በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ኢየሱስ እንደገና ወደ ኢየሩሳሌም አቀና

ኢየሱስ እንደገና ወደ ኢየሩሳሌም አቀና

ምዕራፍ 82

ኢየሱስ እንደገና ወደ ኢየሩሳሌም አቀና

ኢየሱስ ብዙም ሳይቆይ ከከተማ ወደ ከተማ እንዲሁም ከመንደር ወደ መንደር እያስተማረ እንደገና መጓዝ ጀመረ። አሁን ያለው ከይሁዳ ባሻገር ከዮርዳኖስ ወንዝ ማዶ በምትገኘው የፍርጊያ አውራጃ እንደሆነ ከሁኔታው መረዳት ይቻላል። ሆኖም እየተጓዘ ያለው ወደ ኢየሩሳሌም ነው።

አንድ ሰው “ጌታ ሆይ፣ የሚድኑ ጥቂቶች ናቸውን?” ብሎ ጠየቀው፤ ሰውየው ይህን ጥያቄ እንዲያቀርብ ያነሳሳው የሚድኑት የተወሰነ ቁጥር ያላቸው ብቻ ናቸው የሚለው የአይሁዶች ፍልስፍና ሳይሆን አይቀርም። ኢየሱስ “በጠበበው በር ለመግባት ተጋደሉ [ተጣጣሩ ወይም በጭንቅ ታገሉ ማለት ነው]” ብሎ መልስ በመስጠት ሕዝቡ ለመዳን ምን ማድረግ እንደሚያስፈልግ የግድ እንዲያስቡበት አድርጓቸዋል።

ኢየሱስ በመቀጠል “ብዙዎች ሊገቡ ይፈልጋሉ አይችሉምም” ስላለ እንዲህ ዓይነቱን ብርቱ ጥረት ማድረግ ቀጠሮ የሚሰጠው ጉዳይ አይደለም። መግባት የማይችሉት ለምንድን ነው? ኢየሱስ ‘ባለቤቱ ተነሥቶ በሩን ከቆለፈ በኋላ፣ ሰዎች በውጭ ቆመው:- ጌታ ሆይ፣ ክፈትልን እያሉ በሩን ያንኳኳሉ፤ እርሱም መልሶ ከወዴት እንደሆናችሁ አላውቃችሁም፤ ሁላችሁ ዓመፀኞች ከእኔ ራቁ ይላቸዋል’ በማለት ገልጿል።

ውጪ እንዳሉ የተዘጋባቸው ሰዎች ለራሳቸው ብቻ አመቺ በሆነው ጊዜ የመጡ ይመስላል። ሆኖም በዚያን ጊዜ መግባት የሚችሉበት አጋጣሚ ተዘግቶና ተቆልፎ ነበር። ወቅቱ ለእነርሱ አመቺ ላይሆን ቢችልም እንኳ ለመግባት እንዲችሉ ቀደም ብለው መምጣት ነበረባቸው። በእርግጥም የይሖዋን አምልኮ የሕይወታቸው ዋነኛ ዓላማ ከማድረግ የሚዘገዩ ሰዎች አሳዛኝ ውጤት ይጠብቃቸዋል!

ኢየሱስ እንዲያገለግላቸው የተላከላቸው አብዛኞቹ አይሁዶች አምላክ ያዘጋጀላቸውን አስደናቂ የመዳን ዝግጅት በመቀበል መዳን የሚችሉበትን ግሩም አጋጣሚ ሳይጠቀሙበት ቀርተዋል። ስለዚህ ወደ ውጪ ሲጣሉ እንደሚያለቅሱና ጥርሳቸውን እንደሚያፋጩ ኢየሱስ ተናግሯል። በሌላ በኩል ደግሞ “ከምሥራቅና ከምዕራብም ከሰሜንና ከደቡብም” የመጡ ከሁሉም ብሔራት የተውጣጡ ሰዎች “በእግዚአብሔርም መንግሥት በማዕድ ይቀመጣሉ።”

ኢየሱስ በመቀጠል እንዲህ አለ:- “ከኋለኞች [አይሁዳውያን ካልሆኑት የተናቁ ሰዎችና ከተጨቆኑ አይሁዶች] ፊተኞች የሚሆኑ አሉ፣ ከፊተኞችም [ቁሳዊና ሃይማኖታዊ ብልጫ ካላቸው አይሁዶች] ኋለኞች የሚሆኑ አሉ።” ኋለኞች ይሆናሉ ማለት እንዲህ ዓይነቶቹ ሰነፎችና ለተደረገላቸው ነገር አመስጋኞች ያልሆኑ ሰዎች ፈጽሞ የአምላክን መንግሥት ሊወርሱ አይችሉም ማለት ነው።

