በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ኢየሱስ የሚሞትበት ጊዜ ሲቃረብ ደቀ መዛሙርቱ ተከራከሩ

ኢየሱስ የሚሞትበት ጊዜ ሲቃረብ ደቀ መዛሙርቱ ተከራከሩ

ምዕራፍ 98

ኢየሱስ የሚሞትበት ጊዜ ሲቃረብ ደቀ መዛሙርቱ ተከራከሩ

ኢየሱስና ደቀ መዛሙርቱ ከፍርጊያ አውራጃ ወደ ይሁዳ በሚሻገሩበት የዮርዳኖስ ወንዝ አቅራቢያ ይገኛሉ። ሌሎች ብዙ ሰዎች በ33 እንደ ዘመናችን አቆጣጠር በሚከበረው የማለፍ በዓል ላይ ለመገኘት አብረዋቸው እየተጓዙ ነው። በዓሉ የቀረው አንድ ሳምንት ገደማ ብቻ ነበር።

ኢየሱስ ከደቀ መዛሙርቱ ፊት ፊት እየሄደ ነበር። ደቀ መዛሙርቱ ድፍረት በተሞላበት ቆራጥ እርምጃው በጣም ተገረሙ። ከጥቂት ሳምንታት በፊት አልዓዛር በሞተበት ጊዜ ኢየሱስ ከፍርጊያ ወደ ይሁዳ ሊሄድ ሲል ቶማስ ሌሎቹን “ከእርሱ ጋር እንሞት ዘንድ እኛ ደግሞ እንሂድ” በማለት አበረታቷቸው እንደነበረ አስታውስ። በተጨማሪም ኢየሱስ አልዓዛርን ከሞት ካስነሳው በኋላ የሳንሄድሪን ሸንጎ ኢየሱስን ለማስገደል እንዳሴረ አስታውስ። ደቀ መዛሙርቱ አሁን እንደገና ወደ ይሁዳ ተመልሰው ሲሄዱ መፍራታቸው ምንም አያስደንቅም።

ኢየሱስ አሥራ ሁለቱን ወደፊት ለሚጠብቃቸው ነገር ከወዲሁ ለማዘጋጀት ለብቻቸው ወስዶ እንዲህ አላቸው:- “እነሆ፣ ወደ ኢየሩሳሌም እንወጣለን፣ የሰው ልጅም ለካህናት አለቆችና ለጻፎች ይሰጣል፤ የሞት ፍርድም ይፈርዱበታል፣ ሊዘባበቱበትም ሊገርፉትም ሊሰቅሉትም ለአሕዛብ አሳልፈው ይሰጡታል፣ በሦስተኛውም ቀን ይነሣል።”

ኢየሱስ ከጥቂት ወራት ወዲህ ስለ ሞቱና ስለ ትንሣኤው ለደቀ መዛሙርቱ ሲናገር ይህ ሦስተኛው ጊዜ ነበር። ምንም እንኳ ይህን ሲናገር የሰሙት ቢሆንም ምን ማለቱ እንደሆነ አልገባቸውም። ይህ የሆነው የእስራኤል መንግሥት በምድር ላይ ተመልሶ እንደሚቋቋም ያምኑ ስለነበረና በምድራዊ መንግሥት ውስጥ ከክርስቶስ ጋር ክብርና ዝና የሚጎናጸፉበትን ጊዜ ይጠባበቁ ስለነበረ ሊሆን ይችላል።

የማለፍ በዓልን ለማክበር እየተጓዙ ከነበሩት ሰዎች መካከል አንዷ የሐዋርያቱ የያዕቆብና የዮሐንስ እናት የሆነችው ሰሎሜ ነበረች። ኢየሱስ እነዚህን ሰዎች “የነጐድጓድ ልጆች” ብሎ ጠርቷቸው ነበር፤ እንዲህ ያላቸው በነበራቸው የቁጠኝነት ባሕርይ እንደሆነ ጥርጥር የለውም። እነዚህ ሁለት ሰዎች በክርስቶስ መንግሥት ውስጥ ከፍ ያለ ቦታ የማግኘት ፍላጎታቸውን ለተወሰነ ጊዜ በውስጣቸው ይዘው ከቆዩ በኋላ ይህን ምኞታቸውን ለእናታቸው ገለጹላት። አሁን እናታቸው እነሱን ወክላ ወደ ኢየሱስ በመቅረብ በፊቱ ሰገደችና አንድ ውለታ እንዲውልላት ለመነችው።

