በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ከአንድ ፈሪሳዊ ጋር ምሳ በላ

ከአንድ ፈሪሳዊ ጋር ምሳ በላ

ምዕራፍ 76

ከአንድ ፈሪሳዊ ጋር ምሳ በላ

ኢየሱስ መናገር የማይችለውን ሰው የፈወሰበትን ኃይል በተመለከተ ጥያቄ ላነሱት ተቺዎች መልስ ከሰጠ በኋላ አንድ ፈሪሳዊ ምሳ ጋበዘው። ፈሪሳውያኑ ከመብላታቸው በፊት ሃይማኖታዊ ወጋቸውን በመከተል እጃቸውን እስከ ክርናቸው ድረስ ይታጠባሉ። ምግብ ከመብላታቸው በፊትና በኋላ አልፎ ተርፎም በየጣልቃው እንዲህ ያደርጉ ነበር። ምንም እንኳ ይህ ልማድ በጽሑፍ የሰፈረውን የአምላክ ሕግ የሚያስጥስ ባይሆንም አምላክ በሃይማኖታዊ ሥርዓቶች ላይ ሊደረግ ስለሚገባው የንጽህና አጠባበቅ ከሰጠው መመሪያ አልፎ የሚሄድ ነበር።

ኢየሱስ ይህን ወግ ሳይጠብቅ በመቅረቱ ጋባዡ በጣም ተገረመ። የተሰማውን የመገረም ስሜት በቃላት አውጥቶ ያልተናገረው ሊሆን ቢችልም እንኳ ኢየሱስ ስሜቱን በመረዳት እንዲህ አለ:- “አሁን እናንተ ፈሪሳውያን የጽዋውንና የወጭቱን ውጭ ታጠራላችሁ፣ ውስጣችሁ ግን ቅሚያና ክፋት ሞልቶበታል። እናንት ደንቆሮዎች [“ሞኞች፣” የ1980 ትርጉም]፣ የውጭውን የፈጠረ የውስጡን ደግሞ አልፈጠረምን?”

በዚህ መንገድ ኢየሱስ ሃይማኖታዊ ወግ በመከተል እጃቸውን የሚታጠቡትን ሆኖም ልባቸውን ከክፋት ያላጠሩትን ፈሪሳውያን ግብዝነት አጋልጧል። “በውስጥ ያለውን ምጽዋት አድርጋችሁ ስጡ፣ እነሆም ሁሉ ንጹሕ ይሆንላችኋል” ሲል መከራቸው። መስጠት ያለባቸው ለይምሰል በሚያደርጉት ጽድቅ የሌሎችን ትኩረት ለመሳብ በመፈለግ ሳይሆን ልባቸው በፍቅር ገፋፍቷቸው መሆን ነበረበት።

“እናንተ ፈሪሳውያን፣” በማለት ኢየሱስ ቀጠለ፤ “ከአዝሙድና ከጤና አዳም ከአትክልትም ሁሉ አሥራት ስለምታወጡ፣ ፍርድንና እግዚአብሔርን መውደድ ስለምትተላለፉ፣ ወዮላችሁ፤ ነገር ግን ሌላውን ሳትተዉ ይህን ልታደርጉት ይገባችሁ ነበር።” እስራኤላውያን ካመረቱት ምርት አሥራት ወይም አንድ አሥረኛውን እንዲከፍሉ የአምላክ ሕግ ያዛቸው ነበር። አዝሙድና ጤና አዳም ምግብን ለማጣፈጥ የሚያገለግሉ ትንንሽ ተክሎች ናቸው። ፈሪሳውያን የእነዚህን አነስተኛ ተክሎች አሥራት እንኳ ሳይቀር በሚገባ ይከፍሉ ነበር፤ ሆኖም ፍቅርና ደግነት እንዲሁም ልቆ ለመታየት ያለመፈለግ ባሕርይን ማሳየት የሚጠይቀውን ይበልጥ አስፈላጊ የሆነ ደንብ ባለመጠበቃቸው ኢየሱስ አውግዟቸዋል።

በተጨማሪም ኢየሱስ እንዲህ ሲል አውግዟቸዋል:- “እናንተ ፈሪሳውያን፣ በምኵራብ የከበሬታ ወንበር በገበያም ሰላምታ ስለምትወዱ፣ ወዮላችሁ። እናንተ ግብዞች ጻፎችና ፈሪሳውያን፣ ሰዎች ሳያውቁ በላዩ የሚሄዱበት የተሰወረ መቃብር ስለምትመስሉ፣ ወዮላችሁ።” ርኩሰታቸው በግልጽ የሚታይ አልነበረም። የፈሪሳውያን ሃይማኖት ውጫዊ መልክ ያለው ቢሆንም ውስጡ ግን ባዶ ነበር! በግብዝነት ላይ የተመሠረተ ነበር።

