በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ከጲላጦስ ወደ ሄሮድስ ከዚያም እንደገና ወደ ጲላጦስ ተወሰደ

ከጲላጦስ ወደ ሄሮድስ ከዚያም እንደገና ወደ ጲላጦስ ተወሰደ

ምዕራፍ 122

ከጲላጦስ ወደ ሄሮድስ ከዚያም እንደገና ወደ ጲላጦስ ተወሰደ

ኢየሱስ ንጉሥ መሆኑን ከጲላጦስ ለመደበቅ አንዳችም ሙከራ ያላደረገ ቢሆንም መንግሥቱ በሮም መንግሥት ላይ ምንም የሚፈጥረው ስጋት እንደሌለ ገለጸ። ኢየሱስ “መንግሥቴ ከዚህ ዓለም አይደለችም” አለው። “መንግሥቴስ ከዚህ ዓለም ብትሆን፣ ወደ አይሁድ እንዳልሰጥ ሎሌዎቼ ይዋጉልኝ ነበር፤ አሁን ግን መንግሥቴ ከዚህ አይደለችም።” በዚህ መንገድ ኢየሱስ ምንም እንኳ መንግሥቱ ምድራዊ ባይሆንም መንግሥት እንዳለው ሦስት ጊዜ ገልጿል።

ሆኖም ጲላጦስ “እንግዲያ ንጉሥ ነህን?” ሲል አጥብቆ ጠየቀው። መንግሥትህ ከዚህ ዓለም ባይሆንም እንኳ ንጉሥ ነህን? ማለቱ ነበር።

ኢየሱስ የሚከተለውን መልስ በመስጠት ጲላጦስ ትክክለኛ መደምደሚያ ላይ እንደደረሰ እንዲገነዘብ አደረገው:- “እኔ ንጉሥ እንደ ሆንሁ አንተ ትላለህ። እኔ ለእውነት ልመሰክር ስለዚህ ተወልጃለሁ ስለዚህም ወደ ዓለም መጥቻለሁ፤ ከእውነት የሆነ ሁሉ ድምፄን ይሰማል።”

አዎን፣ ኢየሱስ ወደ ምድር የመጣው “ለእውነት” ለመመስከር፣ በተለይም ስለ መንግሥቱ የሚገልጸውን እውነት ለመመስከር ነው። ኢየሱስ ሕይወቱን የሚያሳጣው ቢሆን እንኳ ለዚህ እውነት ታማኝ ሆኖ ለመገኘት ዝግጁ ነው። ጲላጦስ “እውነት ምንድር ነው?” ብሎ የጠየቀው ቢሆንም እንኳ ተጨማሪ ማብራሪያ ለማግኘት አልፈለገም። ፍርድ ለመስጠት የሚያስችል በቂ ነገር አግኝቷል።

ጲላጦስ ከቤተ መንግሥቱ ውጪ ሆኖ ወደሚጠባበቀው ሕዝብ ተመለሰ። ከሁኔታው መረዳት እንደሚቻለው ኢየሱስን ጎኑ አቁሞ የካህናት አለቆቹንና አብረዋቸው ያሉትን ሰዎች “በዚህ ሰው አንድ በደል ስንኳ አላገኘሁበትም” አላቸው።

ሕዝቡ በውሳኔ ተበሳጭተው ግትር አቋም በመያዝ “ከገሊላ ጀምሮ እስከዚህ ድረስ በይሁዳ ሁሉ እያስተማረ ሕዝቡን ያውካል” አሉ።

የአይሁዶቹ ጭፍን የሆነ ግትር አቋም ጲላጦስን ሳያስገርመው አይቀርም። ስለዚህ የካህናት አለቆቹና የሕዝቡ ሽማግሌዎች መጮኻቸውን ሲቀጥሉ ጲላጦስ ወደ ኢየሱስ ዞር አለና “ስንት ያህል እንዲመሰክሩብህ አትሰማምን?” ሲል ጠየቀው። ሆኖም ኢየሱስ ምንም መልስ አልሰጠም። ኢየሱስ ይህን ሁሉ መሠረተ ቢስ የሆነ ክስ ሲሰነዝሩበት ዝም ማለቱ ጲላጦስን አስደነቀው።

ጲላጦስ ኢየሱስ የገሊላ ሰው መሆኑን ሲያውቅ ራሱን ከኃላፊነት ነፃ የሚያደርግበት መንገድ አገኘ። የገሊላ ገዥ የሆነው ሄሮድስ አንቲጳስ (የታላቁ ሄሮድስ ልጅ) የማለፍ በዓሉን ለማክበር ወደ ኢየሩሳሌም መጥቶ ነበር፤ ስለዚህ ጲላጦስ ኢየሱስን ወደ እርሱ ሰደደው። ቀደም ሲል ሄሮድስ አንቲጳስ የአጥማቂው ዮሐንስ ራስ እንዲቆረጥ አድርጓል። ከዚያም ሄሮድስ ኢየሱስ እየፈጸማቸው ስለነበሩት ተአምራት ሲሰማ ዮሐንስ ከሞት እንደተነሳና ኢየሱስ የተባለው እሱ እንደሆነ አድርጎ በማሰብ ፈርቶ ነበር።

