በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

“እነሆ ሰውዬው!”

“እነሆ ሰውዬው!”

ምዕራፍ 123

“እነሆ ሰውዬው!”

ጲላጦስ፣ ኢየሱስ ያሳየው ጠባይ ስለማረከውና ንጹሕ መሆኑን ስለተገነዘበ እሱን ለመፍታት ሌላ መንገድ መፈለግ ጀመረ። ሕዝቡን “በፋሲካ [“በማለፍ በዓል፣” NW] አንድ ልፈታላችሁ ልማድ አላችሁ” አላቸው።

በርባን የሚባል አንድ የታወቀ ነፍሰ ገዳይም ታስሮ ነበር፤ ስለዚህ ጲላጦስ “በርባንን ወይስ ክርስቶስ የተባለውን ኢየሱስን ማንኛውን ልፈታላችሁ ትወዳላችሁ?” ሲል ጠየቃቸው።

ሕዝቡ ከሥር ሆነው የሚቆሰቁሷቸው የካህናት አለቆች ስላግባቧቸው በርባን እንዲፈታና ኢየሱስ እንዲገደል ጠየቁ። ጲላጦስ አሁንም ተስፋ ባለመቁረጥ “ከሁለቱ ማንኛውን ልፈታላችሁ ትወዳላችሁ?” ሲል በድጋሚ ጠየቃቸው።

“በርባንን” ብለው ጮኹ።

ጲላጦስ በጣም በመጨነቅ “ክርስቶስ የተባለውን ኢየሱስን እንግዲህ ምን ላድርገው?” ብሎ ጠየቃቸው።

ጆሮ በሚያደነቁር ድምፅ “ይሰቀል” “ስቀለው ስቀለው” እያሉ ጮኹ።

ጲላጦስ አንድ ንጹሕ ሰው እንዲገደል እየጠየቁ መሆኑን ስለተረዳ የሚከተለውን የተቃውሞ ሐሳብ አቀረበ:- “ምን ነው? ያደረገውስ ክፋት ምንድር ነው? ለሞት የሚያደርሰው በደል አላገኘሁበትም፤ ስለዚህ ቀጥቼ እፈታዋለሁ።”

ጲላጦስ የተለያዩ ሙከራዎች ቢያደርግም ክፉኛ የተቆጣው ሕዝብ በሃይማኖት መሪዎቹ ግፊት “ይሰቀል” እያለ መጮኹን ቀጠለ። በካህናቱ ቆስቋሽነት ያበደው ሕዝብ ደም ተጠምቶ ነበር። ከሕዝቡ መካከል አንዳንዶቹ ከአምስት ቀናት በፊት ኢየሱስ ንጉሥ ሆኖ ወደ ኢየሩሳሌም ሲገባ ጥሩ አቀባበል አድርገውለት የነበሩት ሰዎች ሳይሆኑ አይቀሩም! በዚህ መካከል የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት በቦታው ከነበሩ ድምፃቸውን አጥፍተው ተደብቀዋል።

ጲላጦስ ሕዝቡን ለማግባባት ያደረገው ጥረት እንዳልተሳካና ሁከት እየተቀሰቀሰ መሆኑን ሲረዳ ውኃ አመጣና እጆቹን በሕዝቡ ፊት ታጥቦ “እኔ ከዚህ ጻድቅ ሰው ደም ንጹሕ ነኝ፤ እናንተ ተጠንቀቁ” አላቸው። በዚህ ጊዜ ሕዝቡ መልሰው “ደሙ በእኛና በልጆቻችን ላይ ይሁን” አሉ።

ስለዚህ ጲላጦስ ካቀረቡት ጥያቄ ጋር በመስማማትና ትክክል እንደሆነ የሚያውቀውን ነገር ከማድረግ ይልቅ የሕዝቡን ፍላጎት ለማሟላት በመፈለግ በርባንን ፈታላቸው። ኢየሱስን ወሰደውና ልብሱን አስወልቆ አስገረፈው። ይህ ተራ ግርፋት አይደለም። ዘ ጆርናል ኦቭ ዚ አሜሪካን ሜዲካል አሶሲየሽን ሮማውያን ለመግረፍ ይጠቀሙበት የነበረውን ልማድ እንዲህ ሲል ገልጾታል:-