ኢየሱስ “ምን ትፈልጊያለሽ?” ሲል ጠየቃት።

“እነዚህ ሁለቱ ልጆቼ አንዱ በቀኝህ አንዱም በግራህ በመንግሥትህ እንዲቀመጡ እዘዝ” ስትል መለሰችለት።

ኢየሱስ ጥያቄው የመነጨው ከየት እንደሆነ በመገንዘብ ያዕቆብንና ዮሐንስን “የምትለምኑትን አታውቁም። እኔ ልጠጣው ያለውን ጽዋ ልትጠጡ . . . ትችላላችሁን?” አላቸው።

“እንችላለን” ብለው መለሱለት። ምንም እንኳ ኢየሱስ ከባድ ስደት እንደሚገጥመውና በመጨረሻም እንደሚገደል ከጥቂት ጊዜ በፊት የነገራቸው ቢሆንም የምጠጣው “ጽዋ” ብሎ የተናገረው ነገር ይህ መሆኑን የተረዱ አይመስልም።

የሆኖ ሆኖ ኢየሱስ እንዲህ አላቸው:- “ጽዋዬንስ ትጠጣላችሁ፤ በቀኝና በግራ መቀመጥ ግን ከአባቴ ዘንድ ለተዘጋጀላቸው ነው እንጂ እኔ የምሰጥ አይደለሁም።”

ከጊዜ በኋላ ሌሎቹ አሥሩ ሐዋርያት ያዕቆብና ዮሐንስ ያቀረቡትን ልመና ሲሰሙ ተቆጡ። ምናልባትም ቀደም ሲል ሐዋርያት በመካከላቸው ታላቅ ስለሚሆነው ሰው በተከራከሩ ጊዜ ያዕቆብና ዮሐንስ በክርክሩ ላይ ጎላ ያለ ሚና ተጫውተው ሊሆን ይችላል። አሁን ያቀረቡት ጥያቄ ኢየሱስ በዚህ ጉዳይ ላይ የሰጠውን ምክር እንዳልሠሩበት የሚያሳይ ነው። ከፍ ያለ ቦታ ለማግኘት የነበራቸው ምኞት አለመለወጡ የሚያሳዝን ነበር።

ስለዚህ ኢየሱስ አሁን የተከሰተውን ውዝግብና ውዝግቡ የፈጠረውን የጥላቻ መንፈስ ለማስወገድ አሥራ ሁለቱን አንድ ላይ ጠራቸው። እንዲህ በማለት ፍቅራዊ በሆነ መንገድ መከራቸው:- “የአሕዛብ አለቆች እንዲገዙአቸው ታላላቆቹም በላያቸው እንዲሠለጥኑ ታውቃላችሁ። በእናንተስ እንዲህ አይደለም፤ ነገር ግን ማንም ከእናንተ ታላቅ ሊሆን የሚወድ የእናንተ አገልጋይ ይሁን፣ ከእናንተም ማንም ፊተኛ ሊሆን የሚወድ የእናንተ ባሪያ ይሁን።”

ኢየሱስ እንደሚከተለው ብሎ በመግለጽ ሊከተሉት የሚገባውን ምሳሌ ትቷል:- “እንዲሁም የሰው ልጅ ሊያገለግል ነፍሱንም ለብዙዎች ቤዛ ሊሰጥ እንጂ እንዲያገለግሉት አልመጣም።” ኢየሱስ ሌሎችን ከማገልገሉም በላይ ነፍሱን ለሰው ዘር አሳልፎ እስከ መስጠት ደርሷል! ደቀ መዛሙርቱም ክርስቶስ ያሳየውን ይህንኑ ዝንባሌ በማሳየት ከመገልገል ይልቅ ማገልገልን እንዲሁም ከፍ ያለ ቦታን ሳይሆን ዝቅተኛ ቦታን የሚፈልጉ መሆን አለባቸው። ማቴዎስ 20:⁠17⁠-​28፤ ማርቆስ 3:⁠17፤ 9:⁠33⁠-37፤ 10:​32-45፤ ሉቃስ 18:​31-34፤ ዮሐንስ 11:​16

▪ ደቀ መዛሙርቱ ፍርሃት ያደረባቸው ለምንድን ነው?

▪ ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን ከፊታቸው ለሚጠብቃቸው ነገር ያዘጋጃቸው እንዴት ነው?

▪ ኢየሱስ የቀረበለት ልመና ምን ነበር? ሌሎቹ ሐዋርያትስ ምን ተሰማቸው?

▪ ኢየሱስ በሐዋርያቱ መካከል ተፈጥሮ የነበረውን ችግር ያስወገደው እንዴት ነው?