በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

እንደገና በሰባተኛው ቀን አስተማረ

እንደገና በሰባተኛው ቀን አስተማረ

ምዕራፍ 68

እንደገና በሰባተኛው ቀን አስተማረ

ጊዜው የዳስ በዓል የመጨረሻ ቀን ማለትም ሰባተኛው ቀን ነው። ኢየሱስ በቤተ መቅደሱ ውስጥ በሚገኘው “ግምጃ ቤት” ተብሎ በሚጠራው ቦታ እያስተማረ ነው። ይህ ቦታ የሚገኘው ሰዎች የመዋጮ ገንዘብ የሚያስቀምጡባቸው ዕቃዎች ባሉበት የሴቶች አደባባይ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ሳይሆን አይቀርም።

በዓሉ በሚከበርበት በእያንዳንዱ ቀን ማታ ማታ በቤተ መቅደሱ ውስጥ በሚገኘው በዚህ አካባቢ ቦግ ያለ ብርሃን በርቶ ይታያል። እያንዳንዳቸው በዘይት የተሞሉ አራት ትላልቅ ጎድጓዳ ሳህኖች ያሏቸው አራት ግዙፍ መቅረዞች በዚህ ሥፍራ ቆመዋል። በ16ቱ ጎድጓዳ ሳህኖች ውስጥ ያለው ዘይት ሲነድ መቅረዞቹ የሚያወጡት ብርሃን ማታ ማታ በርቀት ለሚገኘው አካባቢ ሁሉ ብርሃን ይሰጣል። አሁን ኢየሱስ የተናገረው ነገር አድማጮቹ ይህን እንዲያስታውሱ ሊያደርጋቸው ይችላል። ኢየሱስ “እኔ የዓለም ብርሃን ነኝ” ሲል ገለጸ። “የሚከተለኝ የሕይወት ብርሃን ይሆንለታል እንጂ በጨለማ አይመላለስም።”

ፈሪሳውያን “አንተ ስለ ራስህ ትመሰክራለህ፤ ምስክርነትህ እውነት አይደለም” ሲሉ ተቃወሙት።

ኢየሱስ እንዲህ ሲል መለሰላቸው:- “እኔ ስለ ራሴ ምንም እንኳ ብመሰክር ከወዴት እንደ መጣሁ ወዴትም እንድሄድ አውቃለሁና ምስክርነቴ እውነት ነው፤ እናንተ ግን ከወዴት እንደ መጣሁ ወዴትም እንድሄድ አታውቁም።” አክሎም “ስለ ራሴ የምመሰክር እኔ ነኝ፣ የላከኝም አብ ስለ እኔ ይመሰክራል” አላቸው።

ፈሪሳውያን “አባትህ ወዴት ነው?” ብለው ጠየቁት።

ኢየሱስ “እኔንም ወይም አባቴንም አታውቁም” ሲል መለሰላቸው። “እኔንስ ብታውቁኝ አባቴን ደግሞ ባወቃችሁ ነበር።” ምንም እንኳ ፈሪሳውያን አሁንም ኢየሱስ እንዲያዝ ይፈልጉ የነበረ ቢሆንም አንድም የነካው አልነበረም።

ኢየሱስ በድጋሚ “እኔ እሄዳለሁ” ሲል ተናገረ። “እኔ ወደምሄድበት እናንተ ልትመጡ አትችሉም።”

በዚህ ጊዜ አይሁዶቹ ግራ ተጋቡና “እኔ ወደምሄድበት እናንተ ልትመጡ አትችሉም ማለቱ ራሱን ይገድላልን? እንጃ” አሉ።

“እናንተ ከታች ናችሁ” ሲል ኢየሱስ ገለጸ። “እኔ ከላይ ነኝ፤ እናንተ ከዚህ ዓለም ናችሁ፣ እኔ ከዚህ ዓለም አይደለሁም።” ከዚያም አክሎ “እኔ እንደ ሆንሁ ባታምኑ በኃጢአታችሁ ትሞታላችሁ” አላቸው።

ኢየሱስ ሰው ከመሆኑ በፊት ስለነበረው ሕይወትና ተስፋ የተሰጠበት መሲሕ ወይም ክርስቶስ መሆኑን ማመልከቱ ነበር። ሆኖም በከፍተኛ ንቀት “አንተ ማን ነህ?” ብለው ጠየቁት።

