በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

“ከሰማይ የወረደ እውነተኛ እንጀራ”

“ከሰማይ የወረደ እውነተኛ እንጀራ”

ምዕራፍ 54

“ከሰማይ የወረደ እውነተኛ እንጀራ”

ከዚህ ቀን በፊት በነበረው ዕለት ብዙ ነገሮች ተከናውነዋል። ኢየሱስ በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ሰዎችን ተአምራዊ በሆነ መንገድ ከመገበ በኋላ ሕዝቡ እሱን ለማንገሥ ካደረጉት ሙከራ አምልጧል። በዚያው ዕለት ሌሊት በነፋስ ሲናወጥ በነበረው የገሊላ ባሕር ላይ በእግሩ ሄዷል፤ ሲናወጥ በነበረው ውኃ ላይ ሲራመድ መስመጥ ጀምሮ የነበረውን ጴጥሮስን አድኗል፤ እንዲሁም ደቀ መዛሙርቱ የጀልባ መስጠም አደጋ እንዳይደርስባቸው ሲል ማዕበሉን ጸጥ አሰኝቷል።

አሁን ከገሊላ ሰሜናዊ ምሥራቅ በኩል በሚገኝ ሥፍራ ተአምራዊ በሆነ መንገድ የመገባቸው ሰዎች በቅፍርናሆም አቅራቢያ አገኙትና “ወደዚህ መቼ መጣህ?” ብለው ጠየቁት። ኢየሱስ እሱን ፍለጋ የመጡት አሁንም በነፃ ምግብ እናገኛለን ብለው በማሰብ እንጂ በሌላ ምክንያት እንዳልሆነ በመግለጽ ወቀሳቸው። ለሚጠፋ መብል ሳይሆን የዘላለም ሕይወት ለሚያስገኝ መብል እንዲሠሩ አሳሰባቸው። ስለዚህ ሰዎቹ “የእግዚአብሔርን ሥራ እንድንሠራ ምን እናድርግ?” ብለው ጠየቁት።

ኢየሱስ አንድ ከፍተኛ ዋጋ ያለው ሥራ ጠቀሰላቸው። “ይህ የእግዚአብሔር ሥራ እርሱ በላከው እንድታምኑ ነው አላቸው።”

ይሁን እንጂ ሕዝቡ ምንም እንኳ ኢየሱስ ብዙ ተአምራት የፈጸመ ቢሆንም አላመኑበትም። ያን ሁሉ ተአምር ከፈጸመ በኋላ እንኳ ባለማመን እንደሚከተለው ብለው ጠየቁት:- “እንኪያ አይተን እንድናምንህ አንተ ምን ምልክት ታደርጋለህ? ምንስ ትሠራለህ? ይበሉ ዘንድ ከሰማይ እንጀራ ሰጣቸው ተብሎ እንደ ተጻፈ አባቶቻችን በምድረ በዳ መና በሉ።”

ኢየሱስ ምልክት እንዲሰጣቸው ላቀረቡለት ጥያቄ መልስ ሲሰጥ እንደሚከተለው በማለት የተአምራዊ መብል ምንጭ ማን እንደሆነ ገልጿል:- “እውነተኛ እንጀራ ከሰማይ የሚሰጣችሁ አባቴ ነው እንጂ ከሰማይ እንጀራ የሰጣችሁ ሙሴ አይደለም፤ የእግዚአብሔር እንጀራ ከሰማይ የሚወርድ ለዓለምም ሕይወትን የሚሰጥ ነውና።”

ሕዝቡ “ጌታ ሆይ፣ ይህን እንጀራ ዘወትር ስጠን” አሉት።

ኢየሱስ “የሕይወት እንጀራ እኔ ነኝ” ሲል ገለጸ። “ወደ እኔ የሚመጣ ከቶ አይራብም በእኔ የሚያምንም ሁልጊዜ ከቶ አይጠማም። ነገር ግን አይታችሁኝ እንዳላመናችሁ አልኋችሁ። አብ የሚሰጠኝ ሁሉ ወደ እኔ ይመጣል፣ ወደ እኔም የሚመጣውን ከቶ ወደ ውጭ አላወጣውም፤ ፈቃዴን ለማድረግ አይደለም እንጂ የላከኝን ፈቃድ ለማድረግ ከሰማይ ወርጃለሁና። ከሰጠኝም ሁሉ አንድን ስንኳ እንዳላጠፋ በመጨረሻው ቀን እንዳስነሣው እንጂ የላከኝ የአብ ፈቃድ ይህ ነው። ልጅንም አይቶ በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወትን እንዲያገኝ የአባቴ ፈቃድ ይህ ነው።”