የአምላክን ሕግ በሚገባ ከሚያውቁት ሰዎች አንዱ የሆነ አንድ ሕግ ዐዋቂ ይህን ነቀፋ ሲሰማ “መምህር ሆይ፣ ይህን ማለትህ እኛን ደግሞ መስደብህ ነው” ሲል ቅሬታ አሰማ።

ኢየሱስ እንደሚከተለው በማለት እነዚህን ሕግ ዐዋቂዎችም ተጠያቂ አደረጋቸው:- “እናንተ ደግሞ ሕግ አዋቂዎች፣ አስቸጋሪ ሸክም ለሰዎች ስለምታሸክሙ፣ ራሳችሁም በአንዲት ጣታችሁ ስንኳ ሸክሙን ስለማትነኩት፣ ወዮላችሁ። አባቶቻችሁ የገደሉአቸውን የነቢያትን መቃብር ስለምትሠሩ፣ ወዮላችሁ።”

ኢየሱስ የጠቀሰው ሸክም በቃል የሚነገረውን ወግ የሚያመለክት ነው፤ ሆኖም እነዚህ ሕግ ዐዋቂዎች ሸክሙን ለሕዝቡ ለማቅለል አንድ አነስተኛ ደንብ እንኳ ለማስቀረት አልሞከሩም። ኢየሱስ በነቢያት መገደል የተስማሙ መሆናቸውን በመግለጽ እንዲህ ሲል አስጠነቀቃቸው:- “ዓለም ከተፈጠረ ጀምሮ የፈሰሰው የነቢያት ሁሉ ደም፣ ከአቤል ደም ጀምሮ በመሠዊያውና በቤተ መቅደስ መካከል እስከ ጠፋው እስከ ዘካርያስ ደም ድረስ፣ ከዚህ ትውልድ እንዲፈለግ አዎን እላችኋለሁ፣ ከዚህ ትውልድ ይፈለጋል።”

ከኃጢአት ሊቤዥ የሚችለው የሰው ዘር ዓለም የተመሠረተው የአዳምና የሔዋን ልጆች ከተወለዱበት ጊዜ ጀምሮ ነው፤ ስለዚህ አቤል የኖረው ‘ዓለም በተፈጠረበት ጊዜ ነው።’ በዘካርያስ ላይ አረመኔያዊ ግድያ ከተፈጸመ በኋላ የሶርያ ሠራዊት ይሁዳን በዘበዘ። ሆኖም ኢየሱስ በእሱ ዘመን የነበረው ትውልድ ከዚያ የባሰ ክፉ በመሆኑ የከፋ ጥፋት እንደሚጠብቀው ተነበየ። ይህ ጥፋት ከ38 ዓመታት በኋላ በ70 እንደ ዘመናችን አቆጣጠር ላይ ተፈጽሟል።

ኢየሱስ በመቀጠል እንዲህ ሲል አወገዛቸው:- “እናንተ ሕግ አዋቂዎች፣ የእውቀትን መክፈቻ ስለ ወሰዳችሁ፣ ወዮላችሁ ራሳችሁ አልገባችሁም የሚገቡትንም ከለከላችሁ።” ሕግ ዐዋቂዎቹ የአምላክን ቃል ለሕዝቡ በማብራራት ትርጉሙን የመፍታት ግዴታ ነበረባቸው። ሆኖም ይህን አላደረጉም፤ እንዲያውም ሕዝቡ ቃሉን መረዳት የሚችልበትን አጋጣሚ እንዲያጣ አድርገውታል።

ፈሪሳውያንና ሕግ ዐዋቂዎቹ ኢየሱስ ስላጋለጣቸው በጣም ተናደዱ። ከቤቱ ወጥቶ ሲሄድ ክፉኛ ይቃወሙትና የጥያቄ መዓት ያዥጎደጉዱበት ጀመር። እርሱን ለማስያዝ የሚያስችላቸው ነገር እንዲናገር በመገፋፋት ሊያጠምዱት ሞከሩ። ሉቃስ 11:​37-54፤ ዘዳግም 14:​22፤ ሚክያስ 6:​8፤ 2 ዜና መዋዕል 24:​20-25

▪ ኢየሱስ ፈሪሳውያንንና ሕግ ዐዋቂዎቹን ያወገዘው ለምንድን ነው?

▪ ሕግ ዐዋቂዎቹ በሕዝቡ ላይ ምን ሸክም ጭነውባቸው ነበር?

▪ ‘ዓለም የተፈጠረበት ጊዜ’ መቼ ነው?