በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

እንጀራውና እርሾው

እንጀራውና እርሾው

ምዕራፍ 58

እንጀራውና እርሾው

በዲካፖሊስ ብዙ ሕዝብ ወደ ኢየሱስ ጎርፎ ነበር። ብዙዎቹ ኢየሱስን ለማዳመጥና ከበሽታዎቻቸው ለመፈወስ ሲሉ በአብዛኛው አሕዛብ ወደሚኖሩበት ወደዚህ ክልል የመጡት ረጅም መንገድ አቋርጠው ነበር። አሕዛብ በሚኖሩባቸው አካባቢዎች በሚጓዙበት ጊዜ ስንቅ መያዝ የተለመደ ስለነበረ ትልልቅ ቅርጫቶችን ይዘው መጥተው ነበር።

ይሁን እንጂ ኢየሱስ በመጨረሻ ደቀ መዛሙርቱን ጠራና እንዲህ አላቸው:- “ሕዝቡ ከእኔ ጋር እስካሁን ሦስት ቀን ውለዋልና የሚበሉት ስለሌላቸው አዝንላቸዋለሁ ከእነርሱም አንዳንዶቹ ከሩቅ መጥተዋልና ጦማቸውን ወደ ቤታቸው ባሰናብታቸው በመንገድ ይዝላሉ።”

ደቀ መዛሙርቱም “በዚህ በምድረ በዳ እንጀራ ከየት አግኝቶ ሰው እነዚህን ማጥገብ ይችላል?” ብለው ጠየቁት።

ኢየሱስ “ስንት እንጀራ አላችሁ?” ሲል ጠየቃቸው።

“ሰባት፣ ጥቂትም ትንሽ ዓሣ” አሉት።

ኢየሱስ ሕዝቡ መሬት ላይ እንዲቀመጡ አዘዘና እንጀራውንና ዓሣውን ወስዶ ወደ አምላክ ጸለየ፤ ከዚያም እየቆራረሰ ለደቀ መዛሙርቱ መስጠት ጀመረ። ደቀ መዛሙርቱም ለሕዝቡ አከፋፈሉና ሕዝቡ በሙሉ እስኪጠግቡ ድረስ በሉ። ምንም እንኳ 4,000 ወንዶች እንዲሁም ሴቶችና ልጆች የተመገቡ ቢሆንም በኋላ የተረፈው ሲሰበሰብ ሰባት የስንቅ መያዣ ቅርጫት ሙሉ ሆነ!

ኢየሱስ ሕዝቡን አሰናበተና ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ጀልባ ላይ ወጥቶ ወደ ምዕራባዊው የገሊላ ባሕር ዳርቻ ተሻገረ። እዚያም ሲደርስ ፈሪሳውያን ከሰዱቃውያን የሃይማኖት ቡድን አባላት ጋር ሆነው ኢየሱስ ከሰማይ ምልክት እንዲያሳያቸው በመጠየቅ ሊፈትኑት ሞከሩ።

ኢየሱስ እሱን ለመፈተን እያደረጉት ያሉትን ጥረት በመረዳት እንዲህ ሲል መለሰላቸው:- “በመሸ ጊዜ:- ሰማዩ ቀልቶአልና ብራ ይሆናል ትላላችሁ፤ ማለዳም:- ሰማዩ ደምኖ ቀልቶአልና ዛሬ ይዘንባል ትላላችሁ። የሰማዩን ፊትማ መለየት ታውቃላችሁ፣ የዘመኑንስ ምልክት መለየት አትችሉም።”

ከዚያም ኢየሱስ ክፉና አመንዝራ ትውልድ ብሎ በመጥራት ከዚህ በፊት ለፈሪሳውያን የነገራቸውን በመድገም ከዮናስ ምልክት በቀር ሌላ ምልክት እንደማይሰጣቸው በመግለጽ አስጠነቀቃቸው። ኢየሱስና ደቀ መዛሙርቱ ከዚያ ተነስተው በጀልባ ተሳፈሩና ከገሊላ ባሕር ሰሜናዊ ምሥራቅ ወደምትገኘው ወደ ቤተ ሳይዳ አቀኑ። እየተጓዙ ሳሉ ደቀ መዛሙርቱ እንጀራ መያዝ እንደረሱና በእጃቸው ያለው እንጀራ አንድ ብቻ እንደሆነ አስተዋሉ።

