በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

እንደገና ወደ ቤተ መቅደሱ ሄደ

እንደገና ወደ ቤተ መቅደሱ ሄደ

ምዕራፍ 103

እንደገና ወደ ቤተ መቅደሱ ሄደ

ኢየሱስና ደቀ መዛሙርቱ ከኢያሪኮ ከመጡ ወዲህ ለሦስተኛ ቀን በቢታንያ አደሩ። አሁን ኒሳን 10 ሰኞ ዕለት ማለዳ ወደ ኢየሩሳሌም መጓዝ ጀምረዋል። ኢየሱስ ራበው። ስለዚህ ቅጠል ያወጣች አንዲት የበለስ ዛፍ ሲመለከት ጥቂት የበለስ ፍሬዎች አፍርታ እንደሆነ ለማየት ወደ ዛፏ ሄደ።

በለሶች የሚያቆጠቁጡት ከሰኔ በኋላ ነው፤ አሁን ደግሞ ጊዜው ገና የመጋቢት ወር መገባደጃ ነው። ስለዚህ ዛፏ ቅጠል ያወጣችው ከወቅቱ ቀደም ብላ ነበር። ይሁን እንጂ ኢየሱስ ዛፏ ቀደም ብላ ቅጠል እንዳወጣች ሁሉ ፍሬም አስቀድማ አፍርታ ይሆናል ብሎ እንዳሰበ ከሁኔታው መረዳት ይቻላል። ሆኖም እንዳሰበው አልሆነም። ቅጠሎቹ ዛፏን አሳሳች መልክ ሰጥተዋት ነበር። በዚህ ጊዜ ኢየሱስ ዛፏን “ከአሁን ጀምሮ ለዘላለም ማንም ከአንቺ ፍሬ አይብላ” ብሎ ረገማት። ኢየሱስ የወሰደው እርምጃ ያስከተለው ውጤትና ውጤቱ ያዘለው ቁም ነገር በቀጣዩ ቀን ጠዋት ግልጽ ሆኗል።

ኢየሱስና ደቀ መዛሙርቱ ጉዟቸውን በመቀጠል ከጥቂት ጊዜ በኋላ ኢየሩሳሌም ደረሱ። ከዚህ በፊት በነበረው ቀን ከሰዓት በኋላ ጎብኝቶት ወደነበረው ቤተ መቅደስ ሄደ። ሆኖም ከሦስት ዓመታት በፊት በ30 እንደ ዘመናችን አቆጣጠር በተከበረው የማለፍ በዓል ላይ እንዳደረገው ሁሉ ዛሬም እርምጃ ወሰደ። ኢየሱስ በቤተ መቅደሱ ውስጥ ይሸጡና ይገዙ የነበሩትን ሰዎች አስወጣ። የገንዘብ ለዋጮቹን ጠረጴዛዎችና የርግብ ሻጮቹን ወንበሮች ገለበጠ። አልፎ ተርፎም አንድም ሰው ዕቃ ተሸክሞ በቤተ መቅደሱ ውስጥ እንዳያልፍ ከለከለ።

በቤተ መቅደሱ ውስጥ ገንዘብ የሚለውጡትንና እንስሳት የሚሸጡትን ሰዎች በማውገዝ እንዲህ አላቸው:- “‘ቤቴ ለሕዝብ ሁሉ የጸሎት ቤት ይባላል’ ተብሎ አልተጻፈምን? እናንተ ግን የሌቦች ዋሻ አደረጋችሁት።” (የ1980 ትርጉም) ለመሥዋዕት የሚሆኑ እንስሶችን ከእነሱ ከመግዛት ሌላ ምንም አማራጭ የሌላቸውን ሰዎች በጣም ውድ የሆነ ዋጋ ያስከፍሏቸው ስለነበረ ሌቦች ነበሩ። ኢየሱስ እንዲህ ዓይነቱን ንግድ እንደ ዘረፋ ወይም ሌብነት አድርጎ ተመልክቶታል።

የካህናት አለቆቹ፣ ጻፎቹና የሕዝቡ መሪዎች ኢየሱስ ያደረገውን ሲሰሙ እንደገና እሱን የሚያስገድሉበትን መንገድ መፈለግ ጀመሩ። በዚህም መንገድ ሊስተካከሉ የማይችሉ መሆናቸውን አሳይተዋል። ሆኖም ሕዝቡ ኢየሱስን ለመስማት ክብብ አድርገው ይከተሉት ስለነበር እንዴት ሊገድሉት እንደሚችሉ ግራ ገብቷቸው ነበር።

