በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ኢየሱስ ከቀረቡለት ፈተናዎች መማር

ኢየሱስ ከቀረቡለት ፈተናዎች መማር

ምዕራፍ 13

ኢየሱስ ከቀረቡለት ፈተናዎች መማር

ኢየሱስ ከተጠመቀ በኋላ ወዲያውኑ የአምላክ መንፈስ ወደ ይሁዳ ምድረ በዳ ወሰደው። ብዙ የሚያስብባቸው ነገሮች ነበሩ፤ ምክንያቱም ሲጠመቅ ሰማያዊ ነገሮችን ማስተዋል እንዲችል ‘ሰማያት ተከፍተው ነበር።’ በእርግጥም ብዙ የሚያሰላስልበት ነገር ነበረው!

ኢየሱስ በምድረ በዳ 40 ቀንና 40 ሌሊት ቆየ፤ በዚህ ወቅት ምንም ነገር አልበላም። ከዚያም ኢየሱስ በጣም ሲራብ ዲያብሎስ ሊፈትነው ቀረበና “የእግዚአብሔር ልጅ ከሆንህ፣ እነዚህ ድንጋዮች እንጀራ እንዲሆኑ በል” አለው። ሆኖም ኢየሱስ ተአምራዊ ኃይሉን ለግል ጥቅም ማዋሉ ስህተት መሆኑን ያውቃል። ስለዚህ ለፈተናው አልተሸነፈም።

ሆኖም ዲያብሎስ ተስፋ አልቆረጠም። ሌላ ፈተና አቀረበ። የአምላክ መላእክት ያድኑት ዘንድ ከመቅደስ ጫፍ ላይ እንዲዘል በመጠየቅ ኢየሱስን ተፈታተነው። ሆኖም ኢየሱስ እንዲህ ያለ በጣም አስደናቂ የሆነ ትዕይንት ለመሥራት አልዳዳውም። ኢየሱስ ከቅዱሳን ጽሑፎች በመጥቀስ አምላክን በዚህ መንገድ መፈታተን ትክክል እንዳልሆነ ገለጸ።

በሦስተኛ ፈተና ዲያብሎስ የዓለምን መንግሥታት በሙሉ ተአምራዊ በሆነ መንገድ ለኢየሱስ ካሳየው በኋላ “ወድቀህ ብትሰግድልኝ ይህን ሁሉ እሰጥሃለሁ” አለው። ሆኖም አሁንም ኢየሱስ ለፈተናው በመንበርከክ ስህተት ለመሥራት ፈቃደኛ አልሆነም። ለአምላክ ታማኝ ሆኖ መቆምን መርጧል።

ለኢየሱስ ከቀረቡት ከእነዚህ ፈተናዎች መማር እንችላለን። ለምሳሌ ያህል ዲያብሎስ አንዳንድ ሰዎች እንደሚሉት የክፋት ባሕርይ ሳይሆን በእውን ያለ የማይታይ አካል መሆኑን ያሳያሉ። በተጨማሪም ለኢየሱስ የቀረቡት ፈተናዎች የዓለም መንግሥታት በሙሉ የዲያብሎስ ንብረት መሆናቸውን ያመለክታሉ። ባይሆኑማ ኖሮ ዲያብሎስ እነሱን በስጦታ መልክ ለክርስቶስ ማቅረቡ እንዴት ፈተና ሊሆን ይችል ነበር?

እስቲ ይህንንም አስበው:- ኢየሱስ አንድ ጊዜ ቢሰግድለት ዲያብሎስ ጥሩ ዋጋ ለመክፈል ፈቃደኛ እንደሆነ ተናግሯል፤ እንዲያውም የዓለምን መንግሥታት ሁሉ እሰጥሃለሁ ብሎታል። ዲያብሎስ እኛንም በተመሳሳይ መንገድ ለመፈተን ይሞክር ይሆናል። ዓለማዊ ብልጽግና፣ ሥልጣን ወይም ቦታ ­እንድናገኝ የሚያስችሉ የሚያጓጉ አጋጣሚዎችን ያቀርብልን ይሆናል። ይሁን እንጂ ፈተናው ምንም ይሁን ምን ምንጊዜም ለአምላክ ታማኝ በመሆን የኢየሱስን ምሳሌ መከተላችን ብልህነት ነው! ማቴዎስ 3:​16፤ 4:​1-11፤ ማርቆስ 1:​12, 13፤ ሉቃስ 4:​1-13

▪ ኢየሱስ በምድረ በዳ በቆየባቸው 40 ቀናት ስለ የትኞቹ ነገሮች ሳያሰላስል አይቀርም?

▪ ዲያብሎስ ኢየሱስን ስሕተት እንዲሠራ የተፈታተነው እንዴት ነው?

▪ ኢየሱስ ከቀረቡለት ፈተናዎች ምን ልንማር እንችላለን?