በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ከጨካኝ ገዥ እጅ ማምለጥ

ከጨካኝ ገዥ እጅ ማምለጥ

ምዕራፍ 8

ከጨካኝ ገዥ እጅ ማምለጥ

ዮሴፍ ከእንቅልፉ ሲነሳ ለማርያም አንድ አስቸኳይ መልእክት ነገራት። የይሖዋ መልአክ ሌሊት ተገልጦለት እንዲህ አለው:- “ሄሮድስ ሕፃኑን ሊገድለው ይፈልገዋልና ተነሣ፣ ሕፃኑንና እናቱንም ይዘህ ወደ ግብፅ ሽሽ፣ እስክነግርህም ድረስ በዚያ ተቀመጥ።”

ሦስቱም በፍጥነት ሸሽተው አመለጡ። ሄሮድስ ኮከብ ቆጣሪዎቹ እንዳታለሉትና ወደ አገራቸው እንደተመለሱ አውቆ ስለነበር የሸሹት ጥሩ ጊዜ ላይ ነበር። ኮከብ ቆጣሪዎቹ ኢየሱስን ሲያገኙት ተመልሰው እንዲነግሩት ታዘው እንደነበር አስታውስ። ሄሮድስ በጣም ተናደደ። ስለዚህ ኢየሱስን ለመግደል ሲል በቤተ ልሔምና በአውራጃዋ ውስጥ ያሉት ሁለት ዓመት የሆናቸውና ከዚያም የሚያንሱት ወንድ ልጆች በሙሉ እንዲገደሉ አዘዘ። ይህን ዕድሜ ያሰላው ቀደም ሲል ከምሥራቅ የመጡት ኮከብ ቆጣሪዎች በሰጡት መረጃ ላይ በመመርኮዝ ነበር።

የእነዚያን ሁሉ ሕፃናት እልቂት መመልከቱ በጣም የሚሰቀጥጥ ነበር! የሄሮድስ ወታደሮች ኃይል በመጠቀም ከአንዱ ቤት ወደ ሌላው ይገቡ ነበር። ወንድ ልጅ ሲያገኙም ከእናቱ እጅ መንጭቀው ይወስዱት ነበር። ምን ያህል ሕፃናት እንደገደሉ ባናውቅም የእናቶቹ ከፍተኛ ልቅሶና ጩኸት የአምላክ ነቢይ በነበረው በኤርምያስ የተነገረ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኝ አንድ ትንቢት እንዲፈጸም አድርጓል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ ዮሴፍና ቤተሰቡ በሰላም ግብፅ ደረሱ፤ አሁን በዚያ መኖር ጀምረዋል። ሆኖም አንድ ቀን ሌሊት የይሖዋ መልአክ እንደገና ለዮሴፍ በሕልም ተገለጠለት። መልአኩ “የሕፃኑን ነፍስ የፈለጉት ሞተ​­ዋልና ተነሣ፣ ሕፃኑን እናቱንም ይዘህ ወደ እስራኤል አገር ሂድ” አለው። የአምላክ ልጅ ከግብፅ እንደሚጠራ የሚናገር ሌላ የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት ይፈጸም ዘንድ ቤተሰቡ ወደ ትውልድ አገሩ ተመለሰ።

ዮሴፍ ወደ ግብፅ ከመሸሻቸው በፊት ይኖሩባት የነበረችው የቤተ ልሔም ከተማ በምትገኝበት በይሁዳ ለመኖር ፈልጎ የነበረ ይመስላል። ሆኖም ክፉው የሄሮድስ ልጅ አርኬላዎስ በይሁዳ እንደ ነገሠ ተረዳ። በተጨማሪም ወደዚያ መሄዱ አደገኛ እንደሆነ ይሖዋ በሌላ ሕልም አስጠነቀቀው። ስለዚህ ዮሴፍና ቤተሰቡ ወደ ሰሜን ተጉዘው በገሊላ ውስጥ በምትገኘው በናዝሬት ከተማ መኖር ጀመሩ። ኢየሱስ ከአይሁድ የሃይማኖታዊ እንቅስቃሴ ማዕከል ርቆ በዚህ ማኅበረሰብ ውስጥ አደገ። ማቴዎስ 2:​13-23፤ ኤርምያስ 31:​15፤ ሆሴዕ 11:​1

▪ ኮከብ ቆጣሪዎቹ ሳይመለሱ በቀሩ ጊዜ ንጉሥ ሄሮድስ ምን አሠቃቂ ነገር ፈጸመ? ሆኖም ኢየሱስ ሊድን የቻለው እንዴት ነው?

▪ ዮሴፍ ከግብፅ ከተመለሰ በኋላ እንደገና በቤተ ልሔም ያልተቀመጠው ለምንድን ነው?

▪ በዚህ ጊዜ ውስጥ የትኞቹ የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶች ተፈጽመዋል?