ከሥጋዊ አይሁዳውያን በተጨማሪ አሕዛብም በማለፍ በዓሉ ላይ ለመገኘት መጥተው ነበር። እነዚህ አሕዛብ ወደ አይሁድ ሃይማኖት የተለወጡ ሰዎች ነበሩ። የተወሰኑ ግሪካውያን ወደ ፊልጶስ ቀረቡና ኢየሱስን ሊያነጋግሩ እንደሚፈልጉ ነገሩት፤ እነዚህ ግሪካውያን ወደ አይሁድ እምነት የተለወጡ እንደሆኑ ከሁኔታው መረዳት ይቻላል። ፊልጶስ ወደ እንድርያስ ሄደ፤ ምናልባትም ወደ እሱ የሄደው ሰዎቹ ከኢየሱስ ጋር እንዲነጋገሩ ማድረጉ ተገቢ እንደሆነና እንዳልሆነ ለመጠየቅ ይሆናል። ኢየሱስ በዚህም ወቅት የነበረው ግሪኮቹ ሊያነጋግሩት በሚችሉበት ቦታ ማለትም በቤተ መቅደሱ ውስጥ ሳይሆን አይቀርም።

ኢየሱስ ከጥቂት ቀናት በኋላ እንደሚሞት ያውቅ ስለነበረ ያለበትን ሁኔታ እንዲህ ሲል ግሩም አድርጎ ገልጾታል:- “የሰው ልጅ ይከብር ዘንድ ሰዓቱ ደርሶአል። እውነት እውነት እላችኋለሁ፣ የስንዴ ቅንጣት በምድር ወድቃ ካልሞተች ብቻዋን ትቀራለች፤ ብትሞት ግን ብዙ ፍሬ ታፈራለች።”

አንዲት የስንዴ ዘር ምንም ያህል ዋጋ የላትም። ሆኖም ብትዘራና ዘር መሆኗ አክትሞ ‘ብትሞትስ’? ትበቅልና ከጊዜ በኋላ በጣም ብዙ የስንዴ ዘሮች የምታፈራ አገዳ ትሆናለች። በተመሳሳይም ኢየሱስ አንድ ፍጹም ሰው ነው። ሆኖም ለአምላክ የታመነ ሆኖ ከሞተ ልክ እንደ እሱ የራስን ጥቅም የመሠዋት መንፈስ ያላቸው የታመኑ ሰዎች የዘላለም ሕይወት የሚያገኙበትን መንገድ ይከፍታል። በመሆኑም ኢየሱስ “ነፍሱን የሚወድ ያጠፋታል፣ ነፍሱንም በዚህ ዓለም የሚጠላ ለዘላለም ሕይወት ይጠብቃታል” ሲል ተናግሯል።

ኢየሱስ እያሰበ ያለው ስለ ራሱ ብቻ እንዳልሆነ ግልጽ ነው፤ ምክንያቱም ቀጥሎ እንዲህ ሲል ገልጿል:- “የሚያገለግለኝ ቢኖር ይከተለኝ፣ እኔም ባለሁበት አገልጋዬ ደግሞ በዚያ ይሆናል፤ የሚያገለግለኝም ቢኖር አብ ያከብረዋል።” ኢየሱስን መከተልና እሱን ማገልገል የሚያስገኘው እንዴት ያለ ግሩም ወሮታ ነው! ይህ ወሮታ በአብ ዘንድ ክብር አግኝቶ በመንግሥቱ ከክርስቶስ ጋር ተባባሪ መሆን የሚያስችል ነው።

ኢየሱስ ከፊቱ የሚጠብቀውን ከፍተኛ ሥቃይና አሠቃቂ ሞት በማሰብ እንዲህ አለ:- “አሁን ነፍሴ ታውካለች ምንስ እላለሁ? አባት ሆይ፣ ከዚህ ሰዓት አድነኝ።” ሆኖም ይህ የሚሆነው ከፊቱ የሚጠብቀው ነገር ሊወገድ የሚችል ቢሆን ነበር። ሆኖም ሊወገድ የሚችል ነገር አልነበረም፤ ኢየሱስ ይህን ሲገልጽ “ስለዚህ ወደዚህ ሰዓት መጣሁ” ብሏል። ኢየሱስ የራሱን መሥዋዕታዊ ሞት ጨምሮ ከጠቅላላው የአምላክ ዝግጅት ጋር ተስማምቶ ነበር። ማቴዎስ 21:​12, 13, 18, 19፤ ማርቆስ 11:​12-18፤ ሉቃስ 19:​45-48፤ ዮሐንስ 12:​20-27

▪ ምንም እንኳ ወቅቱ ገና ቢሆንም ኢየሱስ የበለስ ፍሬዎች አገኛለሁ ብሎ ተስፋ አድርጎ የነበረው ለምንድን ነው?

▪ ኢየሱስ በቤተ መቅደሱ ውስጥ ሲሸጡ የነበሩትን ሰዎች “ሌቦች” ያላቸው ለምንድን ነው?

▪ ኢየሱስ ከሚሞት የስንዴ ዘር ጋር የተመሳሰለው በምን መንገድ ነው?

▪ ኢየሱስ ከፊቱ ስለሚጠብቀው ሥቃይና ሞት ምን ተሰምቶት ነበር?