በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ኢየሱስ የተገለጠባቸው ሌሎች ጊዜያት

ኢየሱስ የተገለጠባቸው ሌሎች ጊዜያት

ምዕራፍ 129

ኢየሱስ የተገለጠባቸው ሌሎች ጊዜያት

ደቀ መዛሙርቱ አሁንም በሐዘን እንደተዋጡ ናቸው። መቃብሩ ባዶ መሆኑ ምን ትርጉም እንዳለው አልገባቸውም፤ ሴቶቹ የነገሯቸውንም ነገር አላመኑም። ስለዚህ እሁድ ዕለት ይህ ከሆነ በኋላ ቀለዮጳና አንድ ሌላ ደቀ መዝሙር ከኢየሩሳሌም ወጥተው አሥራ አንድ ኪሎ ሜትር ገደማ ርቆ ወደሚገኘው ኤማሁስ ወደሚባለው ሥፍራ መጓዝ ጀመሩ።

በዕለቱ የተከናወኑትን ነገሮች እየተወያዩ ሲሄዱ መንገድ ላይ አንድ እንግዳ የሆነ ሰው ከእነርሱ ጋር ተቀላቀለ። ሰውዬው “በጉዞው ላይ ሳላችሁ የምትነጋገሩበት ይህ ነገር ምንድን ነው?” ሲል ጠየቃቸው።​— የ1980 ትርጉም

ደቀ መዛሙርቱ በከባድ ሐዘን ተውጠው ፊታቸውን አቀርቅረው ቆሙ፤ ከዚያም ቀለዮጳ “አንተ በኢየሩሳሌም እንግዳ ሆነህ ለብቻህ ትኖራለህን? በእነዚህ ቀኖች በዚያ የሆነውን ነገር አታውቅምን?” ሲል መለሰለት። ሰውዬውም “ይህ ምንድር ነው?” ሲል ጠየቃቸው።

“በናዝሬቱ ኢየሱስ ላይ ስለተፈጸመው ነገር ነዋ!” ብለው መለሱለት። (የ1980 ትርጉም) “እርሱንም የካህናት አለቆችና መኳንንቶቻችን ለሞት ፍርድ እንዴት አሳልፈው እንደ ሰጡትና እንደ ሰቀሉት ነው። እኛ ግን እስራኤልን እንዲቤዥ ያለው እርሱ እንደ ሆነ ተስፋ አድርገን ነበር።”

ቀለዮጳና ጓደኛው በዕለቱ የተፈጸሙትን እጅግ አስገራሚ የሆኑ ነገሮች ማለትም መላእክት እንደታዩና መቃብሩ ባዶ እንደሆነ የሚገልጸውን አስገራሚ ሪፖርት ገለጹለት፤ ሆኖም የእነዚህ ነገሮች ትርጉም እንዳልገባቸው አልሸሸጉትም። ሰውዬው እንዲህ ሲል ወቀሳቸው:- “እናንተ የማታስተውሉ፣ ነቢያትም የተናገሩትን ሁሉ ልባችሁ ከማመን የዘገየ፤ ክርስቶስ ይህን መከራ ይቀበል ዘንድና ወደ ክብሩ ይገባ ዘንድ ይገባው የለምን?” ከዚያም በቅዱስ ጽሑፉ ውስጥ የሚገኙትን ስለ ክርስቶስ የሚናገሩትን ክፍሎች አብራራላቸው።

በመጨረሻ ወደ ኤማሁስ አቅራቢያ ደረሱ፤ ሰውዬው ጉዞውን የሚቀጥል መሰለ። ደቀ መዛሙርቱ ይበልጥ መስማት ስለፈለጉ “ከእኛ ጋር እደር፣ ማታ ቀርቦአልና” ብለው አጥብቀው ለመኑት። ስለዚህ ከእነርሱ ጋር ቆየና አብሯቸው በማዕድ ተቀመጠ። ከጸለየ በኋላ እንጀራውን ቆርሶ ሲሰጣቸው ኢየሱስ ሰብዓዊ የሆነ ሥጋዊ አካል ለብሶ እንደተገለጠላቸው ተገነዘቡ። ሆኖም ከዚያ በኋላ ኢየሱስ ተሰወረ።

አሁን ሰውዬው እንዴት ብዙ ነገር ሊያውቅ እንደቻለ ገባቸው! እርስ በርሳቸውም “በመንገድ ሲናገረን መጻሕፍትንም ሲከፍትልን ልባችን ይቃጠልብን አልነበረምን?” ተባባሉ። ምንም ጊዜ ሳያጠፉ ወዲያውኑ ተነሥተው በፍጥነት ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሱ፤ እዚያም ሐዋርያቱንና አብረዋቸው ተሰብስበው የነበሩትን ሰዎች አገኟቸው። ቀለዮጳና ጓደኛው ገና አንድም ቃል ሳይተነፍሱ ሌሎቹ በደስታ ስሜት ተውጠው “ጌታ በእውነት ተነሥቶአል ለስምዖንም ታይቶአል” ብለው ነገሯቸው። ከዚያም ሁለቱ ኢየሱስ ለእነርሱም እንዴት እንደተገለጠላቸው ተረኩላቸው። ስለዚህ ኢየሱስ በዚያ ቀን ውስጥ ለተለያዩ ደቀ መዛሙርቱ ሲገለጥ ይህ ለአራተኛ ጊዜ መሆኑ ነው።

