በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ኢየሱስ የሚያከብረው የመጨረሻ የማለፍ በዓል ተቃረበ

ኢየሱስ የሚያከብረው የመጨረሻ የማለፍ በዓል ተቃረበ

ምዕራፍ 112

ኢየሱስ የሚያከብረው የመጨረሻ የማለፍ በዓል ተቃረበ

ኒሳን 11 ማክሰኞ እየተገባደደ ሲሄድ ኢየሱስ በደብረ ዘይት ተራራ ላይ ለሐዋርያቱ ሲሰጥ የነበረውን ትምህርት ጨረሰ። እንዴት ያለ ሥራ የበዛበትና አድካሚ ዕለት ነበር! አሁን፣ ምናልባትም በቢታንያ ለማደር ወደዚያ እየተመለሱ በነበረበት ጊዜ ሳይሆን አይቀርም፣ ኢየሱስ ሐዋርያቱን “ከሁለት ቀን በኋላ ፋሲካ [“የማለፍ በዓል፣” NW] እንዲሆን ታውቃላችሁ፣ የሰው ልጅም ሊሰቀል አልፎ ይሰጣል” አላቸው።

ኢየሱስ ቀጣዩን ቀን ማለትም ኒሳን 12 ረቡዕ ዕለትን ያሳለፈው ራሱን ከሰዎች ገለል በማድረግ ከሐዋርያቱ ጋር ብቻ ሳይሆን አይቀርም። ከዚህ ቀን በፊት በነበረው ዕለት የሃይማኖት መሪዎቹን በሕዝብ ፊት ነቅፏቸው ነበር፤ በመሆኑም ሊገድሉት እንደሚፈልጉ አውቋል። ስለዚህ በሚቀጥለው ቀን ምሽት ከሐዋርያቱ ጋር ሆኖ የሚያከብረውን የማለፍ በዓል ምንም ነገር እንዲያስተጓጉልበት ስላልፈለገ ረቡዕ ዕለት በግልጽ አልታየም።

ይህ በእንዲህ እንዳለ የካህናት አለቆቹና የሕዝቡ ሽማግሌዎች ቀያፋ በሚባለው በሊቀ ካህናቱ ግቢ ተሰበሰቡ። ቀደም ሲል በነበረው ቀን ኢየሱስ የሰነዘረባቸው ነቀፋ በጣም ስላንገበገባቸው የተንኮል ዘዴ ተጠቅመው እሱን ለመያዝና ለማስገደል ሴራ እየሸረቡ ነው። ሆኖም “በሕዝቡ ዘንድ ሁከት እንዳይነሣ በበዓል አይሁን” አሉ። ሕዝቡ ኢየሱስን ይወዱት ስለነበረ ሕዝቡን ፈርተው ነበር።

የሃይማኖት መሪዎቹ ኢየሱስን ለመግደል እያሴሩ እያለ አንድ ሰው ወደ እነሱ መጣ። ሰውዬው ከኢየሱስ ሐዋርያት አንዱ የሆነው የአስቆሮቱ ይሁዳ መሆኑ ሳያስገርማቸው አልቀረም! ሰይጣን ጌታውን አሳልፎ የመስጠት መጥፎ ሐሳብ በልቡ ውስጥ እንዲበቅል አድርጎ ነበር። ይሁዳ “ምን ልትሰጡኝ ትወዳላችሁ እኔም አሳልፌ እሰጣችኋለሁ?” ብሎ ሲጠይቃቸው ምንኛ ተደስተው ይሆን! ደስ እያላቸው 30 ብር ሊሰጡት ተስማሙ። ይህ በሙሴ ሕግ ቃል ኪዳን መሠረት የአንድ ባሪያ ዋጋ ነበር። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ይሁዳ ሕዝብ በሌለበት ቦታ ኢየሱስን ለእነርሱ አሳልፎ ለመስጠት ምቹ አጋጣሚ መፈለግ ጀመረ።