አሁን ሄሮድስ ኢየሱስን የሚያይበት አጋጣሚ በማግኘቱ በጣም ተደሰተ። ሄሮድስ የተደሰተው ስለ ኢየሱስ ደህንነት አስቦ ወይም ደግሞ በኢየሱስ ላይ የተነሱት ክሶች እውነተኛ መሆን አለመሆናቸውን በሚገባ ለማጣራት ፈልጎ አይደለም። ከዚህ ይልቅ ኢየሱስ የሆነ ተአምር ሲፈጽም ለማየት ይመኝና ተስፋ ያደርግ ስለነበረ ብቻ ነው።

ይሁን እንጂ ኢየሱስ ሄሮድስ የጓጓለትን ነገር ለመፈጸም ፈቃደኛ አልሆነም። እንዲያውም ሄሮድስ ሲጠይቀው አንድም ቃል አልተነፈሰም። ሄሮድስና ዘብ ጠባቂዎቹ ኢየሱስን እንደጠበቁት ሆኖ ሳላላገኙት ተሳለቁበት። የሚያብረቀርቅ ልብስ አልብሰው አሾፉበት። ከዚያም ወደ ጲላጦስ መልሰው ላኩት። በዚህም ምክንያት ቀደም ሲል ጠላቶች የነበሩት ሄሮድስና ጲላጦስ አሁን ጥሩ ወዳጆች ሆኑ።

ኢየሱስ ተመልሶ ሲመጣ ጲላጦስ የካህናት አለቆችን፣ የአይሁድ መሪዎችንና ሕዝቡን አንድ ላይ ጠርቶ እንዲህ አላቸው:- “ሕዝቡን ያጣምማል ብላችሁ ይህን ሰው ወደ እኔ አመጣችሁት፤ እነሆም፣ በፊታችሁ መርምሬ ከምትከሱበት ነገር አንድ በደል ስንኳ በዚህ ሰው አላገኘሁበትም። ሄሮድስም ደግሞ ምንም አላገኘም፤ ወደ እኛ መልሶታልና፤ እነሆም፣ ለሞት የሚያደርሰው ምንም አላደረገም፤ እንግዲያስ ቀጥቼ እፈታዋለሁ።”

በዚህ መንገድ ጲላጦስ ኢየሱስ ንጹሕ እንደሆነ ሁለት ጊዜ ተናግሯል። ካህናቱ አሳልፈው የሰጡት ስለ ቀኑበት ብቻ እንደሆነ ስለተገነዘበ ሊፈታው ፈልጓል። ጲላጦስ ኢየሱስን ለመፍታት ጥረት ማድረጉን በቀጠለ ጊዜ ይህንኑ ጥረቱን ከበፊቱ የበለጠ እንዲገፋበት የሚያደርግ ነገር አጋጠመው። በፍርድ ወንበሩ ላይ ተቀምጦ ሳለ ሚስቱ መልእክት በመላክ እንዲህ ስትል አጥብቃ አሳሰበችው:- “ስለ እርሱ ዛሬ በሕልም [ከመለኮታዊ ኃይል የመጣ እንደሆነ ግልጽ ነው] እጅግ መከራ ተቀብያለሁና በዚያ ጻድቅ ሰው ምንም አታድርግ።”

ሆኖም ጲላጦስ ይህን ንጹሕ ሰው መፍታት እንዳለበት ቢያውቅም እንኳ እንዴት ሊፈታው ይችላል? ዮሐንስ 18:​36-38፤ ሉቃስ 23:​4-16፤ ማቴዎስ 27:​12-14, 18, 19፤ 14:​1, 2፤ ማርቆስ 15:​2-5

▪ ኢየሱስ ስለ ንግሥናው የቀረበለትን ጥያቄ የመለሰው እንዴት ነው?

▪ ኢየሱስ በምድራዊ ሕይወቱ ወቅት የመሰከረለት “እውነት” ምንድን ነው?

▪ ጲላጦስ ምን ፍርድ ሰጠ? ሰዎቹ ምን ምላሽ አሳዩ? ጲላጦስ ኢየሱስን ምን አደረገው?

▪ ሄሮድስ አንቲጳስ ማን ነው? ኢየሱስን ማየቱ በጣም ያስደሰተው ለምንድን ነው? በእርሱስ ላይ ምን አደረገበት?

▪ ጲላጦስ ኢየሱስን ለመፍታት ከፍተኛ ፍላጎት ያደረበት ለምንድን ነው?