ኢየሱስ ከጥቂት ጊዜ በፊት ከፈሪሳውያንና የሄሮድስ ደጋፊዎች ከሆኑት ሰዱቃውያን ጋር ያጋጠመውን ሁኔታ በአእምሮው በመያዝ “ተጠንቀቁ ከፈሪሳውያንና ከሄሮድስ እርሾ ተጠበቁ” ብሎ አጥብቆ መከራቸው። ኢየሱስ ስለ እርሾ ሲናገር ደቀ መዛመርቱ እንጀራ ሳይዙ መቅረታቸውን አስመልክቶ የተናገረ መስሏቸው ስለ ጉዳዩ መከራከር ጀመሩ። ኢየሱስ የተናገረውን በትክክል እንዳልተረዱት በማስተዋል “እንጀራ ስለሌላችሁ ስለ ምን ትነጋገራላችሁ?” አላቸው።

ኢየሱስ ከጥቂት ጊዜ በፊት በሺህ የሚቆጠሩ ሰዎችን ተአምራዊ በሆነ መንገድ መግቧል። ይህን ተአምር ከፈጸመ አንድ ወይም ሁለት ቀን ቢሆነው ነው። ቃል በቃል እንጀራ አለመያዛቸው አሳስቦት መናገሩ እንዳልሆነ ማወቅ ነበረባቸው። “ለአምስቱ ሺህ አምስቱ እንጀራ፣ ስንት መሶብ እንዳነሣችሁ ትዝ አይላችሁምን?” ሲል አስታወሳቸው።

“አሥራ ሁለት” ብለው መለሱ።

“ሰባቱን እንጀራስ ለአራት ሺህ በቆረስሁ ጊዜ ቁርስራሹ የሞላ ስንት ቅርጫት አነሣችሁ?”

“ሰባት” ብለው መለሱ።

ኢየሱስ “ገና አላስተዋላችሁምን?” ሲል ጠየቃቸው። “ከፈሪሳውያንና ከሰዱቃውያን እርሾ እንድትጠበቁ ብዬ ስለ እንጀራ እንዳልተናገርኋችሁ እንዴት አታስተውሉም?”

በመጨረሻ ደቀ መዛሙርቱ ነጥቡን አስተዋሉ። ሊጥ እንዲብላላና ኩፍ እንዲል ለማድረግ የሚያገለግለው እርሾ የተባለው ነገር ብክለትን ለማመልከት የገባ ቃል ነው። ስለዚህ ደቀ መዛሙርቱ ኢየሱስ ምሳሌያዊ አነጋገር እንደተጠቀመና ሊበክል ከሚችለው “ከፈሪሳውያንና ከሰዱቃውያን ትምህርት” እንዲጠበቁ ማስጠንቀቁ እንደሆነ ተገነዘቡ።​— ጋደል አድርገን የጻፍነው እኛ ነን። ማርቆስ 8:​1-21፤ ማቴዎስ 15:​32 እስከ 16:​12

▪ ሕዝቡ ትልልቅ የስንቅ መያዣ ቅርጫቶች ይዘው የነበረው ለምንድን ነው?

▪ ኢየሱስ ዲካፖሊስን ከለቀቀ በኋላ በጀልባ ያደረጋቸው ጉዞዎች የትኞቹ ናቸው?

▪ ኢየሱስ ስለ እርሾ የሰጠውን ሐሳብ በተመለከተ ደቀ መዛሙርቱ ምን የተሳሳተ ግንዛቤ አድሮባቸው ነበር?

▪ ኢየሱስ ‘የፈሪሳውያንና የሰዱቃውያን እርሾ’ ሲል ምን ማለቱ ነበር?