በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ኢየሱስ የአንዲትን መበለት ሐዘን አስወገደ

ኢየሱስ የአንዲትን መበለት ሐዘን አስወገደ

ምዕራፍ 37

ኢየሱስ የአንዲትን መበለት ሐዘን አስወገደ

ኢየሱስ የሠራዊቱን አለቃ አገልጋይ ከፈወሰ በኋላ ብዙም ሳይቆይ ከቅፍርናሆም በደቡብ ምዕራብ ከ30 ኪሎ ሜትር በላይ በሚሆን ርቀት ላይ ወደምትገኘው ወደ ናይን ከተማ ሄደ። ደቀ መዛሙርቱና ሌሎች ብዙ ሰዎች አብረውት ነበሩ። ወደ ናይን ከተማ ዳርቻ የደረሱት አመሻሹ ላይ ሳይሆን አይቀርም። እዚያ ሲደርሱ የቀብር ሥነ ሥርዓት ለመፈጸም የሚጓዙ ሰዎችን አገኙ። የአንድን ወጣት አስከሬን ለመቅበር ተሸክመውት ከከተማው ውጪ እየወሰዱት ነበር።

እናትየዋ ባሏ የሞተባት ሴት ስለነበረችና የሞተውም ልጅ አንድ ልጅዋ ስለነበረ የእሷ ሁኔታ በጣም ያሳዝን ነበር። ባልዋ ሲሞት ልጅዋ ስለነበረ በልጅዋ ልትጽናና ትችላለች። ተስፋዋ፣ ፍላጎትዋና ምኞትዋ ከእሱ የወደፊት ሁኔታ ጋር የተሳሰረ ነበር። አሁን ግን የምትጽናናበት ምንም ሰው የላትም። የከተማይቱ ሰዎች አብረዋት ወደ ቀብሩ ስፍራ ሲሄዱ በጣም ታለቅስ ነበር።

ኢየሱስ ሴትዮዋን ሲያያት በደረሰባት ጥልቅ ሐዘን ልቡ ተነካ። ስለዚህ ርኅራኄ በተሞላበትና እምነት በሚያሳድር ጠንካራ መንፈስ “አታልቅሽ” አላት። የኢየሱስ ሁኔታና ድርጊቱ የሕዝቡን ትኩረት ሳበው። ስለዚህ ቀረብ ብሎ አስከሬኑን የተሸከሙበትን ቃሬዛ ሲነካ የተሸከሙት ሰዎች ቆሙ። ሁሉም ምን እንደሚያደርግ ለማየት እንደጓጉ ጥርጥር የለውም።

እርግጥ ነው፣ ከኢየሱስ ጋር ያሉት ሰዎች ብዙ የታመሙ ሰዎችን ተአምራዊ በሆነ መንገድ ሲፈውስ ተመልክተዋል። ሆኖም የሞተን ሰው ሲያስነሳ አይተው የሚያውቁ አይመስልም። እንዲህ ያለ ነገር ሊፈጽም ይችላልን? ኢየሱስ አስከሬኑን “አንተ ጎበዝ፣ እልሃለሁ፣ ተነሣ” አለው። ሰውየውም ቀና ብሎ ተቀመጠ! መናገር ጀመረ፤ ኢየሱስም ለእናቱ ሰጣት።

ሰዎቹ ወጣቱ በእርግጥ ሕያው መሆኑን ሲመለከቱ “ታላቅ ነቢይ በእኛ መካከል ተነሥቶአል” አሉ። ሌሎቹ ደግሞ “እግዚአብሔር ሕዝቡን ጎበኘ” ሲሉ ተናገሩ። ወዲያውኑ ስለዚህ ተአምራዊ ድርጊት የሚገልጸው ወሬ በይሁዳ ሁሉና በዙሪያዋ ባለው አገር ሁሉ ተዳረሰ።

አጥማቂው ዮሐንስ አሁንም እንደታሰረ ነው፤ ኢየሱስ ሊፈጽማቸው ስለቻላቸው ሥራዎች ይበልጥ ማወቅ ፈልጓል። የዮሐንስ ደቀ መዛሙርት ስለነዚህ ተአምራት ነገሩት። ያሳየው ምላሽ ምን ነበር? ሉቃስ 7:​11-18

▪ ኢየሱስ ወደ ናይን ከተማ ሲቃረብ ምን ተመለከተ?

▪ ኢየሱስ ባየው ነገር የተነካው እንዴት ነው? ያደረገውስ ምን ነበር?

▪ ሰዎቹ ኢየሱስ ለፈጸመው ተአምር ያሳዩት ምላሽ ምን ነበር?