በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ከመወለዱ በፊት ክብር ተሰጥቶታል

ከመወለዱ በፊት ክብር ተሰጥቶታል

ምዕራፍ 2

ከመወለዱ በፊት ክብር ተሰጥቶታል

መልአኩ ገብርኤል ዘላለማዊ ንጉሥ የሚሆን ልጅ እንደምትወልድ ለወጣቷ ማርያም ከነገራት በኋላ ማርያም “ወንድ ስለማላውቅ ይህ እንዴት ይሆናል?” ብላ ጠየቀች።

“መንፈስ ቅዱስ በአንቺ ላይ ይመጣል፣” ሲል ገብርኤል ገለጸ፤ “የልዑልም ኃይል ይጸልልሻል። ስለዚህ ደግሞ ከአንቺ የሚወለደው ቅዱሱ የእግዚአብሔር ልጅ ይባላል።”

ማርያም መልእክቱን እንድታምን ለመርዳት ገብርኤል እንዲህ ሲል ቀጠለ:- “እነሆም ዘመድሽ ኤልሳቤጥ፣ እርስዋ ደግሞ በእርጅናዋ ወንድ ልጅ ፀንሳለች፣ ለእርስዋም መካን ትባል ለነበረችው ይህ ስድስተኛ ወር ነው፤ ለእግዚአብሔር የሚሳነው ነገር የለምና።”

ማርያም የገብርኤልን ቃል አምና ተቀበለች። የሰጠችው ምላሽ ምን ነበር? “እነሆኝ የጌታ ባሪያ፤ እንደ ቃልህ ይሁንልኝ” አለች።

ገብርኤል ከሄደ በኋላ ብዙም ሳትቆይ ማርያም ተዘጋጀችና በተራ⁠ራ​­ማው አገር በይሁዳ ከባሏ ከዘካርያስ ጋር የምትኖረውን ኤልሳቤጥን ልትጠይቅ ሄደች። ማርያም ከምትኖርበት ከናዝሬት ተነስቶ እዚያ ለመድረስ ረጅም ጉዞ ማድረግ ይጠይቃል፤ ምናልባትም ጉዞው ሦስት ወይም አራት ቀን ሊወስድ ይችላል።

በመጨረሻ ማርያም ዘካርያስ ቤት ከደረሰች በኋላ ወደ ውስጥ ገብታ ሰላምታ አቀረበች። በዚህ ጊዜ ኤልሳቤጥ በመንፈስ ቅዱስ ተሞልታ ማርያምን እንዲህ አለቻት:- “አንቺ ከሴቶች መካከል የተባረክሽ ነሽ፣ የማኅፀንሽም ፍሬ የተባረከ ነው። የጌታዬ እናት ወደ እኔ ትመጣ ዘንድ እንዴት ይሆንልኛል? እነሆ፣ የሰላምታሽ ድምፅ በጆሮዬ በመጣ ጊዜ ፅንሱ በማኅፀኔ በደስታ ዘሎአልና።”

ማርያም ይህን ስት⁠ሰማ ከልብ በመነጨ የምስጋና ስሜት እንዲህ አለች:- “ነፍሴ ጌታን ታከብረዋለች፣ መንፈሴም በአምላኬ በመድኃኒቴ ሐሴት ታደርጋለች፤ የባሪያይቱን ውርደት ተመልክቶአልና። እነሆም፣ ከዛሬ ጀምሮ ትውልድ ሁሉ ብፅዕት ይሉኛል፤ ብርቱ የሆነ እርሱ በእኔ ታላቅ ሥራ አድርጎአልና።” ሆኖም ማርያም ምንም እንኳ የአምላክን ልዩ ሞገስ ያገኘች ቢሆንም ክብሩን ሁሉ ለአምላክ ሰጥታለች። “ስሙም ቅዱስ ነው። ምሕረቱም ለሚፈሩት እስከ ትውልድና ትውልድ ይኖራል” ስትል ተናግራለች።

ማርያም በመንፈስ አነሳሽነት በተነገረ ትንቢታዊ መዝሙር እንዲህ በማለት አምላክን ማወደሷን ቀጠለች:- “በክንዱ ኃይል አድርጎአል፤ ትዕቢተኞችን በልባቸው አሳብ በትኖአል፤ ገዢዎችን ከዙፋናቸው አዋርዶአል፤ ትሑታንንም ከፍ አድርጎአል፤ የተራቡትን በበጎ ነገር አጥግቦአል፤ ባለ ጠጎችንም ባዶአቸውን ሰዶአቸዋል። ለአባቶቻችን እንደ ተናገረ፣ ለአብርሃምና ለዘሩ ለዘላለም ምሕረቱ ትዝ እያለው እስራኤልን ብላቴናውን ረድቶአል።”

ማርያም ኤልሳቤጥ ጋር ለሦስት ወር ያህል ተቀመጠች፤ የኤልሳቤጥ የመውለጃ ጊዜ በተቃረበባቸው በእነዚህ የመጨረሻ ሳምንታት ማርያም ከፍተኛ እርዳታ እንዳደረገችላት ምንም ጥርጥር የለውም። በአምላክ እርዳታ ልጅ የፀነሱ እነዚህ ሁለት የታመኑ ሴቶች በዚህ የተባረከ የሕይወት ዘመናቸው ወቅት አንድ ላይ መሆን መቻላቸው በእርግጥም በጣም ጥሩ ነበር!

ኢየሱስ ከመወለዱ በፊት እንኳ የተሰጠውን ክብር አስተዋልክ? ኤልሳቤጥ “ጌታዬ” ብላ ጠርታዋለች። በተጨማሪም ማርያም በመጀመሪያ ብቅ ስትል በኤልሳቤጥ ማኅፀን ውስጥ የነበረው ሕፃን በደስታ ዘሏል። በሌላ በኩል ግን ቀጥለን እንደምንመለከተው ሌሎች ሰዎች ማርያምንና በማኅፀኗ ያለውን ሕፃን አክብሮት አላሳዩአቸውም። ሉቃስ 1:​26-56

▪ ማርያም የምትፀንሰው እንዴት እንደሆነ ለማስረዳት ገብርኤል ምን አላት?

▪ ኢየሱስ ከመወለዱ በፊት አክብሮት የተሰጠው እንዴት ነበር?

▪ ማርያም ትንቢታዊ በሆነ መዝሙር አምላክን ስታወድስ ምን አለች?

▪ ማርያም ኤልሳቤጥ ጋር ምን ያህል ጊዜ ቆየች? በዚያ ወቅት ማርያም ኤልሳቤጥ ጋር መቆየቷ ተገቢ የነበረውስ ለምንድን ነው?