“ለመግረፍ ይጠቀሙበት የነበረው የተለመደው መሣሪያ የተለያየ ርዝመት ያላቸው ነጠላ የሆኑ ወይም ደግሞ የተገመዱ የቆዳ ጠፍሮች ያሉትና በጠፍሮቹ ላይ አለፍ አለፍ ብለው የተሰኩ ትንንሽ የብረት እንክብሎች ወይም ስለት ያላቸው የበግ አጥንት ቁርጥራጮች ያሉት አጠር ያለ ጅራፍ (ፍላግረም ወይም ፍላጀለም) ነው። . . . ሮማውያን ወታደሮቹ የሰውዬውን ጀርባ ባለ በሌለ ኃይላቸው ደጋግመው ሲገርፉት የብረት እንክብሎቹ ትልልቅ ሰንበር ያወጣሉ። የቆዳ ጠፍሮቹና የበግ አጥንት ቁርጥራጮቹ ደግሞ ቆዳውንና ከቆዳው ሥር ያሉትን ሕብረ ሕዋሳት ይቆራርጧቸዋል። ከዚያም ግርፋቱ ሲቀጥል የቆዳው ስንጥቅ እየጠለቀ ይሄድና ከሥር ያሉት ጡንቻዎች ድረስ ይደርሳል፤ ይህም ሥጋው እንዲተለተልና ደም ቋጥሮ እንዲነዝረው ያደርገዋል።”

ኢየሱስ በዚህ መንገድ በጣም በሚያሠቃይ ሁኔታ ከተገረፈ በኋላ ወደ ገዥው ቤተ መንግሥት ተወሰደና ወታደሮቹ በሙሉ እንዲሰበሰቡ ተደረገ። እዚያም ወታደሮቹ የእሾህ አክሊል ራሱ ላይ በማጥለቅና ወደ ታች በመጫን ሌላ አረመኔያዊ ድርጊት ፈጸሙበት። በቀኝ እጁ መቃ አስያዙት፤ ንጉሣውያን ቤተሰቦች የሚለብሱትን ዓይነት ሐምራዊ ልብስ አለበሱት። ከዚያም “የአይሁድ ንጉሥ ሆይ፣ ሰላም ለአንተ ይሁን” እያሉ ዘበቱበት። ምራቃቸውን ተፉበት፤ በጥፊም መቱት። ጠንካራውን መቃ ከእጁ ወስደው ጭንቅላቱን ሲመቱት ራሱ ላይ ባጠለቀው የሚያዋርድ “አክሊል” ላይ ያሉት ሹል እሾኾች ይበልጥ ጭንቅላቱ ውስጥ ተሰኩ።

ኢየሱስ ይህን ሁሉ ቁም ስቅል ተቋቁሞ ያሳየው አስደናቂ ግርማ ሞገስና ጥንካሬ ጲላጦስን በጣም ስላስደነቀው ኢየሱስን ለማስለቀቅ ሌላ ሙከራ ለማድረግ ተገፋፋ። ሕዝቡን “እነሆ፣ አንዲት በደል ስንኳ እንዳላገኘሁበት ታውቁ ዘንድ እርሱን ወደ ውጭ አወጣላችኋለሁ” አላቸው። ምናልባትም በኢየሱስ ላይ የደረሰውን ሥቃይ ሲመለከቱ ልባቸው ይራራ ይሆናል ብሎ አስቦ ይሆናል። ኢየሱስ የእሾኹን አክሊል አጥልቆና ከላይ የሚደረበውን ሐምራዊ ልብስ አድርጎ እየደማ ያለው ፊቱ እየጠዘጠዘው በዚያ ጨካኝ ሕዝብ ፊት ሲቆም ጲላጦስ “እነሆ ሰውዬው!” ሲል ተናገረ።

ምንም እንኳ የተደበደበና የቆሳሰለ ቢሆንም በታሪክ ዘመናት ሁሉ ተወዳዳሪ ያልተገኘለት ታላቅ ሰው ፊታቸው ቆሟል፤ በእርግጥም እስከ ዛሬ ከኖሩት ሁሉ የሚበልጥ ታላቅ ሰው! አዎን፣ ኢየሱስ፣ ጲላጦስ እንኳን ሳይቀር አምኖ የተቀበለውን ታላቅነቱን የሚመሰክር ግርማና እርጋታ አሳይቷል፤ ምክንያቱም ጲላጦስ የተናገራቸው ቃላት አክብሮትና ሐዘን የተቀላቀለባቸው ይመስላሉ። ዮሐንስ 18:​39 እስከ 19:​5፤ ማቴዎስ 27:​15-17, 20-30፤ ማርቆስ 15:​6-19፤ ሉቃስ 23:​18-25

▪ ጲላጦስ ኢየሱስን ለማስለቀቅ የሞከረው በምን መንገድ ነው?

▪ ጲላጦስ ራሱን ከኃላፊነት ነፃ ለማድረግ የሞከረው እንዴት ነው?

▪ መገረፍ ሲባል ምን ነገሮችን ይጨምራል?

▪ ኢየሱስን ከገረፉት በኋላ የዘበቱበት እንዴት ነው?

▪ ጲላጦስ ኢየሱስን ለማስለቀቅ ምን ተጨማሪ ሙከራ አድርጓል?