በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ኢየሱስ ፈሪሳውያንን ነቀፈ

ኢየሱስ ፈሪሳውያንን ነቀፈ

ምዕራፍ 42

ኢየሱስ ፈሪሳውያንን ነቀፈ

ኢየሱስ እኔ አጋንንትን የማስወጣው በሰይጣን ኃይል ከሆነ ሰይጣን ከራሱ ጋር ተከፋፍሏል ማለት ነው የሚል መከራከሪያ ነጥብ አቅርቧል። ከዚያም በመቀጠል “ዛፍ ከፍሬዋ ትታወቃለችና ዛፍዋን መልካም፣ ፍሬዋንም መልካም አድርጉ፣ ወይም ዛፍዋን ክፉ ፍሬዋንም ክፉ አድርጉ” ብሏል።

ኢየሱስ አጋንንትን በማስወጣት መልካም ፍሬ ማፍራት የቻለው ሰይጣንን የሚያገለግል በመሆኑ ነው ብሎ መወንጀል ሞኝነት ነው። ፍሬው መልካም ከሆነ ዛፉ መጥፎ ሊሆን አይችልም። በሌላ በኩል ደግሞ ፈሪሳውያን በኢየሱስ ላይ ትክክል ያልሆነ ክስ በማንሳትና መሠረተ ቢስ ተቃውሞ በመሰንዘር ያፈሩት መጥፎ ፍሬ እነርሱ ራሳቸው መጥፎዎች እንደሆኑ የሚያሳይ ማስረጃ ነው። ኢየሱስ እንዲህ አላቸው:- “እናንተ የእፉኝት ልጆች፣ ክፉዎች ስትሆኑ መልካም ለመናገር እንዴት ትችላላችሁ? በልብ ሞልቶ ከተረፈው አፍ ይናገራልና።”

የምንናገራቸው ቃላት የልባችንን ሁኔታ የሚያንጸባርቁ በመሆናቸው የምንናገረው ነገር ፍርድ ለመስጠት ጥሩ መሠረት ይሆናል። ኢየሱስ እንዲህ አለ:- “እኔ እላችኋለሁና፣ ሰዎች ስለሚናገሩት ስለ ከንቱ ነገር ሁሉ በፍርድ ቀን መልስ ይሰጡበታል፤ ከቃልህ የተነሣ ትጸድቃለህና ከቃልህም የተነሣ ትኰነናለህ።”

ኢየሱስ ብዙ ተአምራዊ ሥራዎች ያከናወነ ቢሆንም ጻፎችና ፈሪሳውያን “መምህር ሆይ፣ ከአንተ ምልክት እንድናይ እንወዳለን” ብለው ጠየቁት። ከኢየሩሳሌም የመጡት እነዚህ ሰዎች ተአምራቱን ራሳቸው ያላዩ ቢሆንም እንኳ እነዚህን ተአምራት በተመለከተ ፈጽሞ ሊካድ የማይችል የዓይን ምሥክሮች ማስረጃ አለ። ስለዚህ ኢየሱስ የአይሁድ መሪዎቹን እንዲህ አላቸው:- “ክፉና አመንዝራ ትውልድ ምልክት ይሻል፣ ከነቢዩም ከዮናስ ምልክት በቀር ምልክት አይሰጠውም።”

ኢየሱስ በመቀጠል ምን ማለቱ እንደሆነ ሲያብራራ እንዲህ አለ:- “ዮናስ በዓሣ አንባሪ ሆድ ሦስት ቀንና ሦስት ሌሊት እንደ ነበረ፣ እንዲሁ የሰው ልጅ በምድር ልብ ሦስት ቀንና ሦስት ሌሊት ይኖራል።” ዮናስ በዓሣው ከተዋጠ በኋላ ከሞት የተነሣ ያህል ሆኖ ከዓሣው ሆድ ወጥቷል። ስለዚህ ኢየሱስ እንደሚሞትና በሦስተኛው ቀን ሕያው ሆኖ እንደሚነሣ አስቀድሞ መናገሩ ነበር። ሆኖም የአይሁድ መሪዎች ከጊዜ በኋላ ኢየሱስ ከሞት ከተነሣ በኋላም እንኳ ‘የዮናስን ምልክት’ ለመቀበል ፈቃደኞች አልሆኑም።