ረቡዕ ፀሐይ ከጠለቀች በኋላ ኒሳን 13 ሆነ። ኢየሱስ ከኢያሪኮ የመጣው ዓርብ ስለሆነ አሁን በቢታንያ ሲያድር ይህ ስድስተኛውና የመጨረሻው ሌሊት ነው። በሚቀጥለው ቀን ማለትም ሐሙስ ፀሐይ ከጠለቀች በኋላ መከበር ለሚጀምረው የማለፍ በዓል የመጨረሻ ዝግጅቶች መከናወን አለባቸው። የማለፍ በዓሉ በግ መታረድና ሙሉ በሙሉ መጠበስ ያለበት በዚያን ጊዜ ነው። በዓሉን የሚያከብሩት የት ነው? ዝግጅቱንስ የሚያደርግላቸው ማን ይሆን?

ኢየሱስ ይህን በዝርዝር አልተናገረም፤ ምናልባትም ይህን ያደረገው ይሁዳ ለካህናት አለቆቹ ጠቁሞ የማለፍ በዓሉ እየተከበረ እያለ እንዳያስይዘው ለማድረግ ብሎ ሊሆን ይችላል። ሆኖም አሁን፣ ሐሙስ ቀትር ላይ ሳይሆን አይቀርም፣ ኢየሱስ ጴጥሮስንና ዮሐንስን “ፋሲካን [“የማለፍ በዓልን፣” NW] እንድንበላ ሄዳችሁ አዘጋጁልን” ብሎ ከቢታንያ ላካቸው።

“ወዴት እናዘጋጅ ዘንድ ትወዳለህ?” ብለው ጠየቁት።

“እነሆ፣ ወደ ከተማ ስትገቡ” አለ ኢየሱስ፤ “ማድጋ ውኃ የተሸከመ ሰው ይገናኛችኋል፤ ወደሚገባበት ቤት ተከተሉት፤ ለባለቤቱም:- መምህሩ:- ከደቀ መዛሙርቴ ጋር ፋሲካን [“የማለፍ በዓልን፣” NW] የምበላበት የእንግዳ ቤት ክፍል ወዴት ነው? ይልሃል በሉት፤ ያም በደርብ ላይ ያለውን የተነጠፈ ታላቅ አዳራሽ ያሳያችኋል፤ በዚያም አሰናዱልን።”

የቤቱ ባለቤት የኢየሱስ ደቀ መዝሙር እንደሆነ ጥርጥር የለውም፤ ምናልባትም ኢየሱስ ይህን ልዩ በዓል በእሱ ቤት ለማክበር እንደሚጠይቀው ሲጠባበቅ ቆይቶ ሊሆን ይችላል። ያም ሆነ ይህ ጴጥሮስና ዮሐንስ ኢየሩሳሌም ሲደርሱ ሁሉም ነገር ኢየሱስ እንዳለው ሆኖ አገኙት። ስለዚህ ሁለቱ ሐዋርያት በጉ እንዲዘጋጅና የማለፍ በዓሉን የሚያከብሩት አሥራ ሦስቱ ሰዎች ማለትም ኢየሱስና አሥራ ሁለቱ ሐዋርያት የሚያስፈልጓቸው ሌሎች ነገሮች በሙሉ እንዲዘጋጁ አደረጉ። ማቴዎስ 26:​1-5, 14-19፤ ማርቆስ 14:​1, 2, 10-16፤ ሉቃስ 22:​1-13፤ ዘጸአት 21:​32

▪ ኢየሱስ ረቡዕ ዕለት ምን ሳያደርግ አይቀርም? ለምንስ?

▪ በሊቀ ካህናቱ ቤት ምን ስብሰባ ተካሄደ? ይሁዳ ወደ ሃይማኖት መሪዎቹ የሄደውስ ለምን ነበር?

▪ ኢየሱስ ሐሙስ ወደ ኢየሩሳሌም የላከው እነማንን ነው? የላካቸውስ ለምንድን ነው?

▪ እነዚህ የተላኩት ሰዎች አሁንም የኢየሱስን ተአምራዊ ኃይል የሚያሳይ ምን ነገር አገኙ?