በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ከኢያኢሮስ ቤት ወጥቶ እንደገና ወደ ናዝሬት ተጓዘ

ከኢያኢሮስ ቤት ወጥቶ እንደገና ወደ ናዝሬት ተጓዘ

ምዕራፍ 48

ከኢያኢሮስ ቤት ወጥቶ እንደገና ወደ ናዝሬት ተጓዘ

ኢየሱስ ቀኑን ያሳለፈው በሥራ ተጠምዶ ነበር፤ ከዲካፖሊስ በባሕር ላይ ተጉዞ መጣ፣ ደም ይፈስሳት የነበረችውን ሴት ፈወሰ፣ ከዚያም የኢያኢሮስን ልጅ ከሞት አስነሳ። ይሁን እንጂ ቀኑ ገና አልመሸም ነበር። ሁለት ዓይነ ስውሮች “የዳዊት ልጅ ሆይ፣ ማረን” እያሉ ተከተሉት፤ ይህ የሆነው ኢየሱስ ከኢያኢሮስ ቤት ወጥቶ ሲሄድ እንደሆነ ከሁኔታው መረዳት ይቻላል።

እነዚህ ሰዎች ኢየሱስን “የዳዊት ልጅ” ብለው በመጥራት ኢየሱስ የዳዊትን ዙፋን እንደሚወርስና በተስፋ ሲጠበቅ የነበረው መሲሕ መሆኑን እንደሚያምኑ አሳይተዋል። ይሁን እንጂ ኢየሱስ ለእርዳታ ያሰሙትን ጩኸት በቸልታ ያለፈው ይመስል ነበር። ምናልባትም ይህን ያደረገው ጽናታቸውን ለመፈተን ይሆናል። ሆኖም ሰዎቹ ተስፋ አልቆረጡም። ወደሚሄድበት ቤት ተከትለውት ሄዱ፤ ወደ ቤት ሲገባም ተከትለውት ገቡ።

ከገቡ በኋላ ኢየሱስ “ይህን ማድረግ እንድችል ታምናላችሁን?” ሲል ጠየቃቸው።

“አዎን፣ ጌታ ሆይ” ብለው በእርግጠኝነት መለሱለት።

ስለዚህ ኢየሱስ ዓይኖቻቸውን ዳሰሰና “እንደ እምነታችሁ ይሁንላችሁ” አላቸው። ወዲያውኑ ማየት ቻሉ! ከዚያም ኢየሱስ “ማንም እንዳያውቅ ተጠንቀቁ” በማለት አጥብቆ አዘዛቸው። ሆኖም በጣም ከመደሰታቸው የተነሣ የኢየሱስን ትእዛዝ ችላ በማለት ወሬውን በገጠሩ ሁሉ አዳረሱት።

እነዚህ ሰዎች እንደሄዱ ሌሎች ሰዎች ጋኔን የያዘው አንድ ሰው ይዘው መጡ። ጋኔኑ የሰውየውን ልሳን ዘግቶት ነበር። ኢየሱስ ጋኔኑን ሲያስወጣው ሰውየው ወዲያውኑ መናገር ጀመረ። ሕዝቡ በእነዚህ ተአምራት በመደነቅ “እንዲህ ያለ በእስራኤል ዘንድ ከቶ አልታየም” አሉ።

ፈሪሳውያንም በቦታው ተገኝተው ነበር። ተአምራቱን መካድ አይችሉም፤ ሆኖም ሆን ብለው ለማመን ባለመፈለጋቸው “በአጋንንት አለቃ አጋንንትን ያወጣል” በማለት ኢየሱስ ተአምራቱን የሚፈጽምበትን ኃይል በተመለከተ የቀድሞ ክሳቸውን በድጋሚ ሰንዝረዋል።

እነዚህ ነገሮች ከተፈጸሙ በኋላ ብዙም ሳይቆይ ኢየሱስ ወዳደገባት ከተማ ወደ ናዝሬት ተመለሰ። በዚህ ጊዜ ደቀ መዛሙርቱ አብረውት ነበሩ። ከአንድ ዓመት ገደማ በፊት በዚያ ወዳለው ምኩራብ ሄዶ አስተምሮ ነበር። ሰዎቹ በመጀመሪያ ማራኪ በሆኑት ቃላቱ ተደንቀው የነበረ ቢሆንም በኋላ ግን በትምህርቱ በመበሳጨት ሊገድሉት ሞክረው ነበር። አሁን ኢየሱስ የምሕረት መንፈስ በማሳየት የቀድሞ ጎረቤቶቹን ለመርዳት ሌላ ሙከራ አደረገ።

በሌሎች ቦታዎች ብዙ ሕዝብ ወደ ኢየሱስ ይጎርፍ የነበረ ሲሆን በዚህ ሥፍራ ግን ይህ ሁኔታ የነበረ አይመስልም። ስለዚህ በሰንበት ቀን በምኩራብ ለማስተማር ሄደ። ሲያዳምጡት የነበሩት አብዛኞቹ ሰዎች በጣም ተደነቁ። “ይህን ጥበብና ተአምራት ይህ ከወዴት አገኘው?” ሲሉ ጠየቁ። “ይህ የጸራቢ ልጅ አይደለምን? እናቱስ ማርያም ትባል የለምን? ወንድሞቹስ ያዕቆብና ዮሳ ስምዖንም ይሁዳም አይደሉምን? እኅቶቹስ ሁሉ በእኛ ዘንድ ያሉ አይደሉምን? እንኪያስ ይህን ሁሉ ከወዴት አገኘው?”

‘ኢየሱስ እንደ እኛው የዚች ከተማ ሰው ነው’ ሲሉ አሰቡ። ‘ከልጅነቱ ጀምሮ እናውቀዋለን፤ ቤተሰቦቹንም እናውቃቸዋለን። እርሱ እንዴት መሲሕ ሊሆን ይችላል?’ ታላቅ ጥበቡና ተአምራቱ በቂ ማስረጃ ቢሆንም ሰዎቹ ኢየሱስን አልተቀበሉትም። የራሱ ዘመዶች እንኳ ሳይቀሩ የቅርብ ትውውቃቸው እንዲሰናከሉበት አድርጓቸዋል። ይህም ኢየሱስ “ነቢይ ከገዛ አገሩና ከገዛ ዘመዶቹ ከገዛ ቤቱም በቀር ሳይከበር አይቀርም” ብሎ እንዲደመድም አድርጎታል።

በእርግጥም ኢየሱስ እምነት የጎደላቸው መሆኑ አስገርሞታል። ስለዚህ በጥቂት ሕሙማን ላይ እጁን በመጫን ከመፈወሱ በቀር በዚህች ከተማ ሌላ ተአምር አልፈጸመም። ማቴዎስ 9:​27-34፤ 13:​54-58፤ ማርቆስ 6:​1-6፤ ኢሳይያስ 9:​7

▪ ዓይነ ስውር የነበሩት ሰዎች ኢየሱስን “የዳዊት ልጅ” ብለው በመጥራት ምን እምነት እንደነበራቸው አሳይተዋል?

▪ ፈሪሳውያን ኢየሱስ የፈጸማቸውን ተአምራት በተመለከተ ምን ሰበብ ፈጥረዋል?

▪ ኢየሱስ በናዝሬት የሚገኙትን ሰዎች ለመርዳት መመለሱ ምሕረቱን የሚያሳይ ነው የምንለው ለምንድን ነው?

▪ ኢየሱስ በናዝሬት የተደረገለት አቀባበል ምን ዓይነት ነው? ለምንስ?