ስለዚህ ኢየሱስ በዮናስ ስብከት ንስሐ የገቡት የነነዌ ሰዎች በፍርድ ቀን ተነሥተው ኢየሱስን አንቀበልም ባሉት አይሁዶች ላይ እንደሚፈርዱ ገልጿል። በተመሳሳይም የሰሎሞንን ጥበብ ለመስማት ከምድር ዳርቻ የመጣችውንና ባየችውና በሰማችው ነገር የተደነቀችውን የሳባ ንግሥት በመጥቀስ ሁኔታውን አነጻጽሯል። ከዚያም ኢየሱስ “እነሆም፣ ከሰሎሞን የሚበልጥ ከዚህ አለ” ሲል ተናግሯል።

ከዚያም ኢየሱስ ርኩስ መንፈስ ስለወጣለት ሰው የሚገልጽ ምሳሌ ተናገረ። ይሁን እንጂ ሰውየው ባዶውን ቦታ በመልካም ነገሮች ስላልሞላው ሌሎች ተጨማሪ ሰባት ክፉ መናፍስት ይሰፍሩበታል። ኢየሱስ “ለዚህ ክፉ ትውልድ ደግሞ እንዲሁ ይሆንበታል” አለ። ርኩሱ መንፈስ ለጊዜው እንደሄደ ሁሉ የእስራኤል ሕዝብም ለተወሰነ ጊዜ ነጽቶና አንዳንድ ማሻሻያዎች አድርጎ ነበር። ሆኖም ሕዝቡ በየጊዜው የተነሱትን የአምላክ ነቢያት አለመቀበሉና በመጨረሻም ክርስቶስን መቃወሙ ከመጀመሪያው የከፋ መጥፎ ሁኔታ ላይ እንደደረሰ የሚያሳይ ነው።

ኢየሱስ እየተናገረ ሳለ እናቱና ወንድሞቹ መጥተው በተሰበሰበው ሕዝብ ዳር ቆሙ። ስለዚህ አንድ ሰው “እነሆ፣ እናትህና ወንድሞችህ ሊነጋገሩህ ፈልገው በውጭ ቆመዋል” አለው።

ኢየሱስ “እናቴ ማን ናት? ወንድሞቼስ እነ ማን ናቸው?” ሲል ጠየቀ። እጁን ወደ ደቀ መዛሙርቱ ዘርግቶ “እነሆ እናቴና ወንድሞቼ፤ በሰማያት ያለውን የአባቴን ፈቃድ የሚያደርግ ሁሉ፣ እርሱ ወንድሜ እኅቴም እናቴም ነውና” አለ። በዚህ መንገድ ኢየሱስ ከዘመዶቹ ጋር የሚያስተሳስረው ዝምድና ምንም ያህል ውድ ቢሆንም እንኳ ከዚያ ይበልጥ ውድ የሆነው ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ያለው ዝምድና እንደሆነ አሳይቷል። ማቴዎስ 12:​33-50፤ ማርቆስ 3:​31-35፤ ሉቃስ 8:​19-21

▪ ፈሪሳውያን ‘ዛፉንም’ ሆነ ‘ፍሬውን’ መልካም ማድረግ ሳይችሉ የቀሩት እንዴት ነው?

▪ ‘የዮናስ ምልክት’ ምንድን ነው? ከጊዜ በኋላም ሳይቀበሉት የቀሩት እንዴት ነው?

▪ በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበረው የእስራኤል ሕዝብ ርኩስ መንፈስ ከወጣለት ሰው ሁኔታ ጋር የሚመሳሰለው እንዴት ነው?

▪ ኢየሱስ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ያለውን የተቀራረበ ዝምድና ጠበቅ አድርጎ የገለጸው እንዴት ነው?