በዚህ ጊዜ ፈሪሳውያን ወደ ኢየሱስ ቀረቡና “ሄሮድስ [አንቲጳስ] ሊገድልህ ይወዳልና ከዚህ ውጣና ሂድ” አሉት። ኢየሱስ በፍጥነት ክልሉን ለቆ እንዲወጣ ለማድረግ ይህን ወሬ ያስወራው ራሱ ሄሮድስ ሊሆን ይችላል። ሄሮድስ በአጥማቂው ዮሐንስ ግድያ ውስጥ እጁ እንደነበረበት ሁሉ አሁን ደግሞ በሌላ የአምላክ ነቢይ ግድያ ውስጥ እጁን እንዳያስገባ ፈርቶ ይሆናል። ሆኖም ኢየሱስ ፈሪሳውያኑን እንዲህ አላቸው:- “ሄዳችሁ ለዚያች ቀበሮ:- እነሆ፣ ዛሬና ነገ አጋንንትን አወጣለሁ በሽተኞችንም እፈውሳለሁ፣ በሦስተኛውም ቀን እፈጸማለሁ በሉአት።”

ኢየሱስ በዚያ ሲያከናውነው የነበረውን ሥራ ከጨረሰ በኋላ ወደ ኢየሩሳሌም ጉዞውን ቀጠለ። ወደዚያ የተጓዘበትን ምክንያት ሲገልጽ “ነቢይ ከኢየሩሳሌም ውጭ ይጠፋ ዘንድ አይገባም” ብሏል። ኢየሱስ የሚገደለው በኢየሩሳሌም ነው ብሎ መጠበቁ ተገቢ የሆነው ለምንድን ነው? ኢየሩሳሌም 71 አባላት ያሉት የሳንሄድሪን ከፍተኛ የፍርድ ሸንጎ የሚገኝባትና የእንስሳት መሥዋዕት የሚቀርብባት ዋና ከተማ ስለሆነች ነው። ስለዚህ “የእግዚአብሔር በግ” ከኢየሩሳሌም ውጪ በሌላ ቦታ መገደሉ ተገቢ ሊሆን አይችልም።

“ኢየሩሳሌም፣ ኢየሩሳሌም፣ ነቢያትን የምትገድል ወደ እርስዋ የተ​ላኩትንም የምትወግር፣” በማለት ኢየሱስ በምሬት ተናግሯል፤ “ዶሮ ጫጩቶችዋን በክንፎችዋ በታች እንደምትሰበስብ ልጆችሽን እሰበስብ ዘንድ ስንት ጊዜ ወደድሁ፣ እናንተም አልወደዳችሁም። እነሆ፣ ቤታችሁ የተፈታ ሆኖ ይቀርላችኋል።” ሕዝቡ የአምላክን ልጅ አልቀበልም በማለቱ ጥፋት ተፈርዶበታል!

ኢየሱስ ወደ ኢየሩሳሌም እየተጓዘ ሳለ በአንድ የፈሪሳውያን አለቃ ቤት ተጋበዘ። ቀኑ ሰንበት ነበር፤ ድሮፕሲ በተባለ ሕመም ይሠቃይ የነበረ አንድ ሰው በቦታው ተገኝቶ ስለነበረ ሰዎቹ ኢየሱስ የሚያደርገውን በትኩረት እየተከታተሉ ነበር። በበሽታው ሳቢያ ምናልባት በእጆቹና በእግሮቹ ውስጥ ፈሳሽ ነገር ተከማችቶ ሊሆን ይችላል። ኢየሱስ በቦታው የነበሩትን ፈሪሳውያንና ሕግ ዐዋቂዎች “በሰንበት መፈወስ ተፈቅዶአልን ወይስ አልተፈቀደም?” ሲል ጠየቃቸው።

መልስ የሰጠ አልነበረም። ስለዚህ ኢየሱስ ሰውየውን ፈውሶ አሰናበተው። ከዚያም “ከእናንተ በሰንበት ቀን ልጁ ወይም በሬው በጉድጓድ ውስጥ ቢወድቅበት ወዲያውኑ የማያወጣው ማን ነው?” ብሎ ጠየቃቸው። (የ1980 ትርጉም) አሁንም አንድም ሰው መልስ አልሰጠም። ሉቃስ 13:​22 እስከ 14:​6፤ ዮሐንስ 1:​29

▪ ኢየሱስ ለመዳን ምን እንደሚያስፈልግ አመልክቷል? ብዙዎች ውጪ እንዳሉ የሚዘጋባቸው ለምንድን ነው?

▪ ፊተኞች የሚሆኑት “ኋለኞች” እነማን ናቸው? ኋለኞች የሚሆኑት ‘ፊተኞችስ’?

▪ ሄሮድስ ኢየሱስን ሊገድለው እንደሚፈልግ ተደርጎ የተወራው ለምን ሊሆን ይችላል?

▪ ነቢይ ከኢየሩሳሌም ውጪ መገደሉ ተገቢ ሊሆን የማይችለው ለምንድን ነው?