በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ከሰማይ የመጡ መልእክቶች

ከሰማይ የመጡ መልእክቶች

ምዕራፍ 1

ከሰማይ የመጡ መልእክቶች

መላው መጽሐፍ ቅዱስ ሰማያዊ አባታችን ለእኛ መመሪያ እንዲሆን ያዘጋጀው ከሰማይ የመጣ መልእክት ነው ማለት ይቻላል። ይሁን እንጂ የዛሬ 2,000 ዓመት ገደማ ‘በእግዚአብሔር ፊት የሚቆም’ አንድ መልአክ ሁለት ልዩ መልእክቶች አድርሷል። ይህ መልአክ ገብርኤል ይባላል። ገብርኤል እነዚህን በጣም አስፈላጊ የሆኑ መልእክቶች ይዞ ወደ ምድር በመጣበት ጊዜ የነበሩትን ሁኔታዎች እስቲ እንመልከት።

ጊዜው በ3 ከዘመናችን አቆጣጠር በፊት ነበር። ዘካርያስ የተባለ አንድ የይሖዋ ካህን በይሁዳ ኮረብቶች ይኖር ነበር፤ ይህ ቦታ ለኢየሩሳሌም ቅርብ የነበረ ሳይሆን አይቀርም። ዘካርያስም ሆነ ሚስቱ ኤልሳቤጥ አርጅተው ነበር። ምንም ልጅ አልነበራቸውም። ዘካርያስ ተራው ደርሶ በኢየሩሳሌም በሚገኘው የአምላክ ቤተ መቅደስ ውስጥ የክህነት አገልግሎት እያከናወነ ነበር። በድንገት ገብርኤል ዕጣኑ በሚጤስበት መሠዊያ በስተቀኝ በኩል ተገለጠ።

ዘካርያስ በጣም ፈራ። ሆኖም ገብርኤል “ዘካርያስ ሆይ፣ ጸሎትህ ተሰምቶልሃልና አትፍራ ሚስትህ ኤልሳቤጥም ወንድ ልጅ ትወልድልሃለች፣ ስሙንም ዮሐንስ ትለዋለህ” በማለት አረጋጋው። ገብርኤል በመቀጠል ዮሐንስ “በጌታ ፊት ታላቅ ይሆናል፤” በተጨማሪም ‘ለይሖዋ የተዘጋጁ ሕዝብ ያሰናዳል’ ሲል ተናገረ።

ሆኖም ዘካርያስ ይህን ሊያምን አልቻለም። ዘካርያስና ኤልሳቤጥ በዚያ ዕድሜያቸው ልጅ ይወልዳሉ ማለት ፈጽሞ የማይታሰብ ነገር ይመስል ነበር። ስለዚህ ገብርኤል “ቃሌን ስላላመንህ፣ ይህ ነገር እስከሚሆን ቀን ድረስ ድዳ ትሆናለህ መናገርም አትችልም” አለው።

ይህ በእንዲህ እንዳለ ውጪ ቆመው የነበሩት ሰዎች ዘካርያስ በቤተ መቅደሱ ውስጥ በጣም በመቆየቱ ግራ ተጋቡ። በመጨረሻ ከቤተ መቅደሱ ሲወጣ በእጆቹ ምልክት ከመስጠት በስተቀር መናገር አልቻለም። በዚህ ጊዜ ተአምራዊ የሆነ ነገር እንደተመለከተ ተገነዘቡ።

ዘካርያስ በቤተ መቅደስ ያከናውን የነበረውን የሰሞን አገልግሎት ከፈጸመ በኋላ ወደ ቤት ተመለሰ። ከዚያ በኋላ ብዙም ሳይቆይ፣ ልክ እንደተባለው ኤልሳቤጥ ፀነሰች! ኤልሳቤጥ ልጅዋ የሚወለድበትን ጊዜ እየተጠባበቀች ከሰዎች ተገልላ ቤት ውስጥ ለአምስት ወራት ያህል ተቀመጠች።

ከጊዜ በኋላ ገብርኤል እንደገና ተገለጠ። በዚህ ጊዜ ያነጋገረው ማንን ነበር? በናዝሬት ከተማ የምትኖረውንና ገና ያላገባችውን ማርያም የምትባል ወጣት ሴት ነበር። በዚህ ወቅት ይዞት የመጣው መልእክት ምን ነበር? ምን እንዳለ አዳምጥ! ገብርኤል “በእግዚአብሔር ፊት ጸጋ አግኝተሻል” ሲል ለማርያም ነገራት። “እነሆም፣ ትፀንሻለሽ ወንድ ልጅም ትወልጃለሽ፣ ስሙንም ኢየሱስ ትዪዋለሽ።” ገብርኤል አክሎም እንዲህ አለ:- “እርሱ ታላቅ ይሆናል የልዑል ልጅም ይባላል፣ . . . በያዕቆብ ቤትም ላይ ለዘላለም ይነግሣል፣ ለመንግሥቱም መጨረሻ የለውም።”

ገብርኤል እነዚህን መልእክቶች እንዲያደርስ የተሰጠውን ተልዕኮ እንደ ትልቅ መብት እንደሚቆጥረው እርግጠኞች ልንሆን እንችላለን። ስለ ዮሐንስና ስለ ኢየሱስ ይበልጥ እያነበብን ስንሄድ እነዚህ ከሰማይ የተላኩ መልእክቶች እጅግ አስፈላጊ የሆኑበትን ምክንያት ይበልጥ ግልጽ በሆነ መንገድ እንረዳለን። 2 ጢሞቴዎስ 3:​16፤ ሉቃስ 1:​5-33

▪ ከሰማይ የተላኩት ሁለት አስፈላጊ መልእክቶች ምንድን ናቸው?

▪ መልእክቶቹን ያደረሰው ማን ነው? መልእክቶቹ የተነገሩትስ ለእነማን ነበር?

▪ መልእክቶቹ ለማመን አዳጋች የነበሩት ለምንድን ነው?