ኢየሱስ ሊቀበሉት ያልፈለጉ ቢሆንም እንኳ “ከመጀመሪያ ለእናንተ የተናገርሁት ነኝ” ሲል መለሰላቸው። ሆኖም ቀጥሎ እንዲህ አለ:- “የላከኝ እውነተኛ ነው እኔም ከእርሱ የሰማሁትን ይህን ለዓለም እናገራለሁ።” ኢየሱስ በመቀጠል እንዲህ አላቸው:- “የሰውን ልጅ ከፍ ከፍ ባደረጋችሁት ጊዜ እኔ እሆን ዘንድ አባቴም እንዳስተማረኝ እነዚህን እናገር ዘንድ እንጂ ከራሴ አንዳች እንዳላደርግ በዚያን ጊዜ ታውቃላችሁ። የላከኝም ከእኔ ጋር ነው፤ እኔ ደስ የሚያሰኘውን ዘወትር አደርጋለሁና አብ ብቻዬን አይተወኝም።”

ኢየሱስ እንዲህ ብሎ ሲናገር ብዙ ሰዎች አመኑበት። በእርሱ ያመኑትን ሰዎች እንዲህ አላቸው:- “እናንተ በቃሌ ብትኖሩ በእውነት ደቀ መዛሙርቴ ናችሁ፤ እውነትንም ታውቃላችሁ እውነትም አርነት ያወጣችኋል።”

ተቃዋሚዎቹ ወዲያውኑ ቀበል አደረጉና “የአብርሃም ዘር ነን ለአንድም ስንኳ ከቶ ባሪያዎች አልሆንም፤ አንተ:- አርነት ትወጣላችሁ እንዴት ትላለህ?” አሉት።

ምንም እንኳ አይሁዶች ብዙ ጊዜ በውጪ ኃይሎች የተገዙ ቢሆንም ማንኛውንም ጨቋኝ እንደ ጌታ አድርገው አይቀበሉም ነበር። ባሪያዎች ተብለው መጠራት አይፈልጉም ነበር። ሆኖም ኢየሱስ በእርግጥ ባሪያዎች መሆናቸውን አመለከተ። ባሪያዎች የሆኑት በምን መንገድ ነው? ኢየሱስ “እውነት እውነት እላችኋለሁ፣ ኃጢአት የሚያደርግ ሁሉ የኃጢአት ባርያ ነው” አላቸው።

አይሁዶች የኃጢአት ባሪያዎች መሆናቸውን አምነው ለመቀበል አለመፈለጋቸው አደገኛ ሁኔታ ያስከትልባቸዋል። “ባርያም ለዘላለም በቤት አይኖርም” ሲል ኢየሱስ ገለጸ። “ልጁ ለዘላለም ይኖራል።” አንድ ባሪያ ምንም ዓይነት የወራሽነት መብት ስለሌለው በማንኛውም ጊዜ የመባረር አደጋ ሊደርስበት ይችላል። በቤተሰቡ ውስጥ “ለዘላለም” ማለትም በሕይወት እስካለ ድረስ የሚቆየው ከቤተሰቡ የተወለደው ወይም በማደጎነት የተወሰደው ልጅ ብቻ ነው።

ኢየሱስ በመቀጠል “እንግዲህ ልጁ አርነት ቢያወጣችሁ በእውነት አርነት ትወጣላችሁ” አለ። ስለዚህ ሰዎችን ነፃ የሚያወጣው እውነት ልጁን ማለትም ኢየሱስ ክርስቶስን የሚመለከት እውነት ነው። ማንኛውም ሰው ሞት ከሚያስከትለው ኃጢአት ነፃ መውጣት የሚችለው ፍጹም በሆነው የኢየሱስ ሰብዓዊ ሕይወት መሥዋዕት አማካኝነት ብቻ ነው። ዮሐንስ 8:​12-36

▪ ኢየሱስ በሰባተኛው ቀን ያስተማረው የት ነው? በዚያ ቦታ ማታ ምን ነገር ይታያል? ይህስ ከኢየሱስ ትምህርት ጋር የተያያዘው እንዴት ነው?

▪ ኢየሱስ ከየት እንደመጣ ሲናገር ምን አለ? ይህስ ስለ ማንነቱ ምን ይገልጻል?

▪ አይሁዶች ባሪያዎች የሆኑት በምን መንገድ ነው? ሆኖም ነፃ የሚያወጣቸው እውነት የትኛው ነው?