ኢየሱስ “ከሰማይ የወረደ እንጀራ እኔ ነኝ” ስላለ አይሁዳውያን ማጉረምረም ጀመሩ። እነርሱ የሚያውቁት ሰብዓዊ ወላጆች የወለዱት ልጅ መሆኑን ብቻ በመሆኑ በናዝሬት የነበሩት ሰዎች እንዳደረጉት እነርሱም እንዲህ በማለት ተቃወሙት:- “አባቱንና እናቱን የምናውቃቸው ይህ የዮሴፍ ልጅ ኢየሱስ አይደለምን? እንግዲህ:- ከሰማይ ወርጃለሁ እንዴት ይላል?”

ኢየሱስ “እርስ በርሳችሁ አታንጎራጉሩ” ሲል መለሰ። “የላከኝ አብ ከሳበው በቀር ወደ እኔ ሊመጣ የሚችል የለም፣ እኔም በመጨረሻው ቀን አስነሣዋለሁ። ሁሉም ከእግዚአብሔር የተማሩ ይሆናሉ ተብሎ በነቢያት ተጽፎአል፤ እንግዲህ ከአብ የሰማ የተማረም ሁሉ ወደ እኔ ይመጣል። አብን ያየ ማንም የለም፤ ከእግዚአብሔር ከሆነ በቀር፣ እርሱ አብን አይቶአል። እውነት እውነት እላችኋለሁ በእኔ የሚያምን የዘላለም ሕይወት አለው።”

ኢየሱስ በመቀጠል ቀደም ሲል የተናገረውን ቃል በመድገም እንዲህ አለ:- “የሕይወት እንጀራ እኔ ነኝ። አባቶቻችሁ በምድረ በዳ መና በሉ ሞቱም፤ ሰው ከእርሱ በልቶ እንዳይሞት ከሰማይ አሁን የወረደ እንጀራ ይህ ነው። ከሰማይ የወረደ ሕያው እንጀራ እኔ ነኝ፤ ሰው ከዚህ እንጀራ ቢበላ ለዘላለም ይኖራል።” አዎን፣ ሰዎች አምላክ ወደ ምድር በላከው በኢየሱስ በማመን የዘላለም ሕይወት ማግኘት ይችላሉ። መናም ሆነ ማንኛውም ሌላ እንጀራ ይህን ሊያስገኝ አይችልም!

ከሰማይ የወረደውን እንጀራ በተመለከተ ውይይቱ የተከፈተው ሕዝቡ ኢየሱስን በቅፍርናሆም አቅራቢያ ካገኙት ከጥቂት ጊዜ በኋላ ሳይሆን አይቀርም። ሆኖም ውይይቱ የተቋጨው ኢየሱስ ከጊዜ በኋላ በቅፍርናሆም ውስጥ በሚገኝ አንድ ምኩራብ ባስተማረበት ጊዜ ነበር። ዮሐንስ 6:​25-51, 59፤ መዝሙር 78:​24፤ ኢሳይያስ 54:​13፤ ማቴዎስ 13:​55-57

▪ ኢየሱስ ከሰማይ የወረደውን እንጀራ በተመለከተ ውይይት ከማድረጉ በፊት ምን ነገሮች ተከናውነዋል?

▪ ምልክት መጠየቃቸው ተገቢ አልነበረም የምንለው ኢየሱስ ምን ነገር ፈጽሞ ስለነበረ ነው?

▪ አይሁዳውያን ኢየሱስ ከሰማይ የወረደ እውነተኛ እንጀራ እኔ ነኝ በማለቱ ያጉረመረሙት ለምንድን ነው?

▪ ከሰማይ የወረደውን እንጀራ በተመለከተ ውይይት የተደረገው የት ነበር?