በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ከሰው በላይ ኃይል ያለው ተፈላጊ ገዥ

ከሰው በላይ ኃይል ያለው ተፈላጊ ገዥ

ምዕራፍ 53

ከሰው በላይ ኃይል ያለው ተፈላጊ ገዥ

ኢየሱስ በሺህ የሚቆጠሩትን ሰዎች ተአምራዊ በሆነ መንገድ በመገበ ጊዜ ሰዎቹ በጣም ተደነቁ። “ይህ በእውነት ወደ ዓለም የሚመጣው ነቢይ ነው” ሲሉ ተናገሩ። ከሙሴ እንደሚበልጥ የተነገረለት ነቢይ ኢየሱስ መሆን አለበት የሚል መደምደሚያ ላይ ከመድረሳቸውም በላይ ከሁሉ የተሻለ ገዥ መሆን ይችላል የሚል እምነት አደረባቸው። ስለዚህ ይዘው ሊያነግሡት ፈለጉ።

ይሁን እንጂ ኢየሱስ ሰዎቹ ምን እንዳሰቡ አውቆ ነበር። ስለዚህ ኃይል ተጠቅመው እንዳያነግሡት ወዲያውኑ እርምጃ ወሰደ። ሕዝቡን አሰናበተና ደቀ መዛሙርቱ በጀልባቸው ወደ ቅፍርናሆም እንዲመለሱ ግድ አላቸው። ከዚያም ለመጸለይ ወደ ተራራ ወጣ። በዚያ ሌሊት ኢየሱስ ብቻውን ነበር።

ሌሊቱ ከመንጋቱ ትንሽ ቀደም ብሎ ኢየሱስ ከፍ ያለ ቦታ ላይ ሆኖ ሲመለከት ኃይለኛ ነፋስ የባሕሩን ሞገድ እያናወጠው ነበር። ጊዜው ከማለፍ በዓል ጥቂት ቀደም ብሎ ስለነበረ ሙሉ ልትሆን ምንም ያህል ያልቀራት ጨረቃ በፈነጠቀችው ብርሃን አማካኝነት ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱ ማዕበሉን እየሰነጠቁ ለመጓዝ የሚያደርጉትን ትግል ተመለከተ። ሰዎቹ ባለ በሌለ ኃይላቸው እየቀዘፉ ነበር።

ኢየሱስ ይህን ሲመለከት ከተራራው ወረደና በሚናወጠው ሞገድ ላይ እየተራመደ ወደ ጀልባዋ መሄድ ጀመረ። ኢየሱስ ወደ ጀልባዋ በደረሰበት ጊዜ ጀልባዋ ከዳርቻው ከአምስት እስከ ስድስት ኪሎ ሜትር ያህል ርቃ ነበር። ይሁን እንጂ ልክ በዚያ እንደሚያልፍ ሰው በውኃው ላይ መጓዙን ቀጠለ። ደቀ መዛሙርቱ ሲያዩት “ምትሐት ነው” ብለው ጮኹ።

ኢየሱስ “እኔ ነኝ፤ አትፍሩ” በማለት የሚያረጋጋ መልስ ሰጣቸው።

ይሁን እንጂ ጴጥሮስ “ጌታ ሆይ፣ አንተስ ከሆንህ በውኃው ላይ ወደ አንተ እንድመጣ እዘዘኝ” አለው።

ኢየሱስ “ና” አለው።

በዚህ ጊዜ ጴጥሮስ ከጀልባው ላይ ወረደና እየተራመደ ወደ ኢየሱስ መምጣት ጀመረ። ሆኖም ጴጥሮስ ማዕበሉን አይቶ በመፍራት መስመጥ ሲጀምር “ጌታ ሆይ፣ አድነኝ” ብሎ ጮኸ።

ወዲያውኑ ኢየሱስ እጁን ዘርግቶ ያዘውና “አንተ እምነት የጎደለህ፣ ስለ ምን ተጠራጠርህ?” አለው።

ጴጥሮስና ኢየሱስ ጀልባዋ ላይ ከወጡ በኋላ ነፋሱ ቆመ፤ ደቀ መዛሙርቱም በጣም ተገረሙ። ግን ይህ ሊያስደንቃቸው ይገባ ነበርን? ኢየሱስ ከጥቂት ሰዓታት በፊት በአምስት እንጀራዎችና በሁለት ትንንሽ ዓሦች ብቻ በሺህ የሚቆጠሩ ሰዎችን በመመገብ የፈጸመውን ታላቅ ተአምር በማድነቅ ‘የእንጀራውን ተአምር’ ትርጉም አስተውለው ቢሆን ኖሮ በውኃ ላይ መራመድ መቻሉና ነፋሱን ማቆሙ ይህን ያህል ባላስደነቃቸው ነበር። ይሁን እንጂ አሁን ደቀ መዛሙርቱ “በእውነት የእግዚአብሔር ልጅ ነህ” ብለው ሰገዱለት።

በጥቂት ጊዜ ውስጥ ጌንሴሬጥ ተብላ ወደምትጠራው በቅፍርናሆም አቅራቢያ ወደምትገኘው ውብና ፍሬያማ ምድር ደረሱ። በዚያም ጀልባዋ መልሕቋን ጣለች። ሆኖም ወደ ባሕሩ ዳርቻ ሲሄዱ ሰዎቹ ኢየሱስን አወቁትና በአካባቢው ወዳለው አገር ሄደው የታመሙ ሰዎችን ይዘው መጡ። ሕመምተኞቹ በቃሬዛ ይመጡና የኢየሱስን ልብስ ጫፍ ሲነኩ ሙሉ በሙሉ ጤነኞች ይሆኑ ነበር።

ይህ በእንዲህ እንዳለ ኢየሱስ ተአምራዊ በሆነ መንገድ በሺህ የሚቆጠሩ ሰዎችን ሲመግብ በቦታው የነበሩት ሰዎች ኢየሱስ አካባቢውን ለቆ እንደሄደ ተረዱ። ስለዚህ ትንንሽ ጀልባዎች ከጥብርያዶስ ሲመጡ ተሳፈሩና ኢየሱስን ለማግኘት ወደ ቅፍርናሆም መጡ። ኢየሱስን ሲያገኙት “መምህር ሆይ፣ ወደዚህ መቼ መጣህ?” ብለው ጠየቁት። ቀጥሎ እንደምንመለከተው ኢየሱስ እነዚህን ሰዎች ወቅሷቸዋል። ዮሐንስ 6:​14-25፤ ማቴዎስ 14:​22-36፤ ማርቆስ 6:​45-56

▪ ኢየሱስ በሺህ የሚቆጠሩትን ሰዎች ከመገበ በኋላ ሰዎቹ ምን ሊያደርጉት ፈልገው ነበር?

▪ ኢየሱስ ከወጣበት ተራራ ላይ ሆኖ ምን ተመለከተ? ከዚያስ ምን አደረገ?

▪ ደቀ መዛሙርቱ በእነዚህ ነገሮች በጣም መደነቅ ያልነበረባቸው ለምንድን ነው?

▪ ወደ ባሕሩ ዳርቻ ከደረሱ በኋላ ምን ነገር ተፈጸመ?