ኢየሱስ በድንገት ለአምስተኛ ጊዜ ተገለጠ። ምንም እንኳ ደቀ መዛሙርቱ አይሁዶችን በመፍራታቸው በሮቹን ቆልፈዋቸው የነበረ ቢሆንም ኢየሱስ ገብቶ በመካከላቸው ቆመና “ሰላም ለእናንተ ይሁን” አላቸው። መንፈስ ያዩ መስሏቸው በጣም ፈሩ። ስለዚህ ኢየሱስ ጣረሞት አለመሆኑን በመግለጽ እንዲህ አላቸው:- “ስለ ምን ትደነግጣላችሁ? ስለ ምንስ አሳብ በልባችሁ ይነሣል? እኔ ራሴ እንደ ሆንሁ እጆቼንና እግሮቼን እዩ፤ በእኔ እንደምታዩት፣ መንፈስ ሥጋና አጥንት የለውምና እኔን ዳስሳችሁ እዩ።” እነርሱ ግን አሁንም ለማመን አመነቱ።

በእርግጥ ኢየሱስ መሆኑን እንዲያስተውሉ ለመርዳት ሲል “በዚህ አንዳች የሚበላ አላችሁን?” ሲል ጠየቃቸው። የተጠበሰ ዓሣ ቁራጭ ተቀብሎ ከበላ በኋላ እንዲህ አላቸው:- “ከእናንተ ጋር ሳለሁ [ከመሞቴ በፊት] በሙሴ ሕግና በነቢያት በመዝሙራትም ስለ እኔ የተጻፈው ሁሉ ይፈጸም ዘንድ ይገባል ብዬ የነገርኋችሁ ቃሌ ይህ ነው።”

ኢየሱስ በመቀጠል ከእነርሱ ጋር የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት እንዳደረገ በሚቆጠር ሁኔታ እንዲህ ሲል አስተማራቸው:- “ክርስቶስ መከራ ይቀበላል በሦስተኛውም ቀን ከሙታን ይነሣል፣ በስሙም ንስሐና የኃጢአት ስርየት ከኢየሩሳሌም ጀምሮ በአሕዛብ ሁሉ ይሰበካል ተብሎ እንዲሁ ተጽፎአል። እናንተም ለዚህ ምስክሮች ናችሁ።”

ቶማስ በሆነ ምክንያት እሁድ ዕለት ምሽት በተደረገው በዚህ ወሳኝ ስብሰባ ላይ አልነበረም። ስለዚህ ከዚያ በኋላ በነበሩት ቀናት ሌሎቹ በደስታ ፈንድቀው “ጌታን አይተነዋል” ብለው ነገሩት።

“የችንካሩን ምልክት በእጆቹ ካላየሁ” አለ ቶማስ፤ “ጣቴንም በችንካሩ ምልክት ካላገባሁ እጄንም በጎኑ ካላገባሁ አላምንም።”

ከስምንት ቀናት በኋላ ደቀ መዛሙርቱ እንደገና ቤት ውስጥ ተሰበሰቡ። በዚህ ወቅት ቶማስም አብሯቸው ነበረ። በሮቹ የተዘጉ ቢሆንም እንኳ አሁንም ኢየሱስ በመካከላቸው ቆመና “ሰላም ለእናንተ ይሁን” አላቸው። ከዚያም ወደ ቶማስ ዞረና “ጣትህን ወደዚህ አምጣና እጆቼን እይ፤ እጅህንም አምጣና በጎኔ አግባው፤ . . . ያላመንህ አትሁን” አለው።

ቶማስ “ጌታዬ አምላኬም” በማለት በመደነቅ ተናገረ።

ኢየሱስም “ስለ አየኸኝ አምነሃል፤ ሳያዩ የሚያምኑ ብፁዓን [“ደስተኞች፣” NW] ናቸው” አለው። ሉቃስ 24:​11, 13-48፤ ዮሐንስ 20:​19-29

▪ ሁለት ደቀ መዛሙርት ወደ ኤማሁስ እየተጓዙ ሳለ አንድ እንግዳ የሆነ ሰው ምን ጥያቄዎች አቀረበላቸው?

▪ ደቀ መዛሙርቱ ልባቸው በውስጣቸው እንዲቃጠልባቸው ያደረገው እንግዳው ሰው የተናገረው ነገር ምንድን ነው?

▪ ደቀ መዛሙርቱ እንግዳው ሰው ማን መሆኑን ለይተው ያወቁት እንዴት ነው?

▪ ቀለዮጳና ጓደኛው ወደ ኢየሩሳሌም ሲመለሱ ምን አስደሳች ሪፖርት ሰሙ?

▪ ኢየሱስ ለአምስተኛ ጊዜ ለደቀ መዛሙርቱ የተገለጠው እንዴት ነው? በዚያ ወቅትስ ምን ነገር ተከናወነ?

▪ ኢየሱስ ለአምስተኛ ጊዜ ከተገለጠ ከስምንት ቀናት በኋላ ምን ነገር ተፈጸመ? ቶማስ በመጨረሻ ኢየሱስ ሕያው መሆኑን ያመነው እንዴት ነው?