና ነገሮች ማለትም ፍርድን፣ ምሕረትንና ታማኝነትን’ ግን በመተዋቸው አውግዟቸዋል።

ኢየሱስ ፈሪሳውያንን “ዕውሮች መሪዎች፣ ትንኝን የምታጠሩ ግመልንም የምትውጡ” ብሏቸዋል። ከሚጠጡት ወይን ውስጥ ትንኝ ያወጡ የነበረው በራሪ ነፍስ ስለሆነ ብቻ ሳይሆን በሃይማኖታቸው ርኩስ ስለነበረ ነው። ሆኖም በሕጉ ውስጥ ያሉትን የበለጠ ክብደት የሚሰጣቸውን ጉዳዮች ችላ ማለታቸው በሃይማኖታቸው እንደ ርኩስ የሚታየውን ግመልን ከመዋጥ ጋር የሚመሳሰል ነው። ማቴዎስ 22:​41 እስከ 23:​24፤ ማርቆስ 12:​35-40፤ ሉቃስ 20:​41-47፤ ዘሌዋውያን 11:​4, 21-24

▪ ፈሪሳውያን ዳዊት በ⁠መዝሙር 110 ላይ ስለተናገረው ነገር ኢየሱስ በጠየቃቸው ጊዜ ዝም ያሉት ለምንድን ነው?

▪ ፈሪሳውያን ክታቦቻቸውን ያሰፉትና የልብሶቻቸውን ዘርፎች ያስረዘሙት ለምንድን ነው?

▪ ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ ምን ምክር ሰጠ?

▪ ፈሪሳውያን በገዛ ፈቃዳቸው ምን ደንቦችን አውጥተዋል? ኢየሱስ ይበልጥ ክብደት የሚሰጣቸውን ነገሮች በመተዋቸው ያወገዛቸውስ እንዴት ነው?